ግረት ቨዥን የበጎ ፈቃደኞች ማህበር (ጂቫ)/ GREAT VISION VOLUNTARIES ASSOCIATION (GVVA) በሚል የተሰየመው የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ማህበር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መጋቢት 21/07/2003 ዓ.ም በዲላ ከተማ በጥቂት ተማሪ ወጣቶች ተመሰረተ፡፡ ይህ ‹‹ግረት ቨዥን›› (GVVA) ተብሎ የተሰየመው ማህበር ስሙ እንደሚያመለክተው በውስጡ ትልቅ ራዕይ ይዞ የተነሳና ሕልናን የሚያረካ ዓላማ ያለው ማህበር ነው፡፡
ይህን ማህበር ለመመስረት ጥቂት በተለያዩ የትምህርት ደረጃ ማለትም ከ1ኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ ትምህርት ተማሪዎች የነበሩና በወቅቱ ምንም ዓይነት የራሳቸው የሆነ ቋሚ ገቢ ባልነበራቸው ነገር ግን ቋሚ ዓላማ
ባላቸው ወጣት ተማሪዎች ባደረጉት ጉልህ እንቅስቃሴ እንደ አንድ ማህበር ተቋቁሟል፡፡
የማህበሩ አላማ
የዚህ ማህበር አላማ ለወደፊት ኢትዮጵያ ዕድገት ጉልህ ሚና የሚኖራቸውና ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር ተጋልጠው የወደፊት ተስፋ ጨልሞባቸው በየጎዳናው ለሚንከራተቱ ሕፃናት የተስፋ ብርሃን ለመፈንጠቅ ቆርጦ የተነሳ ማህበር ሲሆን ማህበሩ አሁን ካለበት ደረጃ አድጎ ራሱን በገቢ ደረጃም ሆነ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያጠናክር በተለያየ ሁኔታ ወላጆቻቸውን ያጡትንና ለመማርም ሆነ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት አቅም አጥተው በየጎዳናው እየተንከራተቱ ለተለያዩ ችግሮች የተዳረጉትን ህፃናት ሰብስቦ ለመርዳትና ለወደፊት ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው ዕድገት የጎላ ተሳትፎ እንድኖራቸው ለማብቃት ታስቦ ይህ ማህበር ተቋቁሟል፡፡
የማህበሩ ራዕይ
ከላይ በዓላማው ለመግለጽ እንደተሞከረው እጅግ መልካምና ህልናን የሚያረካ ዓላማ ይዞ የተነሳውን ይህን ማህበር ለብዙ ኢትዮጵያውያን፣ አፍርካውያንና ለዓለም ሕዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ተምሳሌት ሆኖ ማየት የማህበሩ ዋና ራዕይ ነው፡፡
የማህበሩ ተልዕኮ
የማህበሩ አባላት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተቸገሩትን ሰዎች በግላቸው ከመርዳት ባለፈ ወደተቀናጀ ማህበራዊ አሰራር በማምጣትና ማህበሩን ለአጋር ግለሰቦችና ድርጅቶች ማስተዋወቅ እንድችሉ ማድረግ የማህበሩ ግንባር ቀደም ተልዕኮ ነው፡፡ እንድሁም ደግሞ ግረት ቨዥን የበጎ ፈቃደኞች ማህበር (ጂቫ)/ GREAT VISION VOLUNTARIES ASSOCIATION (GVVA) ትልቅ ዓላማ ይዞ የተነሳና ዓላማውንም ከግብ ለማድረስ በአሁኑ ጊዜ በአፋጣኝ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ታዳጊ ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ ይህንን መሰረት በማድረግ በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን ለዚህ መልካም አላማ መሳካት የድርሻችውን ለመወጣት ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ለማሳተፍ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ይጥራል፡፡ ለዚህም በኢንተርኔትና በተለያዩ ማስታወቂያዎች ማህበሩን ከዓለም ህዝብ ጋር በማስተዋወቅ ማህበሩን ማስፋፋት ለላው የማህበሩ ተልዕኮ ነው፡፡
ግረት ቨዥን የበጎ ፈቃደኞች ማህበር (GVVA) የያዘው ዓላማ ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ደስታንና የህሊና እርካታን ከመለገስ ባለፈ ለብዙ ወላጅ አልባና ለችግር ለተጋጡ ህፃናት ልጆች የመማርና ራሳቸውን የሚችሉበትን እድል በመፍጠር ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት ቆርጦ የተነሳ ማህበር ነው፡፡
ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት በዚህ በጎ አድራጊ ማህበር በአባልነት ለመንቀሳቀስ ለሚፈልግ ሁሉ የማህበሩ መተዳደሪያ ውስጠ-ደንብ በሚፈቅድ መልኩ በራችን ክፍት መሆኑን እየገለጽን ለነገ ኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር የበኩልዎን ድርሻ ለመወጣት ከእኛ ጋር በመተባበር ለወገኖቻችን መልካም ስራ ለመስራት እንነሳ!!!
ለመልካም ነገር እጆቻችንን በዘረጋን ልክ ፈጣሪ ይባርከናል፡፡
ምናልባት በረከቶቻችን የዘገዩብን ለዚሁ ይሆን?
ነጮች የመባረካቸውስ ሚስጥር ይኸው ይሆን?
ወይ ደግሞ ነጮች የሚረዱን ሞልቶ ስለተረፋቸው ነው?
አልያም እኛ ጋር ደግሞ መርዳት የሚንችልበት አንዳችም አቅጣጫ አጥተን ነው? አይደለም!!!
እኛ ጋር ለመልካም ነገሮች ሚዘረጉ እጆች ስላጠሩን ፤
መልካም ነገሮችን የሚመለከቱ ዓይኖች ስላልተከፈቱልን ይመስለናል፡፡ ከዚህ በኃላ ግን ይህን አንድ ላይ ሆነን በGVVA ታሪክ እናደርጋለን!!!
መጋቢት 21 / 2003 ዓ/ም
ዲላ
''የተቸገረን መርዳት የህሊና ግዴታ እንጂ የዜግነት ተልዕኮ አይደለም!!!''
Alerts
Be the first to know and let us send you an email when Great Vision Voluntaries Association - GVVA posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.