12/05/2022
ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ቼዝ ውድድር መድረክ፤🇪🇹‼️
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቼዝ ፌደሬሽን አባል የሆነቸው በ1984 ዓ/ም እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ቼዝ ውድድሮች ላይ በወንድም በሴትም ተሳታፊ ሆናለች፡፡ በተሳተፈችባቸው ውድድሮች ላይ ምን ውጤት ተመዘገበ የሚለውን መረጃ ለቼዝ ማህበረሰቡ ማስተላለፍ እውቅና መስጠትም ስለሆነ ይህ አጭር መረጃ ለማዘጋጀት ተሞክሯል፡፡ አንዳንድ የቦታ፤ የቀንና የውጤት መፋለስ ቢኖር ማስተካከል ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ በኦሎምፒያድ መሳተፍ የጀመረችው በ1993 ዓ/ም በ34ኛው ቱርክ ኢስታንቡል ጀምሮ ሲሆን እስካሁን ያልተሳተፈችው የስፔኑን ብቻ ነው፡፡ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በተካሄደው ውድድር ዳዊት ወንድሙ በታሪክ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ በ35ኛው ስሎቪኒያ ብሌድ ከተማ ላይ በተካሄደው ውድድር ወሰንየለው ሀይሉ የነሀስ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስገኝቷል፡፡ እንዲሁም በቡድን 1ኛ በመውጣት ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ጆርጂያ ከተካሄደው እስከ 43ኛው ኦሎምፒያድ ድረስ ሜዳሊያ አልተገኘም፡፡ እንዲሁም በታይትል ደረጃ አዘርባጃን ባኩ ከተማ በተካሄደው ኦሎምፒያድ ለይኩን መስፍን የፊዴ ማስተር ታይትል አግኝቷል፡፡ ጆርጂያ ላይ በተካሄደው ኦሎምፒያድ አይዳኙህም ግዛቸው የፊዴ ማስተር (ያልፀደቀ)፤ በሴቶች መቅደስ ደምሴ ካንዲዴት ማስተር ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በመላው አፍሪካ ጨታዎች ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቼዝ የተሳተፈችው በ1996 ዓ/ም ናይጄሪያ ላይ በተካሄደው ሲሆን ቡድኑ ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡ አልጀሪያ ላይ በተካሄደው ውድድር ብርሀኔ ገ/እግዚአብሄር የነሀስ ሜዳሊያ አስገኝቷል፡፡ በሞዛምቢክና ሞሮኮም ላይ ኢትዮጵያ በቼዝ ተሳታፊ ነበረች፡፡
በአፍሪካ ዞናል ውድድር ኢትዮጵያ መሳተፍ የጀመረችው ግብፅ ላይ በ1990 ዓ/ም በተካሄደው ሲሆን በወቅቱ ከተሳተፉት ሁለት ስፖርተኞች መካከል ይማም አበራ የፊዴ ማስተር ታይትል ማግኘት ችሏል፡፡ ጅቡቲ (2018) ላይ በተካሄደው የዞን 4.2 ውድድር ለይኩን መስፍን እና ፌቨን ገ/መስቀል ለኢትዮጵያ በዞናል ውድድር የመጀመሪያውን የነሀስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የቼዝ ውድድር ያስተናገደችው በ2009 ዓ/ም ጂማ ከተማ ላይ የተካሄደውን የዞን 4.2 ውድድር ነው፡፡ በዚህ ውድድር አይዳኙህም ግዛቸው 5ኛ ደረጃና የፊዴ ማስተር ታይትል (ያልፀደቀ) አግኝቷል፡፡
የዞን 4.2 ወደ ዞን 4.4 ሲለወጥ የመጀመሪያውን ውድድር በዚህ ዓመት 2014 ዓ/ም ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በውጤት የደመቀችበት ነው፡፡ ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ ዝግጅት የተደረገበት፤ ብዙ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት፤ እንዲሁም የፊዴ፤ የአፍሪካና የዞን 4.4 ፕሬዚዳንቶች የተገኙበት ነበር፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዓቀፍ ቼዝ ውድድር መድረክ ወርቅ ያገኘችበት ነው፡፡ በወንዶች ደሳለኝ ፍቃዱ ወርቅ፤ አይዳኙህም ግዛቸው ብር ሲያስገኙ በሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የብር ሜዳሊያ በልደት አባተ፤ አስቴር መላከ ነሀስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስመዝግበዋል፡፡ ይህም ውጤት በዓለም አቀፍ ውድድር መድረክ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በሩጫ ብቻ ሳይሆን በቼዝም ማስመዝገብ እንደምትችል አሳይቷል፡፡ በታይትል ደረጃ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ኢንተርናሽናል ማስተር IM ታይትል ያገኘችበት ውድድር ነው፡፡ ደሳለኝ ፍቃዱና አይዳኙህም ግዛቸው ኢንተርናሽናል ማስተር IM እንዲሁም ሀብታሙ አሸናፊ የፊዴ ማስተር ሲያገኙ በሴቶች ልደት አባተና አስቴር መላከ የፊዴ ማስተር (በተጨማሪም የኢንተርናሽናል ማስተር ኖርም) አግኝተዋል ፡፡ ካንዲዴት ማስተር ታይትል ያገኙ አዲስ ዓለም፤ሀብታሙ ባዩ፤ አክመል፤ ጴጥሮስ፤ ሰላማዊት፤ ሀና፤ የኔነሽ፤ እስራኤል፤ መቅደስ አግኝተዋል፡፡ በቀጣዩ የ2022 የህንድ ኦሎምፒያድ ምን ውጤት ይመዘገብ ይሆን??
ምንጭ፤ ከኢንተርኔትና ከተጫዋቾች፡፡
ፊዴ ኢንስትራክተር ተገኝ መሀድም
Photo;
Slovinia,2002 Men's Team: kneeling (from left to right) are Dawit Wondimu (Bd. 1), Fikreselassie Alemu (Bd. 2), Yimam Abera (Bd. 3); standing (from left to right) Abenet Bekele (Bd. 4), Mekitew Molla (Bd. 5), Wossenyelew Hailu (Bd. 6) and the Team Captain, Tsega Kumlachew. Photo by Jerry Bibuld.