24/08/2026
የተንሸዋረረዉ የዶር በለጠ ምላ እይታ
የዶክተር በለጠ ሞላ መልእክት የአንድን ወገን ቅሬታ ብቻ ነጥሎ በማንሳት የተሟላ እውነታን የማያንጸባርቅና ሚዛናዊነት የጎደለው አቀራረብ ይታይበታል። ሕዝቦች በሙሉ ክብርና እኩልነት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው መርህ የማይሸራረፍ ቢሆንም፣ የትችቱ አቅጣጫ ግን በአንድ ወገን ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ ተገኝቷል።
የአማራ ሕዝብ ክብር ሊጠበቅ ይገባል የሚለው ሀሳብ ትክክል ቢሆንም፣ በአማራ ኤሊቶችና አብንን ጨምሮ የአማራን ሕዝብ እንወክላለን በሚሉ አካላት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በየዕለቱ የሚሰነዘሩትን አዋራጅ ስድቦች፣ ማንኳሰሶችና የፖለቲካ ጥቃቶች ችላ ብሎ ማለፉ ትክክለኛ ፍትሐዊነትን አያሳይም።
የኦሮሞ ሕዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች ፍትሐዊና መሠረታዊ ናቸው። ለፊንፊኔ ታሪካዊ ባለቤትነት ዕውቅና እንዲያገኝ መጠየቅ የሌላውን ወገን መብት መጋፋት ሳይሆን፣ ታሪካዊና መዋቅራዊ በደሎችን የማረም ፍላጎት ነው።
ሕዝብና ኤሊቶችን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። አብንን ጨምሮ ያሉ ኤሊቶችና የፖለቲካ ቡድኖች ሕዝብን ሽፋን በማድረግ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ማንነት ለማንኳሰስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሳይኮንኑ፣ ተቃውሞ ሲነሳ ብቻ ሕዝብ ተሰደበ ብሎ ማቅረብ እውነተኛውን ችግር ይሸፍናል።
ዘላቂ ሰላምና መከባበር ሊመጣ የሚችለው የሁሉም ሕዝቦች ብሔራዊ ክብር፣ ማንነትና ፍትሐዊ ጥያቄዎች እኩል ዕውቅና ሲያገኙ ብቻ ነው። የአንድን ወገን ስሜት ብቻ በማንሳት ሌላውን ችላ ማለት ከአንድ ትልቅ የመንግስት ሃላፊ አይጠበቅም፡፡