Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት

Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት Former Ethiopian armed force
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት
(1)

FORMER ETHIOPIAN ARMED FORCES WORLDWIDE is organized for charitable and humanitarian purposes; with the following Mission: FEAFWW is a non-government, non-profit, non-partisan, human rights organization established to promote social, economic, and legal rights of Ethiopian armed force veterans living worldwide.

06/14/2026

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ ባልደረባ የነበረው ሻምበል ደረጀ አስፋው November 17,2025 ዓም ከሚኖርበት ሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ ለረጅም ጊዜያት ህክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
አምላክ የሻምበል ደረጄን ነፍስ ይማር መላው የገፃችን ተከታዮች ለቤተሰቡና ለቀድሞው ለስራ ባልደረቦቹ መፅናናትን እንመኛለን😭😭😭

Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት

06/14/2026

የሀገሪቱን ወደር የሌለው የላቀ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳይ የተሸለሙ እውቅ ጀግና የቀድሞው አየር ወለድ ክፍለጦር አዛዥ ናቸው።ማዕረጋቸውንና ስማቸውን ላወቀ ሜዳልያ ይሸለማል። ናቅፋ ላይስ ምን ጀብዱ ፈጸሙ ?ስለጀግንነታቸውም በኮሜንት ላስቀመጠና የላቀ ላይክ ያገኛ የበለጠ ተሸላሚ ይሆናል።
Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት

💚💛❤ምግባረ-መልካሙ ኢትዮጵያዊስለሺ መንገሻ ከ1934 እስከ 2018 ዓ.ም💚💛❤     ሠሎሞን ለማ ገመቹ  - ግዮን መጽሔት ላይ የሠፈረ.  🔵➡️   ግላዊ ዕይታ ወ ምልከታ.ከነገረ-ቀደም :-...
06/10/2026

💚💛❤
ምግባረ-መልካሙ ኢትዮጵያዊ
ስለሺ መንገሻ
ከ1934 እስከ 2018 ዓ.ም
💚💛❤
ሠሎሞን ለማ ገመቹ - ግዮን መጽሔት ላይ የሠፈረ.
🔵➡️ ግላዊ ዕይታ ወ ምልከታ.

ከነገረ-ቀደም :- በ2018 ዓ.ም ከዚህኛው ዓለም ድካም ካረፉት የወታደራዊው አብዮታዊ መንግሥት ባለሥልጣኖች መካካል ጓድ ስለሺ መንገሻ፣ ጓድ አሸብር አማረ እና ቆፍጣናው የምሕንድስና ሙያ ሊቀ -ሊቃውንት ጓድ ካሣ ገብሬ የሚጠቀሱ ናቸው።
👉የጓድ አሸብር አማረ የአርባ ቀን የመታሰቢያ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ሰኔ 6/2018 ዓ.ም ማለዳ በመንበረ ጸባዖት ቀድሞ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን (4 ኪሎ) የሚካሄድ ሲሆን ፤ የጓድ ካሣ ገብሬ ካሣ የጸሎተ ፍትሃትና የማንነታቸው መዘከሪያ ሥርዓት ከቤተሰቦቻቸው ዕይታ አኳያ ብቻ... ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከፍ ሲል በተገለጸው ቤተ-ክርስቲያን መከናወኑ የሚታወቅ ነው።
👉 የሆነው ሆኖ... ወደፊት ጓድ አሸብር አማረን እና ጓድ ካሣ ገብሬን በተመለከተ ግላዊ ዕይታ ወ ምልከታዬን በዚሁ ማኅበራዊ መድረክ የማቀርብ ይሆናል።
👇
🔵👉 ለዛሬው ግን በሞት ለተለዩን ጓዶች ነፍስ ይማር! ቤተሰቦቻቸውንም ኃያሉ እግዚአብሔር ያጽናናልን.... እያልኩ:- እነሆ ምግባረ-መልካሙን ኢትዮጵያዊ ስለሺ መንገሻን የሚመለከተውን ጥሑፌን ትመለከቱት ዘንድ... ተይህ በታች ሰድሬዋለሁ👇

🔵👉 ይህን የጓድ ስለሺ መንገሻን ማንነት የሚመለከት ጽሑፍ ሳዘጋጅ ‹‹አንቱ›› ከማለት ይልቅ ‹‹አንተ›› ማለቱን መርጬአለሁ፡፡ ይህን ምርጫ ያደረኩትም ስለ እሱ ማንነት፣ ባሕሪይና ተግባር… የማደርገውን ገለጻ ‹‹እሳቸው…›› እያልኩና ከዘልማዳዊ የአክብሮት ቃል ጋር እየተሟገትኩ ወደፊት ለመቀጠል መሞከሬ፤ ብዕሬን ያነሳሁበትን ዋንኛ ጉዳይ አያቀናልኝም፣ አያሰምርልኝም፣ ስሜቴንም ፈታ አያደርግልኝም ብዬ በመገመቴ ነው፡፡
🔵👉ሌላው ስለ ስለሺ ያቀረብኩትን ጽሑፍ ‹አንተ›› እያልኩ ማስኬዱን የፈለኩበት ምክንያት፤ ግለሰቡ የነበረውን ማኅበረሰባዊ የክብር ሥፍራ በፍፁም በመዘንጋትም ይሁን ባለማስተዋል አይደለም፡፡ ይልቁንም አንተ ብዬ ስለ ጓድ ስለሺ መንገሻ በዚህ መጽሔት የሠፈረውንና ምግባረ-መልካምነቱን የሚያመለክተውን ጽሑፍ የቀመርኩት፤ ለባለጉዳዩ ያለኝ ቀረቤታ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለአንባቢውም ሩቅ ሆኖ እንዳይሰማው በሚል ደግ እሳቤ ነው፡፡ አንተ… እያሉ ግለሰቡን የሚመለከተውን ጽሑፍ መዘወሩም፤ ለአንባቢውም ይሁን ለጸሐፊው የማንበብንም ይሁን የመፃፍን ለቀቅ፣ ፈታ ያለ ነፃነት የሚያጎናጽፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡
🔵👉 ያም ብቻ ሳይሆን… ለግለሰቡ ካለኝ የበረታ አክብሮትና ወንድማዊ ስሜት አንጻር፤ ይህን ጽሑፍ በመጀመሪያ ደረጃ ነጋሪ መደብ አንተ እያልኩ መቀጠሉን መርጬአለሁ፡፡ በእኔ መረዳትና ግንዛቤ፤ ጓድ ስለሺ መንገሻ ለብዙዎች የወንድምነትን፣ የአባትነትን ያህል ቀርቦ በማኅበረሰብ ውስጥ የኖረ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ፤ እሱን የሚመለከተውን ጉዳይ ‹‹እሳቸው…›› እያሉ ማስኬዱ፤ የቅርብን፣ የራስን ሰው… ከነበረው የበዛ ትኅትና፣ የሃገር አፍቃሪነት፣ የወገን ወዳድነት ባሕሪ መሰጠቱ አኳያ ሲመዘን ወይም ሲለካ፤ ስለ እሱ በአንቱታ ደረጃ የሚቀርበው ወደ መሠረታዊ ማንነቱ እውነት ያጋደለ ጽሑፍ፤ የመንገር፣ የማስረዳት፣ የማሳወቅ፣ የመመስከር ጉልበቱን፣ ውበትና ጣዕሙን ያጣል የሚል ግንዛቤ በመውሰዴም፤ እነሆ ስለ ምግባረ-መልካሙ ኢትዮጵያዊ የሚያወሳው ጽሑፌ አንተ… እያለ በመተረኩ ሂደት ቀጥሏል፡፡
👇
🔵👉 ጓድ ስለሺ መንገሻ ከዛሬ ሰማንያ አራት ዓመታት በፊት ነበር የተወለደው፡፡ በቀድሞ አርሲ ክፍለ ሃገር፣ ሶዴ በሚባል ወረዳ፣ ‹‹ሃሰን ዳቦ›› ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር፡፡ እና እሱ በወርሃ ኅዳር ሦስተኛ ቀን 1934 ዓ.ም ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ የወላጅ አባቱ የባሻ መንገሻ መቼአምኜህ የአብራክና የእናቱ የወይዘሮ ደማ አለሚ የማኅፀን ፍሬ ሆኖ፡፡ ዳኸ፡፡ አደገ፡፡ ተመነደገ፡፡ በአባት እናቱ እንክብካቤ በጨዋነት ተይዞ እንደ ዘመኑ የዕድሜ ዕኩዮቹ የቤተ-ክህነቱን ትምህርት እየተከታተለ… የታዳጊነት ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ከቤተ-ክህነት ትምህርቱም በመቀጠል ዘመናዊ ዕውቀትን ለመቅሰም ይችል ዘንድ ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አመራ፡፡
👉 መደበኛ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ሲከታተል ከቆየም በኋላ በአፍለኛ የወጣትነት ዕድሜው እናት ሃገር ኢትዮጵያን በውትድርና ሙያ የማገልገል ፍላጎቱ የሕይወት ምህዋሩ ኮንፓስ… በክብር ዘበኛ ባልደረብነት የውትድርናን ኑሮ ለቀጥል ወደሚችልበት አቅጣጫ መራው፡፡በወርሃ መስከረም 1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ አንድነት ዘመን ሠራዊት ባልደረባ ከሆነ ወዲህ፤ እስከ የካቲት ወር 1966 ዓ.ም ድረስ፤ በኦጋዴን፣ በጅጅጋ፣ በቀብሪ-ደሐርና በሌሎችም ግንባሮች ግዳጆቹን ሲወጣ፣ ከእሱ የሚጠበቀውን የውትድርና በተለይም በወታደራዊ ስፖርት ዘርፍ፤ በመረብ-ኳስና በቅርጫት ኳስ… ውድድሮች በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት ተሳትፎ ሲያደርግ ቆየ፡፡
👉 በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት መቀስቀስ ማግስት፤ ከየጦር ክፍሉ በውክልና ተጠርተውና ተመርጠው… የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባበሪ ኮሚቴ (ደርግን) ለመመስረት ከተሰባሰቡት አብዮታዊያን መኮንንኖች፣ የበታች ሹሞችና ወታደሮች መካከል፤ የነበረበትን የክብር ዘበኛ ጦር በመወከል አንደኛው ሆኖ ተገኘ፡፡
👉 በሂደትም ባሳየው የነቃ ተሳትፎ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተመሰረተው የአስተባባሪው ኮሚቴ ወይም የደርግ ዋንኛ አባል ሆኖ በድምፅ ብልጫ ተመረጠ፡፡ ዕድል፣ ዕጣ-ፈንታውና ኮከቡ በመኖር መንገዱ ላይ ቆማ የሚጓዝበትን መንገድ የተለመችለት በመሆኑ፤ ስለሺ መንገሻ እንደ ሌሎቹ 107 የደርግ አባላት ሁሉ፤ ሃገሩን፣ ወገኑን፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ብሎም አብዮታዊ ኃላፊነትን የመወጣት አደራን መቀበልና ከእሱ የሚጠበቀውን የዜግነት ድርሻ የመወጣቱን ግዳጅ … ሳይወድ ብግድ ተቀበለ፡፡
👉 በ1968 ዓ.ም ወደ ሃገረ ሃንጋሪ ተጉዘው የፖለቲካ ንቃተ-ሕሊና ማዳበሪያ ትምህርት ከተከታተሉትና በሰርተፍኬትም ተመርቀው ወደ እናት ሃገር ኢትዮጵያ ከተመለሱት ‹‹አብዮታዊያን ጓዶች›› መካከል አንደኛው የሆነው የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፤ በቅድሚያ ለአንድ ዓመት ያህል ማለትም ከ1969 እስከ 1970 ዓ.ም ባለው ጊዜ የአርሲ ክፍለ ሃገር የደርግ ዋንኛ ተጠሪ ሆኖ አገልግሏል፡፡
👉 በመቀጠልም ከ1970 እስከ 1971 በነበሩት ጊዜያት በደርግ ዋና ተጠሪነቱ በትግራይ ክፍለ ሃገር ውስጥ ሠርቷል፡፡ ከፍ ሲል ከተገለጹት አገልግሎቶቹና የመንግሥታዊም ይሁን የድርጅታዊ የኃላፊነት ሥራዎቹ በተጨማሪ፤ ጓድ ስለሺ መንገሻ ከ1971 እስከ 1980 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያት ውስጥ የአርሲ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ፣ የክፍለ ሃገሩ የኢሠፓአኮ 1ኛ ጸሐፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ እንዲሁም የአርሲ ክፍለ ሃገር ዋና አስተዳዳሪና በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የክፍለ ሃገሩ አንደኛ ፀሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡
👉 ከ1980 እስከ 1983 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት አጋማሽ በነበሩት ጊዜያትም፤ ጓድ የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ በትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደር የኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖም እያገለገለ ቆይቷል፡፡ በወህኒ በነበረበት ዓመታት የሕግ ሙያን አጥንቶ በዲፕሎም ለመመረቅ የበቃው፣ ከወህኒ ከወጣም በኋላ በተለያዩ የግል ተቋማት በአስተዳደርና በምርት ክፍል ኃላፊነት የሠራው፣ ከወህኒ የተፈቱ የደርግና የኢሠፓ አባላት እንዲሁም በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በተለያዩ የሃገርና የሕዝብ አስተዳደር ቦታ… ሲያገለግሉ የነበሩ ዜጎች መስከረም 23 ቀን 2003 ዓ.ም ያቋቋሙት የሰው ለሰው መረዳጃ ዕድር መሥራችና ሊቀመንበር ሆኖ ያገለገለው ባለ መልካም ምግባሩ ስለሺ መንገሻ፤ አንገቱን እንዳቀረቀረ ከጨዋነቱ ጋር ከዚህ ዓለም የተለየው፤ ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር፡፡ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓትም የተፈፀመው በአዲስ አበባ ከተማ በሳሊተ-ምህረት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን ታኅሣሥ 19 ቀን በጣም ጥቂት ወዳጆቹና በአጋጣሚ ማረፉን የሰሙ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ነው፡፡

🔵➡️ ስለሺ መንገሻ ከ1969 እስከ 1983 ዓ.ም መጀመሪያ ጊዜ ድረስ ለእናት ሃገር ኢትዮጵያና ለወገኖቹ መሻሻልና መለወጥ ሲል በቅንነት ባበረከተው አስተዋጽዖ፤ እንዲሁም ሕዝብን አወያይቶ፣ በአክብሮት መንፈስ አግባብቶና አሳምኖ፣ ብሎም አስተባብሮ ባከናወናቸው የሃገራዊ ኃላፊነቶቹ ወሳኝ ተግባራት፤ በተለይም የሠይድ ባሬ ወራሪ ሠራዊት የኢትዮጵያን ግዛት በእጁ ለማድረግ ሰፊና ጥልቅ ወረራ በፈፀመበት ጊዜ፤ የእናት ሃገር ጥሪውን ሰምቶ አደባባይ የወጣውን፣ ለመዝመት! ለመሰለፍና ለመሰየፍ የተዘጋጀውን ኢትዮጵያዊ የሃገሩ ተከላካይና ጠባቂ ኃይል ሆኖ በወታደራዊ አቋም እንዲደራጅ በማድረግ፣ በትግራይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሣና በቋንቋ… ለመከፋፈል የተነሱትን አስገንጣይ ገንጣይ ወንበዴዎች ለመፋለም፤ የትግራይ ክፍለ ሃገር ወጣቶች በታሪክ ውስጥ አንፀባራቂ የኢትዮጵያ አንድነት መከታነት ስም በነበረው የዘንዶ ተዋጊ ሠራዊት አባል እንዲሆኑ በማድረግ… እና በሌሎችም መሰል ተግባራት በተወጣው ይህ ቀረሽ የማይባል የኢትዮጵያዊነቱ ሚና፡- የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አንደኛ ደረጃ ሜዳይ፣ የየካቲት አብዮት 1ኛ ደረጃ የክብር ኒሻን ለመሸለም የበቃ ነው፡፡

👉በጥቅሉ ስለሺ መንገሻ ከ1968 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት፤ በሃገረ ኢትዮጵያ በቀድሞ አርሲ እና ትግራይ ክፍለ ሃገራት በደንብ ይታወቃል፡፡ በተለይ ሕዝቡ እሱን የሚያውቀው በተግባቦቱ፣ በዝምታው፣ በታታሪ ሠራተኛነቱ፣ በይበልጥም ሰዎችን በዕኩልነት፣ በወንድማዊነትና በአሰላሳይ አባታዊ ስሜት የሚመለከት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ምግባረ-መልካምነቱ ተወዶ እንዲከበር አድርጎታል፡፡
👉የእሱ ተወዶ ተከባሪነት… በዜጎች ዘንድ ብቻ አይደለም፡፡ በፀጥታ የሚሠራ፣ ከሕዝብ ጋር ለመቀራረብና ተቀራርቦም አስፈላጊዎቹን የልማት ተግባራት ለማከናወን፤ ሕዝባዊ ፣ መንግሥታዊ፣ ሃገራዊ ሥራዎች ፍሬያማ በሚሆኑበት ደረጃ እንዲተገበሩ በማድረግ ክህሎቱ… የደርግ አባላት፣ የኢሠፓ አባላት፣ የክፍለ ሃገር አስተዳዳሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ወዛደሮች፣ ገበሬዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ስሙን በመልካም ያነሱታል፡፡ ስሙን አንስተውም ብቻ አያበቁም፡፡
👉 ወደው የሚያከብሩት ሰው መሆኑን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባራቸው ጭምር ይገልጹለታል፡፡ ስለሺ መንገሻ፤ ከፍ ብሎ ይመራል፡፡ ያስተባብራል፡፡ ዝቅ ብሎ ይወያያል፡፡ ምክር፣ ለመፍትኄ ይጠቅማሉ ያላቸውን ሐሣቦች ይጠይቃል፡፡ ሐሣብ ያዋጣል፡፡ በነፃነት ስሜት በሕዝቡ መሀል ይመላለሳል፡፡ ከወጣቶች ጋር በእስፖርታዊ ውድድር ይሳተፋል፡፡ ሳቅ ጨዋታ በሚኖበት ሥፍራ በቁጥብ ፈገግታውና በደርባባ የአስተዋይነቱ ገጽታው ታጅቦ በወገኖቹ መሀል ተቀምጦ የዚያ ሳቅ ጨዋታ ደስታ ታጋሪ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚያም ወደ እናት ሃገር ሥራው ያልፋል፡፡

🔵👉 አዎ!.... እሱ በዘመነ-ደርግ ‹‹መማር፣ መማር፣ አሁንም መማር›› የሚለውን መፈክር ‹‹መሥራት፣ መሥራት፣ አሁንም መሥራት›› ወደሚለው መርህ በተግባር የለወጠ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡ በመጋቢት ወር 1978 ዓ.ም በአሰላ ከተማ የታተመው ‹‹መንደር ምሥረታ በአርሲ›› የተሰኘው መጽሔት በገጾቹ ላይ ካሰፈራቸው መልዕክቶች መካከል፡- ‹‹ዛሬ አርሶ አደሩ በመንደር ተሰባስቦ ለወደፊት ትግሉና ድሉ ምቹ ሁናቴ እንደፈጠረ ሁሉ፤ ከአሁኑ የበልግ ወቅት አንስቶ ለእርሻው ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምርት የራሱን ሕይወትና የሃገሩን ኢኮኖሚያዊ ዕደገት ማዳበር እንዲችል ብሎም አካባቢውንና ራሱን ከማንኛውም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጥቃት እንዲከላከል፤ የፓርቲ የመንግሥትና የማኅበራት በአጠቃላይም የክፍለ ሃገሩ ሕዝብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡…›› የሚለውን የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻን ቃል አስፍሯል፡፡
👉 ስለሺ መንገሻና በወቅቱ ከአጠገባቸው የነበሩት በልማት ላይ ልዩ ትኩረት ያደረጉ የተግባር ሰዎች፤ የመንደር ምሥረተናውን ዓላማ ለማሳከት፤ ሕብረተሰቡን አስተባብረው ባደረጉት የተግባር እንቅስቃሴ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ በአርሲ ክፍለ ሃገር በሚገኙት የጭላሎ፣ የአርባጉጉ እና የጢቾ አውራጃዎች፡- 231 የመሠረተ ልማት ጣቢያዎችን፣ 124 የባሕል አዳራሾችን፣ 44 የመዝናኛ ሥፍራዎችን ወይም ማዕከሎችን፣ 17 የአፀደ-ሕፃናት ማለትም የመዋዕለ ሕፃናት ተቋሞችን፣ እንዲሁም 102 የተጣራ ውሃ ማመንጨት የሚችሉ የውሃ ኩሬ ግንባታዎችን ሥራ ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ ከነዚህ ተግባራት በተጓዳኝ 570 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የጥርጊያ መንገድም በአርሲ ክፍለ ሃገር መሥራት የቻሉ ሲሆን፤ 46.28 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይም ለአፈር ጥበቃና እንክብካቤ ብሎም ለእርሻው ሥራ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል የእርከን ሥራም አከናውነዋል፡፡
👇
💚💛❤ 🔵👉 እንደመውጫ፡- ‹‹በጣም ቅን፣ ንፁህ፣ በሙስና ወይም በምዝበራና ብኩንነት የማይታወቅ፣ ሕዝባዊ የሆነ ሰው ነው ጓድ ስለሺ መንገሻ፡፡ ጥሩ አስተዳደሪ፣ ተግባቢ፣ በአስተዋይነት ለሃገር ለውጥና ዕድገት ከሠሩ የደርግ አባላት መካከል አንደኛው ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ልዩ የሆነና የምስጉን ባሕሪ ባለቤት፡፡ ‹እኔ አንደኛ የፓርቲ ጸሐፊ ነኝ …› ብሎ የማይኮፈስ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ከሕዝቡ የማይለይ፣ አነሳሱን የሚያወቅ፣ አስቀድሞ የነበረበትን ቦታ ያልረሳ ታማኝኛ ጨዋ ወገናችን ነበር፡፡ በሕይወቱ መጨረሻም በእጅ ላይ ለራሱ መታከሚያ ሊሆነው የሚችል ጥቂት ብር ዕንኳን ያልነበረው፤ በደርግ አባልነቱም እንደ ጓዶቹ ሁሉ ለሃያ ዓመታት ከአራት ወራት በወህኒ ከቆየ በኋላ ለሃገሩና ለወገኑ በደግነት፣ በታታሪነትና በጨዋነት መንፈስ ለኢትዮጵያ እንዳልሠራ፤ በኢትዮጵያ ሰዎች መካከል በባይተዋርነት ኖሮ ያለፈ ሰው ነው…. ጓድ ስለሺ መንገሻ›› ብለውኛል፤ ይህን ጽሑፍ ለመከተብ ከመነሳቴ በፊት በስልክ ያነጋገርኳቸው በደርግ የአስተዳደር ዘመን በምክትል ሚኒስቴር ማዕረግ የፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ እና በሙያቸውም ዕውቅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ጓድ ፋሲካ ሲደልል፡፡

🔵➡️ አባሪና ልዩ ማስታወሻ፡- ብዙዎቹ የደርግ አባላት ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ በ1983 አጋማሽ ጓድ ገዛኸኝ ወርቄ ከነ ልጁ በሰሜን ጎንደር ራሱን ሰውቷል፡፡ ‹‹እሱ (ገዛኸኝ) አቶ አሰፋ ጫቦ እንዳሉት (ነፍሳቸውን ይማረውና) ‹‹በቆመለት ዓላማ መሠረት ለኢትዮጵያ አንድነት ክብርና ነፃነት የመጨረሻውን ጽዋ ነው…›› የተጎነጨው፡፡ ሌላው የደርግ አባል ጓድ ዓሊ ሙሣ እራሱን ያጠፋ መሆኑም የሚታወቅ ነው።
👉 በዚህ እየተገባደደ ባለው ዓመትም ስለሺ መንገሻ፣ ኮሎኔል አሸብር አማረ እና ስመ መልካሙ ንጥር አብዮተኛና የምሕንድስና ሙያ ጠበቢ ጓድ ካሣ ገብሬ ከዚህ ዓለም አጠቃላይ ድካም አርፈዋል፡፡ ባለፉት ዓመታትም እነ ጓድ ደበላ ዲንሣ፣ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ፍስሐ ደስታን ጨምሮ ሌሎችም በተፈጥሮ የመኖር አለመኖር ሕግ መሠረት ወደማይቀርበት ሥፍራ ሄደዋል፡፡ ጓድ ተካ ቱሉ እና ካሣዬ አራጋው በወህኒ ቤት ሕይወታቸው አልፏል፡፡....

👉 ዛሬ ማለትም.. ይህ ጽሑፍ እየተረቀቀ በላበት ጊዜ (በ12/9/2018) ከደርግ አባላት መካከል እነ ማን በሕይወት ቀሩ?... ለሚለው የሚከተለው መልስ ነው፡፡ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ጄነራል አዲስ ተድላ፣ ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኝ፣ የመቶ አለቃ ግርማ አድማሱ፣ የመቶ አለቃ በጋሻው አታላይ፣ ማስተር ቴክኒሺያን ገሠሠ ወልደኪዳን፣ ጓድ ውብሸት ደሴ፣ የመቶ አለቃ በጋሻው ጉርሜሣ…አሉ፡፡ ክቡራንና ክቡራት የግዮን መጽሔት ታዳሚያንና ሌሎችንም አንባቢ ኢትዮጵያውያንን ያሰንብትልኝ!

#@ N.B፦ እንደተለመደው ዘወትር ፎቶዎችን በማሳመር ቀና ትብብሩን ያልነፈገኝን ብሩክ ታደሠን ዘ ባሕር ኃይል ከልቤ አመሰግኜዋለሁ።

ሻለቃ አለማየሁ ቶላሻለቃ ጫላ ወርዶፋከሁአሠ አዲስ አበባ
06/01/2026

ሻለቃ አለማየሁ ቶላ
ሻለቃ ጫላ ወርዶፋ
ከሁአሠ
አዲስ አበባ

ሠሎሞን ለማ ገመቹ ሻምበል ሰለሞን ጋዲሳአዲስ አበባ
06/01/2026

ሠሎሞን ለማ ገመቹ
ሻምበል ሰለሞን ጋዲሳ
አዲስ አበባ

ኧረ ጎንደር ጎንደር....   እንደምድን ነሽ ከነ  ብዙ ፍቅርሽ - ከነ ትዝታሽ....👉 ሠላሳ ሰባት ዓመታት ነጎዱ።  በስሜን ጎንደር የ603ኛ ኮር አዛዣችን ጀነራል ኃይሉ በረዋቅ ነበሩ። 👉...
05/30/2026

ኧረ ጎንደር ጎንደር.... እንደምድን ነሽ
ከነ ብዙ ፍቅርሽ - ከነ ትዝታሽ....

👉 ሠላሳ ሰባት ዓመታት ነጎዱ። በስሜን ጎንደር የ603ኛ ኮር አዛዣችን ጀነራል ኃይሉ በረዋቅ ነበሩ።

👉 በሐምሌ ወር 1981 ገንጣይ አስገንጣይ ወንበዴዎችን የመደምሰስ ኢትዮጵያዊ ዘመቻ ነበረብን። የዘመቻው ስም "ዓድዋ ጥረግ...! " ይባል ነበር።

👉 በዚያ ዘመቻ በዳንሻና በአቅራቢያው ነበሩ የውጊያ ቦታዎች ብዙዎች ተሰውተዋል። በካዛ እየሱስና ዙሪያ ገባው ጥቂት የማይባሉ የእናት ኢትዮጵያ ውድ! ልጆች ወድቀዋል። በአንገረብ ወንዝ የተወሰዱም ነበሩ።

👉 ከራሺያ እንደመጡ በዳንሻ ዘመቻ ተሳታፊ የነበሩት ሻምበል አስማረ ኃይማኖት (ከመገናኛ ክፍል) "አይ የኛ ነገር ከራሺያ ዳንሻ"... ሆነ እያሉ በሕይወት ገጠመኛቸው ይሳለቁ እንደነበር አስታውሳለሁ።..........

👉 እንዲያም ሆኖ በዚያ ዘመቻ!... ከሰኔ እስከ ሐምሌ ወር በነበረው ጊዜ.... (1981 ዓ.ም) የማይረሱኝ እነ ኮሎኔል በቀለ ኃይሌ (ነፍስ ይማር) እነ ኮሎኔል ብርሃኑ ሸንቁጤ፣ ፍፁም ዝምተኛ.... የነበረው ሻለቃ አስፋው ሮባ ፣ ዳንሻ ላይ ራሱን ያጠፋው የመቶ አለቃ መኩሪያ ማኔ ከ603ኛ ኮር ዘመቻ መምሪያ ናቸው።

👉 እነ ሻምበል ጌታቸው ፣ እነ መቶ አለቃ መርጊያ ጪብሳ፣ በእኔ ምትክ መገናኛ ሻለቃን ወክሎ ወደ ዳንሻ ቀዳሚ መምሪያ የሄደው ምክትል የአሥር አለቃ ንጉሤ ("ኢንሹ") የመቶ አለቃ ሠይፉ ዓለማየሁ፣ ሻለቃ ሲሳይ ደስታ (ነፍስ ይማር)... አስተዋዩና ባለማተቡ የጦር መኮንን ኮሎኔል ደበበ.... ኮር መሐንዲስ መምሪያ ኃላፊ የነበሩ። ኮሎኔል አሰፋ ወርቄ (ነፍስ ይማር) ፣ ሻለቃ ዳባ መልካ ቆፍጣናው አዋጊ ተዋጊ ድንቅ የጦር ባለሙያ እና ሌሎችም ከማስታውሳቸው መካከል ይገኙበታል....

👉 ከፍ ሲል ላስቀመጥኩት ትዝታ አዘል.... ሐሣብ መነሻ ምንጮቹ ፤ የማከብራቸው የጀነራል ኃይሉ በረዋቅ እና በወርሃ ሐምሌ 1981 ዓ.ም በዳንሻ ግንባር የመታሰቢያ ምስላቸውን... ያስቀሩት፤ የመቶ አለቃዎቹ የእነ ወርቅነህ ፈጠነ፣ ተገኔ አበበ ፣ መኩሪያ ማኔ ፎቶግራፎች ናቸው።

🔵
💚💛❤
ክረምቱ ሲዳምን - መጣሁ መጣሁ ሲል
ትውስታሽ በአዕምርዬ - ደርሶ ሲያቃጭል

ይታየኛል ስሜን - የዳባት ሜዳው
ሠላሳ አርባ ዓመታት - አልፎ ያልጋረደው

ጎንደር እንደምን ነሽ? - ከነ ትዝታሽ
ምንግዜም ጠዋት ማታ - የማልዘነጋሽ።
🔵
💚💛❤

N.B፦ የጀነራል ኃይሉ በረዋቅን እና የእነ የእነ መቶ አለቃ ወርቅነህ ፈጠነን የመታሰቢያ ፎተግራፍ ያሳመረልኝን ብሩክ ታደሠ ዘ ባሕር ኃይል ወ አሜሪካን ከልቤ አመሰግናለሁ።
መረጃዬ እንዳይዛባ ያገዙኝ ሻለቃ ዳባ መልካ እና የመቶ አለቃ ወርቅነህ ፈጠነም ምስጋናዬ ባላችሁበት ይድረሳችሁ። የመቶ አለቃ ተገኔ አበበ የት ነው ያለኸው??? ጀግናው እና ልበ-ቆራጡ ወጣት ኢትዮጵያዊ መኮንን መኩሪያ ማኔ (ከ603ኛ ኮር ዘመቻ መምሪያ) መቼም ቢሆን አስታውስሃለሁ። ዳንሻ ላይ እንደምን የቴዎድሮስን ጽዋ እንደተጎነጨህ ከቶውንም ሊዘነጋኝ አይችልም። አንተ የዕማማ ኢትዮጵያ ውድ!!! ልጅ።
ጀነራል ኃይሉ በረዋቅ ባሉበት ሃገረ እንግሊዝ እግዚአብሔር ጤናዎን እና ዕድሜውን ይባርክ!!!💚💛❤
ሠሎሞን ለማ ገመቹ

ጓድ!!!መንግሥቱ ኃይለማርያም ወልዴ!አሁን ላይ (ዘንድሮ) 85ኛ  ዕድሜያቸው ላይ ናቸው።ወደ ሥልጣን ሲመጡ....(በወርሃ  የካቲት  1966 ዓ.ም)የሠላ ሦስት ዕድሜ ባለቤት ነበሩ።33 + 1...
05/27/2026

ጓድ!!!መንግሥቱ ኃይለማርያም ወልዴ!
አሁን ላይ (ዘንድሮ) 85ኛ ዕድሜያቸው ላይ ናቸው።

ወደ ሥልጣን ሲመጡ....
(በወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም)
የሠላ ሦስት ዕድሜ ባለቤት ነበሩ።

33 + 17 = 50 ዓመታት።
85 - 50 = 35 ዓመታት።
33 - 18 = 15 ዓመታት።

➡️ 18ቱ የልጅነትና የልጅ ወታደርነታቸው ዕድሜ ነበር።
➡️ 15ቱ ኢትዮጵያን በውትድርና ሙያ ያገለገሉበት ጊዜ ነበረ።
➡️35ቱ ያው የስደት እና የብቸኝነት ዓለማቸው ዘመን ውስጥ የሚካተት ይሆናል።

🔵👉17ቱ ግን.... ባለ ብዙ መልክ ነው።
የሕይወታቸው ዘመን ሁሉ!!!... ሠነድ የታጀለበት ሰንዱቅ መከርቸሚያ መክፈቻ ቁልፍ የታተመበት ነው።

🔵👉 አሁን መንግሥቱ ኖረውም ፣ ነገ አልፈውም... ምናልባትም "የዓለም ፍፃሜው" የሚባለው ቀን እስኪከሰት... ድረስ፤ ከ17ቱ ዓመታት የሚለይ መጥፎም ይሁን መልካም... የሚባል ግን ሊረሳ እና ላይወሳ የሚችል አንድም ታሪክ የላቸውም።

🔵👉 ሌሎቹ የነበሩና ከሥልጣን በተገፈተሩባቸው ማግሥት የነበሩት ዓመታት ...
የጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ተከታይና መሠረተ ዕድሜ... ዓመታት ናቸው።

🔵👉 በአጭሩ! እጅግ በአጭሩ ዕድሜና ታሪክ እንዲህ እና - እንዲህ ነው።
ከሃገር ከሕዝብና ከአብዮት ብሎም ከሥልጣን እና ከሁሉን አድራጊ-ፈጣሪነት ከዝናና ከጭብጨባ ተቀባይነት ዘመን ወይም ወቅት ጋር ብቻ ተቀንብቦ ይሾፈተራል።

🔵👉 እእእ.... ማለቴ ይከለማል፣ ይታያል ማለቴ ነው። ከሰማንያ አምስት ዓመታት አሥራ ሰባቱ ዓመታት በአንድ ሰው ዕድሜ ውስጥ ምን ያህል ግዙፍ ነው?
ሠሎሞን ለማ ገመቹ

ግንቦት13 1983 ዓ/ም  ኮ/ል መንግስቱ ኃማርያም-- ባለ መልካም ስብዕናው የኢትዮጵያ ሰራዊት--አውቶብስ ተራ ✍️✍️✍️በዕለቱ የጠዋቱን ስራችንን አከናውነን እኔ ሹልኬ ምግብ ቤት  በ1 ብ...
05/22/2026

ግንቦት13 1983 ዓ/ም ኮ/ል መንግስቱ ኃማርያም-- ባለ መልካም ስብዕናው የኢትዮጵያ ሰራዊት--አውቶብስ ተራ
✍️✍️✍️
በዕለቱ የጠዋቱን ስራችንን አከናውነን እኔ ሹልኬ ምግብ ቤት በ1 ብር ሹሮዬን በልቼ ከሎንችናው የሗላ ወንበር አረፍ እንዳልኩ ከአጎናፍር ሆቴል ጋሽዬ ከ 2 ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በር አንኳኩ… ያለ ሰዓታቸው።
✍️
ሹልኬ ከትልቁ መናኻሪያ አጥር መጨረሻ ገባ ብሎ በሁለት ጠባብ ግድግዳዎች ተሾልኮ የሚገባበት ሽሮ ከፈለከው ቃሪያ ጋር እና ቀዝቃዛ ውሃ በኒኬል የሚቀርብበት አሪፍ ቤት ነበር።

አጎናፍር ሆቴል ደግሞ ኸዚሁ መነኻሪያ ፊት ለፊት የሚገኝ ሲሆን በወቅቱ በሥጋው በተለይም በቅቅሉ እንዲሁም በጠጁ ይታወቃል። በተጨማሪም ከረንቡላ ወዳጆችም ያዘወትሩታል።
✍️
ያለ ሰዐታቸው መምጣታቸው ግር ብሎኝ በር ከፈትኩና ወደ ወንበሬ ስመለስ
“…ሰማህ አንተ ልጅ…” አሉኝ
“..አቤት ጋሽዬ..”
“..ሰውዬው ከዳን…”
“..ማን ነው..”
“.. መንግስቱ ኃ/ማርያም ጥሎን ወጣ..”…
የመድሃኒያለም ያለህ❗️
✍️
ጋሽዬ የአሽከርካሪ ወንበር ላይ, ጓደኞቻቸው አንዱ ሞተር ላይ አንደኛው ጋቢና ሆነው ብዙም የማይሰማኝ ጭውውት ይዘው ከቆዩ በሗላ ተመልሰው ለመሄድ እየተዘጋጁ አንተ ልጅ ምሳ በልተሃል ሲሉኝ መብላቴን ገልጬ ወደ ሗላ ወንበሬ ተመለስኩ።
✍️
የፕሬዝዳንቱ መውጣት ከተሰማ ከሰዓታት በሗላ አምቦ የነበረው ሰራዊታችን በሁለት ረድፍ ከመሰላሚያ አቅጣጫ አውቶብስ ተራ ደረሰ።
ይህ ሰራዊት ከቀናት በሗላ የራሴ የሚለው ነገር እንደማይኖር አያወቀ፤ በበረኸኞቹ ምን ሊያደርሱባቸው እንደሚችሉ ባላወቁበት ሁኔታ ፤ ነገር ግን ባላቸው የፀና ኢትዮጵያዊነትና ከዚህም በመነጨ ከፍ ያለ ሞራል ከፍ ያለ ንግድ የሚከወንበትን አውቶብስ ተራን እና መርካቶን በሚገርም .....በሚገርም... እና ታሪክ ሲያስታውሰውና ሲዘክረው በሚኖር መልካም ስነ- ምግባር አምስት ሳንቲም ሳያነሳ አለፈ❗️...አምስት ሳንቲም ❗️
✍️
ያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የቆመ ሰራዊትን ለረጅም ጉንቦት 20ዎች “.. የደርግ ሰራዊት “ እያሉ በETV ይዘባበቱበት ነበር።
✍️✍️✍️
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ ሰራዊት ❤️
ከሠላምታ ጋር
✒️
ሀብታሙ ሽፈራው

05/09/2026

መሪ ድምፃዊት : የሃገር ፍቅር ስሜት ዓርማ መገለጫ : ሃረር ያበቀላት የኪነጥበብ ፈርጥ : በክብር ዘበኛ ጠቅላይ መምርያ ሬዲዬ ጣቢያ ክፍል በኃለኛው የ4ተኛው የአብዮታዊ ሠራዊት ሙዚቀኛ ሻለቃ ክፍል በ1949 ዓ/ም በድምፃዊነትና ተወዛዋዥነት የሙዚቃ ስራዋን የጀመረችው ተወዳጇ አንጋፋዋ ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ ሙሉ የህይወት ዘመኗን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት የሰጠች የሃገር ኩራት አርቲስት ነች።
Qemant

💚💛❤ጀግኖቹ! ጀግና አባታቸውን እና አለቃቸውን አክብረዋል!!                           💚💛❤ሠሎሞን ለማ ገመቹ 🔵➡️ በወታደራዊ ጀግንነት እና በእናት ሃገር ፍቅር የቀረጹአቸው...
05/07/2026

💚💛❤
ጀግኖቹ! ጀግና አባታቸውን እና አለቃቸውን አክብረዋል!!
💚💛❤
ሠሎሞን ለማ ገመቹ
🔵➡️ በወታደራዊ ጀግንነት እና በእናት ሃገር ፍቅር የቀረጹአቸውን ታላቅና ዕውቅ የጦር ሰው በሸለሙት፣ በአከበሩት.... ጀግኖች ዝግጅት ላይ መታደሜን በተመለከተ ያቀረብኩት ዘገባ ዝርዝር የሚከተለው ነው፡-
👇
👉🔵 በ1969 ዓ.ም የሶማሊያን ወራሪ ሠራዊት በመደምሰስ፣ ሠርጎ-ገብ ኃይሎችን በመመንጠርና ልካቸውን በማሳየት… እንዲሁም ወደ ሰሜን ኤርትራ ክፍለ ሃገር ዘምቶ ገንጣዩን የሻዕቢያ ወንበዴ ቡድን በመፋለም... ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን ያስመሰከሩት የጀግኖች መፍለቂያ የሆነው የሦስተኛው ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ አባላት፤ ማክሰኞ ሚያዚያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም እጅግ በሚያስደስት ሁናቴ ጀግናና የጀግኖችም ቀራፂ የሆኑትን አለቃቸውን ኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌን በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ለእሳቸውና ለውድ ባለቤታቸው ወይዘሮ አልጋነሽ ከበደ፤ እንዲሁም ለልጆቻቸው እና ለመላው ቤተሰባቸው ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡

👉🔵 በ2011 ዓ.ም የተመሰረተውን የሦስተኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ ባልደረቦች፤ የመረዳጃ ዕድርና የጀግና ወንድማማቾች ማኅበር አባላትን በመወከል ፤ ጀግናውን ኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌን ለመጎብኘት፣ ጀግኒት ባለቤታቸውን ወይዘሮ አልጋነሽን የአክብሮት መግለጫ የሆነውን ካባ ለማልበስ፤ በማኅበራቸው ዋና ተወካይ በሃምሣ አለቃ አሰፋ ተፈራ አስተባባሪነት በመኖሪያ ቤታቸው የተገኙት፡-
👇
🔵➡️ ሻምበል ኃይሉ ተሾመ፣ ሻምበል ጌቱ ታደሠ፣ የመቶ አለቃ ከለለኝ ተክለማርያም፣ የመቶ አለቃ ይሄይስ ደምሴ፣ የመቶ አለቃ ፋሲል ወርቅነህ፣ የመቶ አለቃ ስዩም ለማ፣ የመቶ አለቃ ተስፋለም ገብረሕይወት፣ የመቶ አለቃ ክፍሉ ደምሴ፣ የመቶ አለቃ እሸቱ አበበ፣ የመቶ አለቃ ኤርሚያስ ሀብተማርያም፣ ባሻ አብዲሣ አማን፣ ሻምበል ባሻ ተስፋዬ ሀብተወልድ፣ መጋቢ የሃምሣ አለቃ ነጋሽ ስራኔ፣ የአሥር አለቃ ጌታቸው ማሞ፣ የአሥር አለቃ ወስይሁን ጸጋዬ፣ የአሥር አለቃ ግርማ መኩሪያ፣ ወታደር በቀለ ኡርጌሣና ሌሎችም ናቸው፡፡

🔵➡️ ከ3ኛ ፓራ ብርጌድ ማኅበር ተወካይ አባላት በተጨማሪ፤ ኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌን እና ባለቤታቸውን ወይዘሮ አልጋነሽ ከበደን በመጎብኘቱ፣ ይገባቸዋል የተባለውን ስጦታ በማበርከቱ፣ እንዲሁም የአክብሮት ካባውን በማልበሱ ደማቅ የነበረ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር ዕንግድነት፤ የሁለተኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ እና የጀግናው ሦስተኛ አንበሳ ክፍለ ጦር ባልደረቦች የሆኑት ኮሎኔል ተሾመ በላቸው እና ሻምበል ወርቅነህ ታደሠ ተገኝተዋል፡፡

👉 🔵 በዕለቱ በዕንግድነት ከመገኘታቸው ባለፈ ለኮሎኔል ዘመዱና ለባለቤታቸው ለወይዘሮ አልጋነሽ የክብር ካባውን ያለበሷቸው ኮሎኔል ተሾመ በላቸው በሰዓቱ ባደረጉት ንግግር፡- እሳቸው ኢትዮጵያ በሰይድ ባሬ ዕብሪተኛ ሠራዊት የምሥራቅና የደቡብ ሰፊ ግዛቷ በተወረረበት ወቅት የ2ኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ ባልደረባ ሆነው ከጦር ጓዶቻቸው ጋር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለእናት ሃገር አንድነትና ነፃነት መክፈላቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡
👉 🔵 እንዲሁም.... እንደ ኮሎኔል ዘመዴ ኃይሌ ሁሉ፤ የ2ኛ ፓራ-ኮማንዶ አባላት ኮሎኔል ሽባባው ዘለቀን የመሰለ ቁርጠኛና ጀግና! በጦር ሜዳ የተሰዋ!.... ግን ስሙ ሕያው ሆኖ የሚኖር የሚያኮራ የጦር አዛዥ እንደነበራቸውም አስታውሰዋል፡፡ ሲያክሉም:-
👇
🔵➡️ ‹‹የኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌና ይመሩት የነበረው የሦስተኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ ሠራዊት መከበርም፤ ኮሎኔል ሽባባው ዘለቀ እና በእሳቸው አዝማችነትና አዋጊነት ሥር የነበረው የ2ኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ አባላት እንዲሁም የ1ኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ ጀግኖች ስም መከበርም ጭምር ነው›› ብለዋል፡፡

➡️🔵👉 እንደ ኮሎኔል ተሾመ ሁሉ በዕንግድነት የተገኙትና የአንበሣው ሦስተኛ ክፍለ ጦር ባልደረባ የነበሩት ሻምበል ወርቅነህ ታደሠም በበኩላቸው፡-
🔵➡️ ‹‹የሦስተኛ ፓራ-ኮማንዶ ብርጌድ አባላትም ይሁኑ ከ1969 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በምሥራቅም ይሁን በደቡብና በሰሜን… ለእናት ኢትዮጵያ ሕዝብና የግዛት አንድነት፣ ለነፃነቷና ለክብሯ ሲሉ! እጅግ ወደር-የለሽ መስዋዕትነት የከፈሉት ልጆቿ፤ በተከታታዩ ትውልድ ታሪክ ውስጥ እንደ ኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌ ሁሉ፤ ስምና ተግባራቸው በመልካምነት ሲነሳ የሚኖር ነው…›› ብለዋል፡፡

🔵👉 👉 ሦስተኛ ፓራ-ኮማንዶዎችን በመወከል ንግግር ያደረጉት የሃምሣ አለቃ አሰፋ ተፈራም፡-
👉 ‹‹ከአፍላ ወጣትነት ዕድሜያችን ጀምሮ ከአባታችን፣ ከአስተማሪያችን፣ እጅግ ከምንኮራባቸው ጀግና አዛዣችን ከኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌ ጋር በመሆን በተለይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት! በተለይም በመላው ኦጋዴን አውራጃ በመዘዋወር፣ ከሥፍራ ሥፍራ ለውጊያ በመንቀሳቀስ፣ በላቀ የእናት ሃገር ፍቅር ስሜት በመፋለም… ለኢትዮጵያ ክብር! ነፃነትና አንድነት ስንል በከፈልነው መስዋዕትነት፤ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም እንኮራለን፡፡ አባታችንንና ጀግናው አለቃችንን ኮሎኔን ዘመዱን ዘወትር የምናከብረውና በፍቅር የምንመለከተውም፤ በጦር ሜዳ ከአጠገባችን የወደቁ ጓዶቻችንን ለደቂቃዎች የማንዘነጋቸው መሆኑን ለየራሳችን የገባነውን ቃል-ኪዳን በማሰብ ነው…›› የሚለውን ቃል አሰምተዋል፡፡

🔵➡️💚💛❤ 🔵➡️ ትላንት በቆራጥነት እና በላቀ የጀግንነት ስሜት ሲመሯቸው በነበሩት … ወታደሮቻቸው ፊት አንድ አፍታ ቆም በማለት፤ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አልጋነሽ ከበደ ጋር የምስጋና እና የምርቃት ድምፃቸውን ያሰሙት ጀግናው ኢትዮጵያዊ አዛውንት ኮሎኔል ዘመዱ ኃይሌም በንግግራቸው ማሳረጊያ ፡-
👇
👉🔵➡️ ‹‹እኔ ለዚህ ክብርና ሞገስ፣ የመልካም ስምና ተግባር ባለቤት ለመሆን የበቃሁት… ያኔ ከፊት ለፊቴ ማንኛውንም ዓይነት ግዳጅ ለመወጣት በልዩ ወታደራዊ ንቃት ከፊት ለፊቴ በቆሙት፣ በአስደናቂ የቆራጥነት ስሜት የኢትዮጵያን ጠላቶች ይፋለሙ በነበሩት… ጀግናዎቹ ልጆቼ የሕይወት፣ የደምና የአካል… መስዋዕትነት ነው!

👉 "ዛሬም እነዚሁ ልጆቼ ከአጠገቤ ሳይለዩ ስሜን ሲጠሩና ከነቤተሰቦቼ ሲያከብሩኝ ስመለከት የሚሰማኝ ደስታ ወደር-የሌለው ከመሆኑም በላይ፤ ለእንዲህ ዓይነቱ አስደሳች ሁናቴ የተመረጥኩ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ እግዚአብሔርን ከልቤ የማሰመሰግንበት ነው…›› ብለዋል፡፡

Address

Dallas, TX
75287

Opening Hours

Monday 9am - 5pm
Tuesday 9am - 5pm
Wednesday 9am - 5pm
Thursday 9am - 5pm
Friday 9am - 5pm
Saturday 9am - 5pm
Sunday 12pm - 6pm

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት:

Featured

Share