09/09/2026
🌼 እንኳን ለ2019 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! 🌻
የተከበራችሁ ዉድ አጋሮቻችና ወዳጆቻችን ፣ መላው የኮሚሽናችን (EMWACDC) መሪዎችና ሠራተኞች ቦርድ አባላት ፣ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮቻችን እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፦
በመጀመሪያ አምላካችን እግዚአብሔር ሁላችንንም በሰላም እና በጤና ጠብቆ ለ2019 ዓመተ ምህረት አዲስ አመት በሰላም ስላደረሰን ስሙ ለዘላለም የተመሰገነ ይሁን !
በድጋሜ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ልማት ኮሚሽን (EMWACDC) ስም እንኳን ለ2019 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሰን እያልኩ ፤ ከልብ የሆነ ሰላምታዬንና መልካም ምኞቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ ።
ያሳለፍነው የ2018 ዓመተ ምህረት በርካታ ስኬቶች ፣ ፍሬያማ ሥራዎችና አስደናቂ ዉጤቶች የተከናወኑበት ፤ ከችግሮች ይልቅ መልካም ዕድሎችን በማየት የተጋንበት እና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በበጎ መልኩ የለወጥንበት አስደናቂ የአገልግሎት ዓመት ነበር።
ለዚህ ትልቅ ስኬት፦
ለአጋሮቻችንና ወዳጆቻችን በሙሉ ፦ ዘላቂ የልማት፣ የሰላም ና የበጎ አድራጎት ሥራዎቻችንን በጋራ እንድናሳካ ላደረጋችሁልን ያልተቆጠበ ድጋፍና አብሮነት የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ለቦርዳችን አባላት ፦ በልማት ኮሚሽናችን ስትራቴጂካዊ አመራርና ጥበብ የተሞላበት አቅጣጫ በመስጠት ላበረከታችሁት የላቀ አስተዋጽኦ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ለልማት ኮሚሽኑ ሠራተኞች (ስታፎች) ና የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች፦ በታታሪነት፣ በታማኝነትና በፍቅር ሕዝባችንን በማገልገል ላሳያችሁት ቁርጠኝነት፣ መሰጠትና ትጋት ያለኝን አድናቆት ከምስጋና ጋር መግለጽ እወዳለሁ። እናንተ የኮሚሽናችን የጀርባ አጥንት እና የእውነተኛ ለውጥ አምባሳደሮቻችን ናችሁ!።
እንዲሁ ይህ የ2019 አዲሱ ዓመት ለልማት ኮሚሽናችን እጅግ ልዩና ታሪካዊ ነው ብለን እናምናለን ምክንያቱም
በዚህ ዓመት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትከ2019 _ 2023 ዓ.ም (ከ2026 - 2030 ) የልማት ኮሚሽናችን ወደ ላቀ የአገልግሎትና የልማት ምዕራፍ የሚሸጋገርበትን የ5 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ (Strategic Plan) ሥራ ላይ ማዋል የምንጀምርበት አመት ስለሆነ ነው።
ይህንን ታላቅና መልካም ተግባር በላቀ ውጤታማነት ለመፈጸም እና የማኅበረሰባችንን ሕይወት ይበልጥ ወደ ተሻለና ከፍ ያለ ደረጃ ለማድረስ እና ለመለወጥ፤ ሁላችንም ከተለመደው የእለት ተእለት ተግባር ባሻገር ፤ በትጋት፣ በኅብረትና በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንድንቀሳቀስ የከበረ ጥሪዬን ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ ።
2019 ዓመተ ምህረት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት የእድገትና የብልፅግና ፤
ለልማት ኮሚሽናችን ደግሞ የታላቅ በረከት፣ የስኬትና የበዛ የፍሬአማ ዓመት ይሁንልን!
መልካም አዲስ ዓመት!