13/06/2025
በ2 ሚሊዮን ዶላር ዕድሜን ለማርዘም የሚደረግ ሙከራ
*******
የሰው ልጅ ዕድሜ ቢበዛ መቶ ነው፤ አብዛኛው ሰው 80ና 90ዎቹ ዕድሜ ላይ ደርሼ እንዳማረብኝ ይህችን ዓለም ብሰናበት ብሎም ይመኛል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግም አንዳንዶች እርጅናን ከገታን ረጅም ዓመታትን ልንኖር እንችላለን በሚል የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ምንም እንኳን እስካሁን የተሳካ ሙከራ ባይኖርም ይህንን ማሳካት እችላለሁ ብሎ የተነሳ አንድ ባለሃብት አለ።
ብራየን ጆንሰን ይባላል። ትውልድ እና እድገቱ በአሜሪካ ዩታህ ግዛት ነው። እርጅናን ማዘግየትና ህመሞችን መቀነስ እንዲሁም ከማርጀት ይልቅ ወደ ወጣትነት መሸጋገር ይቻላል ይላል።
ብራየን የሰው ልጅ አፈጣጠር ልክ እንደ ኮምፒዩተር ሶፍትዌር መሻሻል የሚችል ነው ብሎ ያምናል።
''ብሉፕሪንት'' የተሰኘ ፕሮጀክትም በመንደፍ ‘የአላረጅም ፣ አልሞትም’ መንገዱን ተያይዞታል።
ሁሌም በየቀኑ የተለያዩ ቫይታሚኖችን ይውጣል፤ አመጋገቡንም እጅግ በጥንቃቄ የተሞላ ሲሆን፤ ስፖርትም ይሰራል። በተጨማሪም ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነው የሚተኛው።
ከፍተኛ የሕክምና ክትትልም በማድረግም የሰውነቱ እያንዳንዷን ጤንነት ለማወቅ ጥረት ያደርጋል።
የ47 ዓመቱ ሚሊየነር ብራየን ይህም አልበቃ ብሎት በየቀኑ ከአንድ መቶ በላይ የተለያዩ የመድኃኒት እንክብሎችን እየወሰደ ነው።
ሃይፐርባሪክ ኦክሲጅን በተሰኘ ቴራፒ አማካኝነት ዝግ በሆነና ግፊት ባለበት ከባቢ ውስጥ የተጣራ ኦክሲጅን አየር ወደሰውነቱ እያስገባ የተጎዱ ህዋሳቶቹ እንዲሻሻሉ በማድረግ እርጅናን ለመከላከል እየጣረ ነው።
ለ90 ቀናት በየቀኑ ለ1 ሰዓት ተኩል ያህል በዚህ አይነት ሕክምና አፉ ላይ የኦክሲጅን አየር ማስገቢያ አድርጎ ያሳልፋል።
ብራየን ህልሙን ለማሳካት በዓመት 2 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ፤ ይህንን ሁሉ እያደረገ ቢሆንም የግል ሕይወቱ ግን ችግሮች የበዙበት ነው። ከትዳሩ ተፋቷል ፣ ሐይማኖቱንም ትቷል።
ለ5 ዓመታት ይህንን ሙከራ ያደረገው ብራየን ግን ወደወጣትነቴ እየተመለስኩ ነው ይላል።
ዘላለም የመኖር ፍላጎት የብራየን ብቻ አደለም፤ የብዙ ሰዎች ፍላጎት ነዉ።
የብራየን ሕይወት አንድ ጥያቄን እንድናነሳ ይጋብዘናል፤ ሕይወት አጭር መሆኗን አምነን እንቀበል ወይስ ዕድሜያችንን ለማርዘም እንታገል? እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
በቢታንያ ሲሳይ
#እድሜ #እርጅና