04/03/2025
የወንፈል ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ከወሎ ቤተ አምሃራ የልማትና የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በድንገተኛ የእሳት አደጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው ለ76 አባወራ አርሶ አደሮች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የስንዴ ድጋፍ አደረገ።
ኮን፦መጋቢት 24/2017 ዓ.ም(ዋድላ ኮሙዩኒኬሽን)
በወንፈል ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ ወረዳ ሰብላቸው በድንገተኛ የእሳት አደጋ ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ከወሎ ቤተ አምሃራ የልማትና የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በዛሬው ዕለት የሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ ከተደረገላቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ አስሜ ካሳውና ወ/ሮ አያል እንደገለጹት ከጥቂት ወራት በፊት ሰብላቸው በእሳት እንደተቃጠለባቸው ገለጸው እስካሁን በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር መቆየታቸውን አብራርተው ዛሬ ይህ ድርጅት ላደረገልን የስንዴ ድጋፍ እናመሰግናለን ያሉት ተጎጂዎቹ የተደረገልን ድጋፍ በቂ ባለመሆኑና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ያሉብን በመሆኑ ረጅ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉልን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የወሎ ቤተ አምሃራ የልማትና የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋዓለም ታደሰ እንደገለጹት በወረዳው ባለፉት ወራት ቤት ንብረታቸው እህል ሰብላቸው በእሳት ቃጠሎ ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ድጋፍ ለማድረግ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በወንፈል ተራድኦ ድርጅት አማካኝነት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት 70 ኩንታል ስንዴ ለ76 አባወራዎች ማድረስ ብንችልም ከችግሩ አንጻር በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ ረጅዎቹ በእኛ ተቋም በኩል አሊያም በግላቸው ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዋድላ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሙልዬ ረታ በበኩላቸው በወረዳችን በ11 ቀበሌዎች ላይ በ1መቶ 54 አባወራዎች የሰብል ክምር ላይና በ62 አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ቃጠሎ መድረሱን አመላክተው ይህ ጉዳት በገንዘብ ሲተመን 31 ሚሊዮን 7መቶ 51ሺህ 2መቶ 80 ብር የሚገመት መሆኑን አብራርተው ይሄው ድርጅትና ሌሎች ረጅ ድርጅቶች ወረዳው ያሉበትን ችግሮች እንዲፈታ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሲልማ ባዬ በድጋፉ ወቅት ተገኝተው ጉዳቱ በደረሰበት ወቅት ቃጠሎውን ለማጥፋት ርብርብ ቢደረግም ማስቆም አለመቻሉን ገልጸው የሚዲያ ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት መረጃውን ተደራሽ በማድረግ በርካታ ረጅ ድርጅቶች የደረሰውን ጉዳት ቢጠይቁም ፈጣን ምላሽ የሰጠን አልነበረም ያሉት አቶ ሲልማ ይሄ ድርጅት ግን ጉዳቱ እንደደረሰ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር በወረዳው ለደረሰው ሁሉንም አይነት ጉዳት ማዳረስ ባንችልም ያሰባሰብነውን ገንዘብ ለተጎጂዎች ማድረስ አለብን በማለት የወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ከአካባቢው ነጋዴዎች ጋር በተመጣጣኝ ዋጋ የገበያ ትስስር በመፍጠር ስንዴ በማቅረብ የተጎጅዎችን የጉዳት መጠን በመለየት በነበረው አጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ በተጎጅዎቹና በወረዳው አስተዳደር ምክር ቤት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።