የድሬ ድምጽ / Dire Voice

የድሬ ድምጽ / Dire Voice Works to alleviate economic, social, and political problems of Dire Dawa city dwellers.

የትምህርት ቤት ትዝታ!በሰሜናዊ ካሊፎርኒያ የባህል ፣ የንግድ ፣ የፋይናንስ ፣ ና የቴክኖዎሎጂ ማእከል በሆነችው ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ነው ያለሁት:: ውቧ  #ሳንፍራንሲስኮ በፓስፊክ ውቂያኖስና...
05/29/2026

የትምህርት ቤት ትዝታ!

በሰሜናዊ ካሊፎርኒያ የባህል ፣ የንግድ ፣ የፋይናንስ ፣ ና የቴክኖዎሎጂ ማእከል በሆነችው ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ነው ያለሁት:: ውቧ #ሳንፍራንሲስኮ በፓስፊክ ውቂያኖስና ሳንፍራንሲስኮ ቤይ መሃል እንደ ፈርጥ ጉብ ያለች ከተማ ናት:: ነዋሪዎቿ ፍሪስኮ እያሉ ሲያቆላምጧት አንዳንዶቹ ደግሞ "The city” ይሏታል:: #ጎልደን ጌት ብሪጅ ፣ የአልካትራዝ አይላንድ ፣ እንዲሁም ኬብል ካሮቿ ፣ ለብዙዎች ጎብኞቿ መስህብ ናቸው:: ውበቷ የጥበብ ዛርን ይቀሰቅሳል:: "ጥበብ ጠራችን" የሚሉት ሰዎች እንዲህ አይነት አካባቢ ሲያዩ ይሆን?:: ለብ ያለው ሙቀት ፣ ና በዙርያዬ ያሉት ዛፎችን ና አልፎ አልፎ ፊቴን እየዳበሰኝ የሚልያፍው ነፋስ ድንገት #ድሬን አስታወሰኝ:: "የበርሃዋ ንግስት" ያስባሏት ዛፎቿ ፣ ትዝታ የሚሆነው የምሽታ አየሯ ሁሉም በተራ በተራ ተመላለሱብኝ:: ድሬዋን ሳስብ የመጀመሪያ በአእምሮዬ የሚመጣው የምሽት አየሯ ነው:: ነገር ግን #ለድሬ ልጅ እንደ ፈትል ቀለም ቢጎለጎል የማያልቅ ብዙ ብዙ ትዝታዎች አሉት:: ትምህርት ቤቷ ፣ አሸዋው ፣ ታይዋኖቿ ፣ ፍራፍሬዎች ፣ ብስኩቶቿ ፣ የጎዳና ምግቦቿ ስንቱን ልጥቀሰው!

#የድሬ ትምህርት ቤቶች በራሳቸው የትዝታ ማህደር ናቸው:: በአንድ አመት ሁለት ክፍል እያለፍኩ(ተርም መታት ይባላል) ስለሆነ አንድም ደግሞ የተለያዩ አካባቢዎች ስለተማርኩ ነው መሰል አንደኛ ደረጃ ላይ ብዙም ትዝታ የለኝም:: አብዛኛው የትምህርት ቤት ትዝታዬ ሚድል ክላስ ላይ ይጀምራል:: #ዲፖ ትምህርት ቤት ምንም እንኳን ዛሬ የድሬዳዋ "ቴክኒክ ኮሌጅ" ጠቅልሎት ታሪኩ ቢጠፋም በወቅቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነበር:: ነብሳቸውን ይማረውና ዳይሬክተራችን ጋሽ ታደስ ፣ የሂሳብ መምህራን እትዬ ሂሩት ና እትዬ አሰለፈች፣ የኤሌክትሪክ ሲቲ መምህርና ተግባራዊ ትምህርት በመስጠት የሚታወቁት ጋሽ ከቤ ፣ የታሪክ መምህራችን ጋሹ(ለእኔ ደግሞ ዘመዴ ነው) ፣ የሳይንስ መምህራኖቻችን ጋሽ ዘነበና ጋሽ ግርማ ፣ ጏደኛሞቹ ጋሽ ዳንኤልና ማይክል:: ጋሽ ዳንኤል ጆግራፊ መምህር ሲሆን ጋሽ ማይክል (ብቅ ጥልቅ እንለው ነበር) ደግሞ እንግሊዘኛ ነበሩ:: ከመምህራኖቹ ሁሉ "አራዳ ነን" የሚሉት ሁለቱ ነበሩ:: ምርጡና ኩሩው ጎበዝ የእንግሊዘኛ መምህራችንና የእንግሊዘኛ ክበብ አስተባባሪው ጋሽ አንተነህ፣ ጉልበተኛው የስፖርት መምህር ጋሽ አሸብር ና የእርሻ መምህራችን ጋሽ ምትኩ (ዘንጋዳ) ከማልረሳቸው መምህራን ውስጥ ናቸው::

እትዬ ሂሩትና እትዬ አሰለፈች

ሁለቱም ምርጥ የሂሳብ መምህራን ናቸው:: ሂሳብን አቡክተው ይጋግሩታል 😂 :: እትዬ ሂሩት ጠይም ደርባባ ስትሆን ሁሉ ነገሯ እንደ አንድ ጠንካራ እናት ነው:: በርህራሄ የተሞላው አስተያየቷ ፈቅደህ እንድታከብራት የሚያስገድድ መግነጢሳዊ ኃይል አለው:: በዛው ልክ ቁጣዋ እንደ እሳት ይጋረፋል:: በሷ ክፍለ ጊዜ መረበሽ የማይታሰብ ነው! በተለይም በሌሎች ክላሶች በማወክ የሚታወቁ የነበሩ የዛን ጊዜ ጎረምሶች እነ ጥሌ ፣ እነ ቢተው ፣ እነ ሚኪያስ በእርሷ ክፍለ ጊዜ ከእነ መኖራቸውም አይታወቅም:: ይሄ ባህርይዋ ከክፍል ውጭም ያው ነው:: አንዴ ማንም ቀና ብሎ የማያየውን ጥሊን ምን እንዳጠፋ አላውቅም የዩኒፎርም ኳሌታዎቹን ጨምድዳ እየጎተተች ወደ ቢሮ ስትወስደው ትዝ ይለኛል:: 4 ሰው የሚያንከባልለው ጥሌ እንደ በግ እየተጎተት ሄደ እንጅ በሌሎች እንደሚያደርገው እንኳን ሊናገራት ልብሱን ለማስለቀቅ እንኳን አልደፈረም:: ፍቅር ናት ፣ እናት ናት ፣ መምህር ናት በዚያው ልክ ደግሞ ከተቆጣች ሁሉም የሚገዙላት ኃያል ነበረች:: እትዬ ሂሩት በሗላ ላይ ትምህርቷን አሻሽላ ወደ ትልቁ ሃይስኩል ገብታ ነበር:: በሗላ ግን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴኩሪቲ ክፍል እንደተቀላቀለች እራሴው አግኝቻታለሁ:: ዩንቨርስቲ ከጨረስኩ በሗላ ድሬዳዋ በምሰራበት ጊዜ ለስራ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ኤርፖርት ፍትሻ ላይ ተገናኝተናል:: አቤት ደስታዋ! ልጇ እንጅ ተማሪዋ አልመስልም! ስራዋን ትታ ጥምጥም ብላ የደስታ ሳግ እየተናነቃት ሳመችኝ! ጥሩ መምህራን የተማሪዎቻቸው ስኬት የደስታቸውም ጥግ ነው:: እትዬ አሁን የት እና እንዴት እንዳለች አላውቅም:: ይሄን የሚያነብ ና የሚያውቅ ቢያጋራን ውለታን እመልሳለሁ:: Yonatan Solomonየምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል::

ሌላዋ ምርጥ መምህራችን እትዬ አሰለፈች ናት:: ከእትዬ ሂሩት ጋር የሚያመሳስላቸው ሁለቱም የሂሳብ መምህራን መሆናቸው ብቻ ነው:: ፍፁም ይለያያሉ! እትዬ አሰለፈች ከአረማመዷ እስከ ንግግሯ ቀስ ብሎ እንደሚወርድ ኩልል ያለ ውሃ ነው:: ቀጭን ረዘም ያለች ጠይም መልከ ቀና ስትሆን እርጋታዋ እንደ ወረርሽኝ ይጋባል:: ከእርሷ ጋር ሲያወሩም ይሁን በክፍለ ጊዜዋ ሁሉም በእርጋታና በፅሞና እንዲከታተሏት የሚያደርግ ልዩ ተሰጥኦ አላት:: እትዬ የቤተክርስቲያን ልጅ ናት:: የማህበረ ቅዱሳን አባል! የት ቤተክርስቲያን እንደምትሄድ አሁን ትዝ ባይለኝም እኔም ያንጊዜ የደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን አባል ስለነበርኩ በየንግሱ አልፎ አልፎ አያት ነበር:: አይን ላይን ከተጋጨን በስስ ፈገግታዋ ታበረታታኝ ነበር:: እትዬ አሰለፈች አስረድታ ስትጨረስ “If you have Any question or any doubts you’re welcome” የምትላት ነገር በብዙዎቻችን የቀረች አባባል ነች:: ልክ እንደ እትዬ ሂሩት እትዬ አሰለፈችም በሗላ ሃስይስኩል ተገናኝተናል:: በጊዜው የሃስይስኩል የሂሳብ መምህራን ውስጥ አንዱ ከሆነው መምህር ደስታ ጋር በጋብቻ ተጣምረው እንደሚኖሩ ብሰማም አሁን ያለችበትን ሁኔታ ግን አላውቅም:: የትዬን ሁኔታ የሚያውቅ ሰው ቢያካፍለን ደስታችን ወደር የለውም:: ይቀጥላል................

ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደ ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ! #የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ ነው:: "ከሱስ ነፃ የ...
05/02/2026

ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደ ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ!

#የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ ነው:: "ከሱስ ነፃ የሆነ ትውልድን መፍጠር" በሚል በዩኒቨርሲቲው #የአእምሮ ህክምና ትምህር ክፍል አማካኝነት የሰጠው ይሄ ስልጠን ከጫት ውጪ ሌሎች አስፈሪ ሱሶች እየተስፋፉበት ባለባት የድሬዳዋ ከተማና ወጣቱ ትልቅ ስራ ነው:: ወደ ፊት የማገገሚያ ማእከል ተገንብቶ በቋሚነት እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ:: በነገራችን ላይ በህግ ትምህርት ክፍሉ አማካኝነት ለማህበረሰቡ ነፃ #የህግ አገልግሎት እንደሚሰጡም እዛው የሚያስተምር ወዳጄ አጫውቶኛል:: በተለያዩ ጊዚያት በከተማው በሚገኙ የአረጋውያን ማእከላት በተለይም #በአሰገደች አረጋውያን የሚሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎትም የሚያስመሰግን ነው:: ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ዓላማ ማህበራዊ አገልግሎት መወጣት በመሆኑ "እሰይ" የሚያስብል ነው:: እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ (Community Based Training Program) በካሪኩለመ ቢያካት ደግሞ ማህበራዊ አገልግሎቱን የበለጠ ከማስፋቱ በተጨማሪ ለተማሪዎችም ችግር ፈችነትን በተግባር እንዲለማመዱ የሚያስችል በመሆኑ ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል::

04/30/2026

ሐበሻ በሰው ሃገር...!

Arlington, Texas ከተማ በአንድ ካፌ ውስጥ ተቀምጫለሁ:: ጥቁር የጀርባ ባግ ያዘለ ብስል ቀይ መልክ ያለው በግምት 22 ዓመት የሚሆነው መልከ-ቀና ወጣት እኔ ወደ ተቀመጥኩበት አቅጣጫ እየመጣ ነው:: ሐበሻ ይመስላል:: ልክ ከአጠገቤ ሲደርስ በድንገት አይን ለአይን ተጋጨን:: ከእንቅልፍ እንደ ባተተ ሰው ብርግግ አለ:: ትንሽ ግራ ብጋባም ፈገግ ለማለት ሞከርኩ:: ፈገግታዬን ሲያይ ተረጋጋ መሰለኝ እሱም ስስ ፈገግታውን እያሳየኝ ወደ እኔ ተጠጋ:: ከመቀመጫዬ ተነስቼ እጄን ዘረጋሁለት ና "ሃበሻ እንደሆንክ ታስታውቃለህ" አልኩት:: ፈገግ እንዳለና እጄን እንደጨበጥ መቀመጫ ወንበር በአይኑ መፈለግ ጀመረ:: "ኦ ይቅርታ" እኔ ተቀምጨበት የነበረውን ወንበር ወደ እርሱ አዙሬ ለእኔ ከሌላ ጠረጴዛ ሌላ ወንበር ስቤ አመጣሁ ና ተቀመጥኩኝ:: እስካሁን ስስ ፈገግታው እንጅ ምንም ቃል አልወጣውም:: ከዛ ላይ አልተቀመጠም:: "ምነው አረፍ በል እንጅ" ስለው በአገጩ ከጀርባው አውርዶ በሁለት እጆቹ ወደ ያዘው ባግ አመላከተኝ:: እንደተቀመጥኩ ሌላ ወንበር ስቤ አስጠጋሁለት:: ባጉን አስቀምጦ ወንበሩ ላይ "ዘፍ አለ":: ሆሆሆሆ የምር ደክሞታል::

ከጥቂት ሰከንዶች በሗላ የደረቁ ከንፈሮቹን በግድ አላቆ "ይቅርታ" አለኝ:: ሌላ ቃላቶችን ግን ለማውጣት አልቻለም:: "ለምኑ?" ጠየኩት:: "ስለ ደከመኝ ለጥያቄዎችህ መልስ ሳልሰጥህ" አለ:: ችግር የለውም ብዬ ውደ ካፌው ገባሁ:: ለካ ምን መጠጣት እንደሚፈልግም አላውቅም:: ተመልሼ ወጥቼ ምን እንደሚፈልግ ጠየኩት:: "ውሃ" አለ:: ገምቻለሁ ግን ከውሃው ጋር አንድ ችክን በርገር አዘዝኩና "ምን አልባት ትንሽ ነገር መብላትም ከፈለክ ብዬ ነው" ብዬ ሳላስፈቅደው ስላዘዝኩኝ ሃፍረት እየተሰማኝ በርገር ና ውሃን ፊት ለፊቱ አደረኩለት:: "አመሰግናለሁ" ብሎ ትንሽ ከውሃው ተጎንጭቶ በርገሩን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት "እንደራበው" ሳይሆን "ቤቱ ጠግቦ ድግስ እንደሄደ ጎንደሬ" በጥቂት በጥቂቱና ረጋ ብሎ ጨረሰ:: ነብሷን ይማረውና አያቴ አዋቂዎችም ሆነ ህፃናቶች ሰው ቤት ስንሄድ በፍፁም ሳንበላ እንድንሄድ አይፈቅዱልንም ነበር:: አሁን ሳስበው ይገርመኛል! ሰው እንዴት ሰርግ ቤት ጠግቦ ይሄዳል? በተቃራኒው እኛ ቤት ድግስ ሲኖር አያቴ ራሳቸው ሰው በልቶ ከጠገበ በሗላ በየመስሪያው(ሞሰቡ) እየዞሩ "አፈር ስሆን" እያሉ ሲያጎርሱ አያቸው ነበር:: ታዲያ እኛን ለምንድነው ጠግበን እንድንሄድ የሚፈልጉት?

የልጁ ሃይለኛ እንጥሾ ከትዝታዬ መለሰኝ:: ጉድ ነው! አስቀምጨው እንደዛ በኃሳብ ስነጉድ ታዝቦኝ ይሆን? እኔ እንጃ! ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ Bathroom ሄደ:: ዓይኔን ወደ ባጉ ጣል ሳደርግ ዚፑ በጥቂቱ ተከፍቶ ኑሮ የላፕቶፕ ጠርዝና መፅሃፍ ነገር ይታያል:: ኦኬ ተማሪ ነው ማለት ነው:: ሳላስተውለው ድንገት ካጠገቤ ደርሶ ኑሮ "You from here or nah” አለኝ:: ሃሪፍ እንግሊዘኛ እንደሚናገር ገባኝ:: "Nope, not from here, but I pull up all the time." አልኩት:: “Okay bet. What brought you out here?” ህምም Casual-street የሚባለውን የወጣቶች እንግሊዘኛ ነው የሚናገረው:: "የመጣሁበትን እውነቱን መናገር ይኖርብኛል ወይስ ቀይሬ ልንገረው?" እያልኩ እያሰብኩ እያለሁ “ Hey, You ghosted my question…” አለ:: ያስብኩትን ያወቀበኝ መሰለኝ:: ፈጠን ብዬ "I came here for business for one week. What about yourself? አልኩት ሌላ ጥያቄ እኔኑ እንዳይጠይቀኝ ተቻኩዬ:: “That’s awesome. You’re chill too, right? I used to study at the University of Texas at Arlington, but I wasn’t lucky — they kicked me out because I couldn’t pay.” ደነገጥኩኝ:: አሁን ያ የጠወለገ ፊት ፀሐይና ድካም ብቻ ሳይሆን ተስፋ መቁረጥና ደጋፊ ማጣት እንደሆነ ገባኝ:: ጨነቀኝ:: ምን ብዬ ላፅናናው? "That must’ve been hard, but trust me—your story isn’t over. You’ve got way more ahead of you than behind you." ዝም ብዬ ልቤ ያቀበለኝን ነገርኩትና ፊቴን ወደ ጎዳናው ዞር አደርኩት::

“Can’t even lie, bro… it’s been tough. I moved from Ethiopia to a university in Italy back in 2023. After staying there for a while, I applied to UTA, and they accepted me in two months because of my high GPA. I moved to the U.S. in August 2025 and started studying. I thought I’d find some cash jobs and pay for school, but things didn’t go the way I expected, and they dismissed me. I tried every option—inside the school and outside—but nothing worked.” አለኝ:: ከዚህ በሗላ ያለው ዝርዝር ነው:: ዝርዝሩ ምን ያደርግላችሗል? ብቻ ግራ ተጋባሁ:: ምን ልበለው? የምለውስ ነገር እንዴት ነው ችግሩን የሚቀርፍለት? በመጽሐፍ ቅዱስ "ወንድም ወይም እህት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብን ቢያጡ ከእናንተ አንዱም 'በደህና ሂዱ እሳትንም ሙቁ ጥገቡም' ቢላቸው ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል?" የሚለው ድምፅ በጆሮዬ ደጋግሞ አስተጋባ::

ቀና ብዬ አየሁት የኔን ያህል የተጨነቀ አልመስለኝ አለ:: መከራ እኮ ሲበዛ ያደነድናል:: ይላመዳል:: ለምዶት ነው:: ምን እየተማረ እንደነበር ጠየኩት:: የኮምፒዩተር NERD ነው:: ዋው! ስለ Algorithm ስለ Data structure ሲያወራ አጥንቶት ሳይሆን አብሮት የተወለደ ነው ሚመስለው። ከዚህ በፊት የሰራቸውን የተለያዩ የ AI ና ሌሎች ሶሉሽኖችን ሲነግረኝ በጣም ገረመኝ:: web profile ና GitHub ላይ የሰራቸውን ፕሮጀክቶች ዝርዝር አሳየኝ:: ልጁ ትምህርቱን እንኳን ባይጨርስ አሁን ባለው Skillsets የትኛውንም ፕሮጀክት ለመስራት የሚቸግረው አይደለም:: ስለ Upwork ና Fiverr ጠየኩት ያውቃቸዋል:: ይሄ ልጅ ይችን ጽዋዕ ቢያሳልፍ ለራሱ አልፎለት ለሌሎች አጋዥ እንደሚሆን ገባኝ:: ይቅርታ ጠይቄ ስልክ ደወልኩ:: ሁኔታውን ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸውና ለትንሽ ጊዜ እንዲቆይ ጠየኳቸው:: ፈቃደኛ ሆኑ:: ስነግረው ለሰከንድ እንኳን አላቅማማም:: በጥሩ አማረኛ አመስግኖ ደስታው ወደር እንደሌለው ገለፀልኝ:: በነገራችን ላይ ይሄን ያህል ስንጨዋወት ከሐበሻነቴ በቀር ብሔሬ ምን እንደሆነ አልጠየቀኝም እኔም አልጠየኩትም:: እረ እንዴውም ገና ስማችንንም አልተለዋወጥንም! "ግን ስምህን ማን ልበል?" አልኩት:: ሳቅ ተናነቀው:: እኔም ስለገባኝ አብረን ተያይዘን ሳቅን:: ኢትዮጵያውያን ምን አለበት ከኢትዮጲያ ውጭ ያለን ባህርይ ሃገር ቤትም ቢኖረን ኑሮ! ብሄር ምን ቦታ ይኖራት ነበር? እርስ በእርስ መተላለቅስ ከየት ይመጣ ነበር? የሰው ልጅ አንዱ ከሌላው የጎደለውን በፍቅር እንኳን ባይሆን በነጋዴ መንፈስ እንኳን እየተሞላላን ብንኖር ኑሮ መቼ እንጋደል ነበር?

በስምምነት ታሪኩን እንጅ ስሙን ለመጥቀስ ስላልፈለግን እዚህ ላይ ስሙን መጥቀስ አልፈልግም:: አዲስ አበቤ ነው:: ከተማው ላይ ውድ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች በአንዱ ተምሯል:: ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን የመካከለኛ ነጋዴዎች ልጅ በመሆኑ አስተዳደጉ እንዳልተበደለ ሰውነቱና እውቀቱ ከባህርይው ጋር ተጋምደው ያሳብቁበታል:: ማን ያውቃል? አንድ ቀን ሁሉም ነገር ተቀይሮ ታሪኩን ራሱ ያወጋችሁ ይሆናል! በዚህ አጋጣሚ ዌብ ሳይት እንዲሰራላችሁ ና AI, Front End ና Backend ላይ እንዲያግዛችሁ የምትፈልጉ ሰዎች በውስጥ መስመር ብታናግሩኝ አገናኛችሗለሁ:: Nagaan naaf turaa!

04/11/2026
የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ዓለም አቀፍ ማህበር ለክርስትና እምነት ተከታይ ና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን የጾም መፍቻ ና ለበዓል መዋያ የሚሆን ገንዘብ ዛሬ ለ9ኛ ጊዜ (ለዘጠኝ ዓመታት) ድጋፍ ...
04/05/2026

የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ዓለም አቀፍ ማህበር ለክርስትና እምነት ተከታይ ና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን የጾም መፍቻ ና ለበዓል መዋያ የሚሆን ገንዘብ ዛሬ ለ9ኛ ጊዜ (ለዘጠኝ ዓመታት) ድጋፍ አድርጏል:: ማህበሩ ከዚህ በፊት ለእስልምና እምነት ተከታይ አረጋውያንም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል::

ድሬዳዋ ሁለተኛዋ ኢንተርናሽናል ከተማ! #የድሬዳዋ  #ኮሙኒኬሽን  #ጉዳዮች ቢሮ ከድሬ ቴሌቭዥን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን "ቶክ ሾው" እያየሁ ነው:: ፕሮግራሙ የድሬዳዋን የውጭና የዲፕሎማሲ...
03/27/2026

ድሬዳዋ ሁለተኛዋ ኢንተርናሽናል ከተማ!

#የድሬዳዋ #ኮሙኒኬሽን #ጉዳዮች ቢሮ ከድሬ ቴሌቭዥን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን "ቶክ ሾው" እያየሁ ነው:: ፕሮግራሙ የድሬዳዋን የውጭና የዲፕሎማሲ ስራዎችንና ውጤታቸውን የሚዳስስ ሲሆን የአስተዳደሩ የውጭና የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ና የከንቲባው የህግና የአካባቢ ጥበቃ አማካሪ አቶ ጁነዲን የተሳተፉበት ነው:: የተነሱ ነጥቦች ላይ አስተያየት ከምስጠቴ በፊት እኔም ስለ ድሬ የውጭና የዲፕሎማሲ ታሪክ ካነበብኩት አንዳንድ ነጥቦችን ላካፍላችሁ::

የድሬ የውጭና የዲፕሎማሲ ታሪክ ከተመሰረተችበት ከ1902 ይጀምራል:: ከተማዋ የተመሰረተችው በፈረንሳይ የባቡር ኩባንያ አማካኝነት በመሆኑ ለውጭ ሃገር ዲፕሎማቶች ና ማህበረሰቦች መናህሪያ እንድትሆን አድርጏታል:: የከተማው ዲዛይን የፈረንሳይ ማህንዲሶች በመሆኑ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የፈረንሳይ ከተሞችን ትመስል እንደነበር በወቅቱ ያዩአት የፈረንሳይ ፃህፍት መስክረዋል:: የፈረንሳይ ካፑቺን ሚሲዮን በ1909 መመስረቱንም ለዚህ ማሳያ ያደርጉታል::

ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ፣ በውጭ ኩባንያዎች ና በውጭ ዜጎች መናህርያነት የምትታወቀው ድሬ ለንግድና ለትራንስፖርት ያላት ስልታዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ከጣሊያን ወረራ በፊት የተለያዩ ሃገራት ቆንስላዎቻቸውን በድሬደዋ ከፍተው እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል:: ከእነዚህም ውስጥ:- #ፈረንሳይ ቆንስላ (ፓሪስ) ፣ #ብሪታንያ ቆንስላ (ሚካኤሊዲሲ) ፣ #የግሪክ ቆንስላ (ቦሎላኮስ) ፣ #የጣሊያን ቆንስላ (ቶሴሊ) ይጠቀሳሉ::

ድሬዳዋን ሌላው ኢንተርናሽናል ከተማ የሚያስብላት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቦች የሚኖሩባት ከተማ የነበረች መሆኗ ነው:: ከተማዋ የፈረንሳይ ፣ የግሪክ ፣ የጣልያን ፣ የአርመን ፣ የህንድ ና የአረብ ህዝቦች በተለያየ መስክ ተሰማርተው በከተማዋ ይኖሩ እንደነበር እስካሁን ድረስ በከተማው የሚገኙ የመቃብር ስፍራዎች ፣ አብያተ -እምነቶች ፣ ልዩ ልዩ ህንፃዎችና በኗሪው የሚታዩ የአመጋገብ ፣ የአለባበስና ልዩ ልዩ ባህሎች ህያው ምስክሮች ናቸው::

በነገራችን ላይ ድሬ የብሪታኒያ ወታደራዊ #አስተዳደር ዋና መቀመጫም ነበረች:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጣሊያን ከተሸነፈች በሗላ ድሬዳዋ ከ1941 - 1947 ዓም ድረስ በብሪታኒያ ወታደራዊ አስተዳደር (Reserved Areas) ስር ነበረች:: ከተማዋ ከጂቡቲ ጋር ያላት የኢኮኖሚ ና የታሪክ ትስስር እጅግ ጠንካራ ነው:: ጂቡቲ በከተማው እምብርት የቆንስላ ፅህፈት ቤት ያላት ሲሆን በባቡር ፣ በመንገድና ፣ በአየር ትራንስፖርትም ጠንካራ ትስስር ተፈጥሯል:: በቅርብ ጊዚያትም ከሱማሌ ላንድና ከጂቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት በከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ፣ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገው March 3,2020 ላይ ባሳተመው ጥናት ያትታል::

#መውጫ

ድሬ ከላይ የተጠቀሱት ምክኒያቶች ሜትሮ ፖሊታን (Metropolitan) ከተማ ሲያደርጋት በዲፕሎማሲውም የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ከተማ እንደሆነች ያረጋግጣል:: በመግቢያው ላይ በጠቀስኩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ባዘጋጀው ውይይት ኃላፊዎች እንደጠቀሱት አስተዳደሩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር (የእህት ከተማ ስምምነት) በማድረጉ የተገኙ ውጤቶ እንደተጠበቁ ሁኖ ያላት ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ እውነቶች አሁን ከተፈራረመቻቸውም ጋር ይሁን ከሌሎች ሃገሮች ከተሞች ጋር ትስስር በመፍጠር ኢንቨስትመንት ፣ ቴክኖዎሎጂ ና እውቀት በሰፊው ወደ ከተማዋ የሚመጣበትን ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል:: በውጭ የሚገኙ የከተማው ተወላጆችን በማንቀሳቅስም በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት መሳብ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ቢደረግ ፣ #ዲያስፖራውም "የእኔ" ብሎ ቢሰራ ከተማችንን በሁሉም ረገድ ከአውሮፓ ከተሞች አንዷ ማድረግ ያን ያህል ከባድ አይመስለኝም:: ድሬዳዋችን ባሏት እሴቶችና ታሪክ እንዲሁም የቱሪዝም መስህቦች ለከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን ሰፊ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ #የፌደራል መንግስቱም በልዩ ትኩረት በጀት መድቦ ና ትከረት ሰጥቶ ቢሰራ ከፍተኛ ውጤት እንደሚገኝበት ለሁላችንም እሙን ነው::

9ኛ ዙር(ዓመት) የአረጋዊያን ድጋፍ!ማህበራችን የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ዓለም-አቀፍ ማህበር እንደተለመደው ለ9ኛ ጊዜ (ዓመት) የድሬዳዋ ሙስሊም እምነት ተከታይ አቅመ ደካሞችን የበዓል መዋያ...
03/23/2026

9ኛ ዙር(ዓመት) የአረጋዊያን ድጋፍ!

ማህበራችን የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ዓለም-አቀፍ ማህበር እንደተለመደው ለ9ኛ ጊዜ (ዓመት) የድሬዳዋ ሙስሊም እምነት ተከታይ አቅመ ደካሞችን የበዓል መዋያ ስጦታ በመስጠት ጎብኝቷል:: የክርስትና እምነት ተከታዮችንም እንዲሁ ጾሙ ሲፈታ በየቤታቸው የሚጎበኝ ይሆናል:: ማህበሩ ይሄን ዓመታዊ ፕሮግራም ወደ ወርሃዊ ፕሮጀክት በመቀየር ለ60 አረጋዊያን በቋሚነት የሚረዳ ሲሆን ይሄም የጤና ኢንሹራንስ ፣ የምግብ ፣ ና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ያጠቃልላል:: ማህበሩ ይሄን በጎ ተግባር ያለማቋረጥ ለ9 ዓመታት 100 ተማሪዎችንና አረጋውያንን እንዲረዳ ከኪሳችሁ በማውጣት የምትደግፉ የማህበሩ አባላትን ና ድሬዳዋ ላይ በጉልበታችሁ ፣ በጊዚያችሁና ፣ በጉልበታችሁ ከእኛ ጋር የቆማችሁትን ሁሉ ከልብ ያመሰግናል::


አፍሪካ አንድ ምሁር  አጣች!ዶክተር  እሸቱ ድሬዳዋ ካፈራቻቸውና ለሃገርም ለአህጉርም በእውቀታቸው አስተዋፅኦ ካደረጉ ምሁራን አንዱ ነው:: እሼን ድሬዳዋ ሃይስኩል ሁነን እኔ 12 እርሱ ፕሪፓ...
12/03/2025

አፍሪካ አንድ ምሁር አጣች!

ዶክተር እሸቱ ድሬዳዋ ካፈራቻቸውና ለሃገርም ለአህጉርም በእውቀታቸው አስተዋፅኦ ካደረጉ ምሁራን አንዱ ነው:: እሼን ድሬዳዋ ሃይስኩል ሁነን እኔ 12 እርሱ ፕሪፓራቶሪ 11ኛ ክፍል ሁኖ በአይን እንተዋወቃለን:: የተቀራረብነው በ1996 ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ ከገባ በሗላ ነው:: እኔ አንድ አመት ቀድሜ ስለገባሁና በዩኒቨርሲቲው የ"ድሬዳዋ ልጆች ኔትወርክ" የሚባልና ከድሬዳዋ የሚመጡ ተማሪዎችን በመቀበል ጌት ቱጌዘር የሚያዘጋጅ ማህበር (የዛሬው ፖለቲከኛው የዛኔው የድሬዳዋ ልጆች አሰባሳቢ Daniel Berhane ና ጏደኞቹ የመሰረቱት ይመስለኛል) ኮሚቴ ስለነበርኩ ና በግቢ ጉባኤም እንቀሳቀስ ስለነበር ያንጊዜ ወደ ዩንቨርስቲው ከገቡት የድሬ ልጆች ጋር ጥሩ ቀረቤታ ነበረኝ:: ከእሼም ጋር የተቀራረብነው በዚያ አጋጣሚ ነው:: ምንም እንኳን ያንጊዜ ከአንድ ምንጭ እንደተቀዳ ውሃ በትምህርትም በመግባባትም ሁሉም አንድ ቢሆኑም እሼ ከሌሎች በተለየ በነበረው እርጋታ የተላበሰ ጨዋታውና ለትምህርት በነበረው ትጋት ከሌሎቹ ለየት ይል ነበር:: በትምህርትም በቁም ነገርም ለሁሉም ምሳሌ ከነበሩት ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነበር ብል ማጋነን አይደለም::

የዛሬ ሁለት ወር አካባቢ October 25 ከረጅም ጊዜ በሗላ ፌስቡክ ላይ ስፖስት የመጀመሪያ ኢንቦክስ ገባልኝ ስከፍተው እሼ ነው :: ይመቼው አይመቼው ሳላረጋግጥ ደወልኩት ከቃላቶቹ ጋር ሁሌም ከፊቱ የማይጠፋው ፈገግታውን በአይነ ልቦናየው እያየሁ ካጠገቡ ያለሁ ያህል አወጋሁት:: ከዓመታት በፊት አሜሪካ ለስራ መጥቶ ከመገናኝታችን ውጭ ና አልፎ አልፎ በቴክስት ሰላምታ ከመለዋወጥ በስተቀር በስልክ ስናወራ ከርጅም ጊዜ በሗላ መሆኑ ነው:: እሼ እውቀቱ ና አስተሳሰቡ እንጅ ሰው አክባሪነቱ ትህትናውና ተጫዋችነቱ እንዳለ ነው:: አዲስ አበባ እንደመጣሁ ነገርኩት:: በደስታ በተሞላ ድምፅ በቅርብ እንደሚመጣና በጋራ የምናውቃቸውን የድሬዳዋ ልጆች ስም እየጠራ የምቆይ ከሆነ ከእነሱ ጋር ሰብሰብ ብለን እንደምንገናኝ ቀጠሮ ያዝን:: እሼ ምክኒያት ፈጥረው ሊቀሩበት ከማይችሉት ጋር ቀጠሮ ነበረውና ከእኔ ጋር መገናኘት አልቻልንም::

ፕሮፌሰር እሸቱ በጅማ ዩኒቨርስቲ በ Health Promotion and Behavioral healthcare science የድግሪና ማስተር ዲግሪውን በመስራት በከፍተኛ ውጤት ተመርቆ እዛው ጅማ ዩንቨርስቲ ለመቅረት ችሏል::

በ1472 እኤአ በተመሰረተው በጀርመን ሙንሽን(ሙኒክ) ከተማ በሚገኘው Ludwig-Maximilians-Universität München በዓለም አቀፍ ጤና ፒኤችዲውን የሰራ ሲሆን ከ70 በላይ peer reviewed ሳይንቲፊክ አርቲክልስ በተለያዩ ጆርናሎች ላይ አሳትሟል::

ገና 30 አመት ሳይሞላው ፒኤችዲውን ሰርቷል:: 35 ሳይሆነው አሶሼት ፕሮፌሰር ለመሆን ችሏል:: ለትምህርትና ማህበረሰብን ለመርዳት የቆረብ እስኪመስል በጅማ ካስተማረው ውጭ ለ10 ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሶሼት ፕሮፌሰር በመሆን በርካታ የማስተርስና የፒኤቺዲ ተማሪዎችን በማማከር አስመርቋል::

ዶክተር እሼቱ “Young Public Health Researcher Award” ከኢትዮጲያ ፐብሊክ ሄልዝ አሶሴሽን የተቀበለ ሲሆን የኢትዮጵያ የጤና ልማት ጆርናል (EJHD) ስራ አስኪያጅና ማኔጀር ሆኖ አገልግሏል:: እስከ እለተ እረፍቱ ደግሞ የዓለም የህክምና ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ጆርናል ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል ሆና እያገለገለ ነበር::

እሼ እንደ ትምህርቱ በጊዜ ትዳር የመሰረተ ሲሆን የሶስት ልጆች አባት አባት ነበር:: እስካረፈበት እለት ድረስ መቀመጫውን ናይሮቢ ባደረገው African Population and Health Research Cente (APHRC) ሪሰርች ሳይንቲስት ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር:: በዚህ ተቋምና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በእርሱ መሪነት በሚልዮኖች የሚቆጠር በጀት ያላቸውን የጥናት ፕሮጀክቶች ለስኬት ያበቃ ሲሆን ከመሞቱ በፊት የ1.9 ሚልዮን ዶላር ፕሮጀክት በመምራት ይገኝ ነበር::

ሃገራችንም አህጉራችንም ካሏቸው ለእውቀትና ለማህበረሰብ አገልግሎት ራሳቸውን ከሰጡ ጥቂት ምሁራን ውስጥ አንዱን አጥተዋል:: ብዙ ብዙ መስራት ይችል የነበረው የድሬው ወጣት ምሁር በድንገተኛ ሞት ተለይቶናል:: ፈጣሪ ነብሱን በሚወዳቸው ቅዱሳን እጅ ያሳርፍልን:: ለባለቤቱ ለልጆቹ ለቤተሰቦቹና ለጏደኞቹ መፅናናትን ይስጥልን::

ድሬዳዋ የሚገኙ የማህበሩ አባላትና አመራሮች በአሰገደች የአረጋዊያን መርጃ ማእከል አረጋውያንን ሲንከባከቡ የሚያሳይ
11/15/2025

ድሬዳዋ የሚገኙ የማህበሩ አባላትና አመራሮች በአሰገደች የአረጋዊያን መርጃ ማእከል አረጋውያንን ሲንከባከቡ የሚያሳይ

Address

11 Grand Terrace
Livingston, NJ
07039

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የድሬ ድምጽ / Dire Voice posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share