05/09/2026
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።
በጉብኝቱ ከርእሰ መሥተዳድሩ በተጨማሪ የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል። ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ ታሪክን ከዘመናዊት ጋር አስተባብሮ የተገነባውን የዞብል ፓርክ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ነው በምሽት ያላቸውን ገጽታ ተዘዋውረው የተመለከቱት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ ልዩ ምልክት በኾነው በታሪካዊው የቅዱስ ፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ገባ የተሠራው ፓርክ በአማረ ሁኔታ መልማቱን ተናግረዋል።
ልማቱ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት አንዱ አካል መኾኑን ገልጸዋል። ጎንደር ደግሞ የቱሪዝም ከተማ በመኾኗ ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ሂደት መኾኑን ነው ያነሱት።
ፓርኩ ለቱሪዝም መዳረሻነት ኾኖ የሚያገለግል፣ ለመዝናኛም የሚኾን ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በጎንደር የኮሪደር ልማት ከፒያሳ ቀጥሎ ትልቁ የመዝናኛ ማዕከል እንደኾነ ነው ያነሱት። አካባቢው ከአሁን በፊት ለጎብኝዎችም ኾነ ለነዋሪዎቹ የተመቸ አልነበረም፤ አሁን ግን ከባሕረ ጥምቀቱ በተጨማሪ ራሱን ችሎ ለጎብኝዎች መዳረሻ ኾኖ እንዲያገለግል ባማረ ሁኔታ ተገንብቷል ብለዋል።
በጎንደር የልማት እንቅስቃሴ የበለጠ እየሰፋ መሄዱን ገልጸዋል። ጎንደር በ2018 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም በክልሉ ከተሞች አንደኛ መውጣቷን ያስታወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በ2019 በጀት ዓመትም የበለጠ መሥራት እንዲቻል ያለመ ጉብኝት እንዳደረጉ አንስተዋል። በተመለከቱት የልማት ሥራ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ገልጸዋል።
ከአማራ ኮሙኒኬሽን