03/31/2026
የ2019 ዓ.ም የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፍቼ-ጫምባላላ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በደማቁ ተከበረ።
************//**********
ማርች 30, 2026
SMN ዲሲ
የዘንድሮው የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል—ፍቼ-ጫምባላላ—ከምንጊዜውም በላይ በላቀ ድምቀት፣ በህብረት እና በታላቅ መነቃቃት በመላው ዓለም በሚገኙ የሲዳማ ተወላጆችና ወዳጆች ዘንድ እንደተከበረ ታውቋል።
በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ዲሲ፣ አትላንታ ጆርጅያ እና ሲያትል፤ በካናዳ ቶሮንቶ፤ በአውሮፓ ጀርመን በዓረብ ሀገራት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተሞች የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት ውብና ማራኪ በሆኑ ባህላዊ አልባሳት አጊጠው፣ የጥንቱንና ጥልቅ ትርጉም ያለውን ቅርሳቸውን በአንድነት አድምቀውታል።
በየቦታው ታዳሚዎች በሲዳማ ህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነውና በክብር የሚቀርበውን ባህላዊ ምግብ ቡርሳሜ በህብረት ተቋድሰዋል። በተጨማሪም የማህበረሰቡን አንድነትና በረከት በሚያበስረው የሻፈታ ስነ-ስርዓት በዓሉ ይበልጥ በባህላዊ እሴቶች ተሞልቷል።
ልዩ መስህብ የሆነው በስነ-ጥበብ የታጀበ፣ በሚገባ የተደራጀ ሚድያ ባልነበረበት ጊዜ ህዝቡ ወሳኝ መልእክቶችን በሚያዝናና መልኩ የሚያስተላልፍበት የቄጣላ ትዕይንትም አንዱ የበዓሉ ድምቀት አካል ነው።
በየቦታው ተሳታፊዎች የነገዋን ብሩህ ተስፋ በማለም የመልካም ምኞት መግለጫዎችን የተለዋወጡበት፣ የሲዳማን መንፈስና ጥንታዊ ስልጣኔ በዓለም ፊት በኩራት ያሳዩበት ታሪካዊ ዓመት መሆኑ ታምኗል።