Semayawi Thought

Semayawi Thought Equipping Ethiopian Christians to renew their minds through this media, serve the church and create culture to the glory of God
(1)

Semayawi Thought is a nonprofit online magazine published in Amharic and English both, a platform for Ethiopian Evangelical Christians Professionals and for those who are attracted in Semayawi (heavenly) thoughts. Our online magazine is much more than a blog, which is simply a chronological list of posts focused on publishing different types of spiritual contents and devoted to personal and spirit

ual growth. Together as a community, we will experience the fullness of life, grow spiritually and personally. For those of you who have been wishing to read and write your deepest reflections and ideas for Ethiopian Churches, Semayawi Thought will provide you opportunities. On Semayawi Thought, we issue a spiritual perspective on world events as well as tools for your spiritual practice, all based on Bible. Filled with convenient as well as inspirational content, hoping it will change your life. And don't miss our ever-expanding line of bringing quality contents to Ethiopian Christians!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቸገረህ ያለው ብትሉኝ አቋም በሚፈልጉ ግልጽ ጉዳዮች ላይ ሆነ ብለው አቋም ላለመያዝ አቋም የያዙ ሰዎች! እጃቸውን ዘርግተው ማትጨብጧቸው Ghost የሆኑ፤ መስመር የሌላቸ...
21/04/2026

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቸገረህ ያለው ብትሉኝ አቋም በሚፈልጉ ግልጽ ጉዳዮች ላይ ሆነ ብለው አቋም ላለመያዝ አቋም የያዙ ሰዎች! እጃቸውን ዘርግተው ማትጨብጧቸው Ghost የሆኑ፤ መስመር የሌላቸው ሰዎች አሉ።

ከቅርብ ጊዜ የመጣው አዲሱ ስትራቴጂ፤ አቋም ሳይይዙ መንሳፈፍ ነው። ለምን? ሁሉም ቤት ጣሪያ ላይ ማረፍ ያስችላል። ለዛ አዋጭ ነው። A ም ነኝ ደግሞም Z ም ነኝ። ከዚህ ከ A ጋር ፀብ የለም ከ Z ም ጋር ፀብ የለም፤ የሁሉም ወዳጅ ሆናችሁ መሄድ ከፈለጋችሁ፤ መንገዱ ውስብስብ አይደለም፤ አቋም አይኑራችሁ። በሁሉም ቤት አባወራ ላይ ዘፍ የሚል አሞራ ነው ምትሆኑት።

መንፈሳዊ ብስለት ወንድሞቼ እህቶቼ፤ ተንሳፋፊ አያደርግም። በዶክትሪን ግንባታ ውስጥ አልፎ ማደግ አቋም የለሽ አማኝ አያደርግም። ተፍገምጋሚ ተንገዋላይ አያደርግም። እንደዛ የሚያደርግም አስተምህሮአዊ ምክር ቅዱሳት መጻሕፍት የላቸውም። የእግዚአብሔር ቃል ምክር የሐዋርያት ትምህርት እርስ በእርስ ፈጽሞ የማይጣጣሙ የተቃረኑ ስድስት እና ሰባት አቋሞች ውስጥ እንዲሁ እየፈሰሳችሁ እንድትሄዱ የሚፈቅድ ምክር የላቸውም። ጤናማ ዶክትሪን እንደ መልህቅ ይይዛል። አንዴ ወደ ፊት አንዴ ወደ ኋላ አያስኬድም። ወዲያና ወዲህ አቅጣጫ የለም! ፖዚሽን የለም! ግራውንድ የለም! እንደሱ የሚያደርግ የአስተምህሮ አቀራረጽ የለም። ጤናማ ዶክትሪን እንደዚህ አያደርግም።

በአስተምህሮ መሬት የረገጠ ሰው ጽኑ ነው። ሀሰት ከየትም ይምጣ ከየትም አያፍገመግመውም። ከሁሉም ጋር ጎረቤት አይደለም! ቢቻላችሁ ነው ከሰው ጋር በሰላም ኑሩ የተባለው ስለማይቻል ነው። ከቻላችሁ ጥሩ፤ ግን አይቻልም። ሐዋርያትን ወንጌል ከሁሉም ሰው ጋር ሲያወዳጃቸው አናይም ። ዘመዳቸው ከቃሉ ጋር ዘመድ የሆነ ሰው ነው። ከቃሉ ጋር በግልጽ ጠብ የወጣን ሰው ጎረቤት የሚያደርግ አስተምህሮ ቀረጻ ብሎ ታሪክ የለም። ለምን የሰማይ ስባሪ አያክሉም። ከመላእክት ጋር ቡና እየጠጡ የሚወርዱ ሰዎች ለምን አይሆኑም! እሚፍገመገሙ ከሆነ ተንሳፋፊዎች ናቸው! ተጠበቋቸው። ጤናማውን አስተምህሮ፤ ከሀሰት ትምህርት ለይቶ ማወቅ የመንፈሳዊ ብስለት ምልክት ነው። በእግዚአብሔር ቃል ተኮትኩቶ የማደግ ምልክት ነው።ይሄ ሀሰት ነው! ይሄ እውነት ነው ማለት። ይሄ ጨለማ ነው ይሄ ብርሃን ነው ማለት። ሰኞን ሰኞ እንደምንል፤ ማክሰኞንም ማክሰኞ እንደምንል፤ አንዳንዱን ትምህርት አንዳንዱን እንቅስቃሴ አንዳንዱን ጎራ፤ አንዳንዱን ስብስብ ይሄ ከሰይጣን ነው፤ ይሄ ከክርስቶስ ነው ማለት ይጠበቅብናል።

ስለዚህ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንግዲህ ህጻናት መሆን አይገባም። ይሄ የሐዋርያው የጳውሎስ ምክር፤ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ፤ ከዘመናት በኋላ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ጠቅሟት ነው ያየነው።

ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐዋርያ እንዳልሆኑ ደርሰህባቸዋል። ይህንን አደንቅልሃለው ብሏቸዋል ጌታችን። ይሄ ሐዋርያዊ ትምህርት ተጽፎ ስለተሰጣቸው፤ እንዲህ ባለ አስደናቂ ምክር ተገርተው ስላደጉ፤ ሐዋርያ ያልሆነውን ሐዋርያ አይደለህም ብለው ዞር ያደርጉት ነበር።

መንፈሳዊ መደባለቅ፤ ጎራ መደባለቅ በበዛበት የትምህርት አውራቂስ፤ የሀሰት ማዕበል፤ የብዙዎችን ታንኳ እየመታበት ባለበት በዚህ ዘመን ውስጥ፤ ሰዎችን ከእውነት መንገድ ዞር የሚያደርጉ፤ መጽሐፍ እንደሚል የአንዳንዶችን እምነት የሚገለብጡ፤ እምነት ገልባጮች እውነቱን ከላይ አሳይተው ሀሰትንና መርዝን ከታች አስርገው፤ አሽሉከው የሚያስገቡ በበዙበት በዚህ ዘመን፤ የመስቀሉ ስር ቁማርተኞች gamblers በረቂቅ ተንኮል እንደወጣ ቁማርተኛ፤ በወንጌል ላይ ቁማር ለመስራት የወጡ ሰዎች የመድረክ ላይ አፈ ቀላጤነትና ጮሌነታቸውን ተጠቅመው ብዙ የዋሆችን በእግዚአብሔር ቃል ያላደጉትን የሚያስቱ ሰዎች፤ በጾታ በቀለም በበዙበት በዚህ ዘመን ውስጥ እንደ ህጻናት መሆን አያስፈልገንም።

በአስተምህሮ ንፋስ ወዲያና ወዲህ መፍገምገም አያስፈልገንም። በማዕበል ወደ ፊት ወደ ኋላ መሄድ አያስፈልገንም። ከመንፈሳዊ ሕፃንነት መውጣት አለብን። በእግዚአብሔር ቃል በሐዋርያቱ ምክር በተቀበልነው በዚያ አንድ ሃይማኖት እስከመጨረሻ ጸንቶ የመቆም ቁርጠኝነት እያንዳንዳችን ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር በሰማያዊ ስፍራ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ከባረካችሁ በፊቱ ቅዱሳንና አለ ነውር ትሆኑ ዘንድ አለም ሳይፈጠር በክርስቶስ ኢየሱስ በፍቅር ከመረጣችሁ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ከወሰነን በክርስቶስ ኢየሱስ ህያዋን ካደረገን በሐዋርያትና በነቢያት መሰረት ላይ የታነጽን ከሆንን እንደ አካል ደግሞ እየተገነባን ሙሉ ሰው እንድንሆንለት የአገልግሎት ስራም እንዲበዛልን መልእክተኞችን ነቢያትን እረኞችን አስተማሪዎችን ከሰጠን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ከሰጠን እንደዚህ ያሉ ነገሮች ደግሞ የበዛላቸው አማኞች ከሆንን ከንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን በልዩ ልዩ አይነት የትምህርት ንፋስ በሰዎችም ረቂቅ ተንኮልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ህጻናት መሆን አይገባንም።

ሳሚ ቱራ

ከሎሌ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን YouTube ላይ የተወሰደ
https://www.youtube.com/

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ከመነሣቴ በፊት፤ ልጽፍ ያሰብሁበት ርእሰ ጕዳይ “ዘፈን” አልነበረም። ከዘፈን ጕዳይ በላይ የሚያሳስቡኝና እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል...
20/04/2026

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ከመነሣቴ በፊት፤ ልጽፍ ያሰብሁበት ርእሰ ጕዳይ “ዘፈን” አልነበረም። ከዘፈን ጕዳይ በላይ የሚያሳስቡኝና እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ከምላቸው ጕዳዮች አንዱ በሆነው የቤተ ክርስቲያን ምንነት ላይ ነበር ዐሳቤን ማካፈል የፈለግሁት። ስለ ቤተ ክርስቲያን ጕዳይ ለዓመታት በውስጥ የሚነድድ ብርቱ ቅንዓት አለኝ። በዚህም ምክንያት የወንጌላውያን ቤተ እምነቶች አካሄድ እግዚአብሔር ለቤቱ ካለው ንድፍና ልብ እጅግ ርቆ፣ የሰው ሥርዐት ተጠናውቶት ያለበትን አካሄድ በተመለከተ የሚሰማኝን ለማጋራት ነበር አነሣሤ። ከሰፊው አማኝ ማኅበረ ሰብ ጋር በቶሎ እንዳልቀላቀል ከልክሎኝ የቈየውም ዋና ምክንያት ይኸው ነበር። ይህም ‘ከእሻላለሁ’ ባይነት በመነሣት ሳይሆን፣ ጌታ ኢየሱስን ወደ ማመን ከመጣሁበት ሁኔታ የተነሣ ነው። ጌታን መቀበል የቻልሁት ቤተ ክርስቲያን ‘ጠፉ’ ብላ ባገለለቻቸው ሙዚቀኞች በኩል ነበር። በዚህም ምክንያት እምነቴን እለማመድ የነበረው፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ጽኑ የእግዚአብሔር ድምፅ በመቀበል፣ የኅብረት አካሄድንም በቃሉ ላይ የነበረችውን የመጀመርያዋን ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በማድረግና ያንን ሕይወት ለመለማመድ በመሞከር ነበር። መሬት ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያን አካሄድ ከቃሉ ከተረዳሁት ጋር ሊታረቅልኝ ሳይችል ከመቈየቱ የተነሣ የተቸገርሁትን መቸገር፣ ስለ ጌታና ስለ ቤቱ ፍቅር ስል ከነጥያቄዬም ቢሆን በግልጽ የተቀላቀልሁትንና እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ ለመታነጹ ራሴን ልሰጠውና፣ እኔም ልታነጽበት ለምወድደው ማኅበረ ሰብ ለማካፈል በማሰብ ነበር። ሆኖም ግን፣ ከተገኘሁበት ዓለምና ሳገለግል ከኖርሁበት ሙያ የተነሣ፣ አስቀድሜ አከራካሪውን የዘፈን ጕዳይ ማንሣት እንዳለብኝ አመንሁ። ይህን ስጽፍ ሊከተል የሚችለውን ተቃውሞና የፍርድ ውርጅብኝ ሳልጠረጥር ቀርቼ አይደለም፤ ነገር ግን፣ ጀግንነት (courage) ከፍርሀት ይልቅ በጎ ነውና ለበጎ ደፈርሁ።

ጌታን በሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ማግኘት
አንዱ ጌታ ለወደደንና ለሞተልን ታናናሾች በተለያየ መንገድና ሁኔታ ራሱን ይገልጣል። በመንገዱ ላይ ሲያስጕዘንና በአንዱ በእርሱ እውነት ላይ ተመሥርተን ስንሄድም በተለያየ ፍጥነትና አካሄድ ነው። በእርሱ አንድ እንድንሆን እንጂ፣ አንድ ዐይነት እንድንሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። እኔም እንደ አንድ ልትድን እንደ ታደለች ነፍስ፣ የእርሱ ምስክር ሆነው የወንጌልን እውነት ሊያካፍሉኝ የወደዱት ወንድሞች፣ በሰፊው አማኝ ማኅበረ ሰብ መረዳት “ቤተ ክርስቲያን” የሚሄዱና በዚያም በተለመደው መልኩ የሚያገለግሉ አልነበሩም፤ እንደውም “ዓለማዊ” ተብሎ የተፈረጀን ሙዚቃ በመጫወታቸው ምክንያት ከተቋማዊው ኅብረት የተገለሉ ነበሩ። እነኚህ ወንድሞች በርግጥ ዓለማዊ ሙዚቃን ተጫውተዋል፤ ከቤተ ክርስቲያን ርቀው በነበሩባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታትም ፍጹም ዓለማዊ በሆነና ጠፉ በሚያስብል ዐይነት ሕይወት ዐልፈዋል። ሆኖም ግን፣ ለጥቂት ጊዜያት ተይዘውበት ከነበረው ክፉ አካሄድ ተላቅቀው፣ ራሳቸውን በቃሉ ጥናት እያተጕና እንደ ቃሉ ለመኖር፣ ብሎም ሌሎችንም ለመድረስ መለማመድን በጀመሩ ጊዜ፣ እንደ እኔ ላሉት መድረስ ችለው ነበር። ጌታን በእነርሱ በኩል ከማግኘቴ የተነሣ በቀጥታ የወረስሁት ወይም የተለማመድሁት የቤተ እምነት ሥርዐት ወይም ልማድ አልነበረም፤ ክርስትናንም የተረዳሁት ከአንድ የሃይማኖት ጎራ ከመመደብ በተለየ ነበር። በሕይወቴ የነበረው ለውጥ ከነበርሁበት የራስ ገዝ ሕይወትና አመለካከት፣ እግዚአብሔርን በቃሉ መሠረት ወደ መታዘዝ፣ እርሱን ወደ መምሰል ማደግና ወደ መሰጠት ሕይወት የመሻገር ነበር።

በዓለማዊነትና በዓለማዊ ሥርዐት ውስጥ እንዳሻው ይመላለስ ለነበረ ሰው ወደ እምነት መንገድ፣ ይህም የናዝሬቱ ኢየሱስ እርሱ ጌታ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ወደ ማመን ለመጣ ማንኛውም ሰው ለውጡ ሥር ነቀል ይሆናል። ይህም ለውጥ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣን ግዛት ዜግነት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ዜግነት፣ ከራስ ፍቃድና ፍልስፍና ወደ አንድ የአምላክ ፈቃድ፣ ከኀጢአት ባርነት ወደ እግዚአብሔር ባርነት፣ ለምንወድደው ከመኖር እርሱ ለሚወድደው ወደ መኖር የሚደረግ የሕይወት ለውጥ ነው። እርሱ በሞቱ የሰጠንን ሕይወት እኛም ለፈቃዳችን በመሞት፣ በፍቃዱ በሕይወት ወደ መኖር የተሻግርንበትና እየተሻገርን የምንኖርበት ሕይወት ነው። እንግዲህ በዚሁ መረዳት ሙዚቃዊ አርቲስትነትም እንደ ማንኛውም ተግባርና ፍላጎት በእግዚአብሔር ቃል ሊመዘንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሆን አለመሆኑ ሊፈተሽ የሚገባው ነው። እኔም ወደ ክርስቶስ መንገድ በመጣሁ ጊዜ የነበርሁበትን ሕይወት በቃሉ ማስፈተሼ አልቀረም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለን አማኞች መካከል አንድ ሰው ወደ መንፈሳዊነት ማዘንበሉን ወይም ከዓለማዊነት መላቀቁን ከሚገልጥባቸው ዋና ነገሮች መካከል፣ ዘፈን አለማድመጥ ወይም ሙዚቃ በሚቀርብባቸው ዝግጅቶች ላይ አለመታደም አንዱ ነው። ወደ እምነት የመጣው ሰው አስቀድሞ በሙዚቃ ሙያ ውስጥ የነበረ ከሆነ ደግሞ፣ ሙያውን ማውገዝና ከልምምዱ መውጣት የተለመደ ተግባር ነው። በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ ዘፈንን በተመለከተ ያለው አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ ይልቅ ልማድ ላይ የተመሠረተ ይመስላል። ከእግዚአብሔር ዐሳብ በተቃራኒ ያሉ ብዙ ዓለማዊ ዕሴቶችንና አመለካከቶችን ዜማ ስለሌላቸው ብቻ እቅፍ ድግፍ አድርጎ የያዘ ማኅበረ ሰብ፣ በቅዱስ ቃሉ ላይ ግልጽ የሆነ ሙሉ ኵነኔ የሌለበትን የሙዚቃ ጕዳይ እንደ ጽድቅ መመዘኛ አድርጎ መውሰዱ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ፍትሕ የጎደለው ሆኖ ይሰማኛል፤ በዚህም ፍርደ ገምድልነት ብዙዎች እንደተጎዱ አውቃለሁ።

ይህን ጕዳይ ሳነሣ ለዘፈን ጥብቅና ልቈም ፈልጌ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ እውነትን መናገርም ሆነ መነጋገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ደግሞ አምናለሁ። በዐጭሩ በሚያግባባን ቋንቋ ለመግለጽ፣ እኔ አሁን ዘፋኝ አይደለሁም። ስለ ዘፈን ለመጻፍ የተገደድሁት፣ እኔና እኔን መሰል ሙዚቀኞች ‘መብታችን ነው’ ባልነው መንገድ ስንሄድ የሚመለከቱን ወጣቶች፣ ‘የኢየሱስም የሙዚቃም መሆን ይቻላል’ የምንልበትን ዐሳብ ወይም ልብ ሳይረዱ በተሳሳተ ጎዳና እንዳይሄዱ ለማድረግ ነው። እኛን ተመልክተው እንደ ቃሉ ሳይሆን ለተጠላውና የኢየሱስ ለሆኑቱ ለማይገባው ዘፋኝነት የተጋለጡ ቢኖሩ፣ እነርሱን ለመመለስና አካሄዳቸውን የማስተካከል ዕድል ለመስጠት ነው። በሌላ አንጻር ደግሞ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተገቢው መንገድ ከመግለጽ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር በላይ ሰውን በመፍራትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሲሉ፣ የብዙዎችን ጥያቄ በቸልተኝነት ሳያስተናግዱ በቀሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ አገልጋዮችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምክንያት የተሰናከሉ ታናናሾች ቢኖሩ አቋሜንና መረዳቴን በማካፈል በጎ አስተዋጽዖ ለማበርከት ነው።

በአማኙ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ስለ ጾታዊ ግንኙነት ያልሆኑ፣ በተለይ ስለ አገር የተዘፈኑ ዘፈኖችን ይዘታቸውና ጭብጣቸው ምንም ቢሆን ምን ከመዝሙር የመቍጠሩ ዝንባሌም ተገቢ አይደለም። የትኛውም የጥበብ ሥራ (ከሙዚቃዊ ጥበብ ውጪ ያሉትንም ጨምሮ) ሊዳኝ የሚገባው ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር የሚያንጸባርቀውን እውነት በመፈተሽ ነው።

እኔ እንደተረዳሁትና መገንዘብ እንደቻልሁት፣ ዘፈን በዋናነት ኀጢአት ሆኖ የሚጠቀስበት የገላትያ 5፥21 ዐውድ የሚያመለክተው፣ ቅጥ ያጣና ልከኝነት የጎደለውን የሕይወት ዘይቤ በሙዚቃ ውስጥ መግለጽን ነው። ይህም ፍጹም ዓለማዊነትን የሚያንጸባርቅና የእግዚአብሔርን መኖር በዘነጋ መንፈስ የሚቀርብ ክንውን ሲሆን፣ ሥጋን በማስደሰት ላይ ባተኰረ አደራረግ የሚካሄድን ፌሽታና ገደብ የሌለው መዝናናትን የሚያመለክት ነው።

"የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው፤ እርሱም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመሰል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፣ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። (ገላትያ 5፥19- 21)"

አማኝ ነኝ የሚል ሁሉ በማንኛውም ጊዜ እንደ መንፈሳዊ ሰው፣ በመንፈስ ሊመላለስ ይገባዋል። መንፈሳዊ ሰው ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን በሁሉም ስፍራ የሚያደርግ ነው። በዚሁ መንፈስ ስንመላለስ፣ በመዝሙር ስም ስንዘፍን ከምንገኝባቸው ሁኔታዎችም ጭምር እንቆጠባለን ማለት ነው። እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ስም በሚሰበሰቡት ሕዝቡ መካከል መገኘትን የሚወድድ፣ በእውነትና በመንፈስ የሚመለክ አምላክ ነው። እርሱን በማምለክ ስም (ሽፋን) ሥጋችንን ለማስደሰት በምናደርገው ሁሉ እግዚአብሔር አይከብርም። ይህን ስል ስለ ሙዚቃ ዘውግና መሰል ገደቦች እያወራሁ አይደለም፤ ስለ እውነተኝነትና በፍጹም ልብ ሊሆን ስለሚገባው ሙዚቃዊ አገልግሎት እንጂ።

Zeritu Kebede

ይህ ጽሁፍ የተወሰደው ዘሪቱ በሕንጸት መጽሄት July 18, 2022 ላይ ከጻፈችው ነው።

ሙሉ ጽሁፉን ለማንበብ የሚከተለውም መስፈንጠሪያ ይጫኑ 👇
https://hintset.org/articles/about-zefen/

ደቦ አሊያንስ ፎር ችልድረን (Debo Alliance for Children) ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ወላጅ አጥ እና ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ ህፃናትን ለመርዳት እየሰራ ስላለው ተልዕኮና...
16/04/2026

ደቦ አሊያንስ ፎር ችልድረን (Debo Alliance for Children) ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ወላጅ አጥ እና ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ ህፃናትን ለመርዳት እየሰራ ስላለው ተልዕኮና በመጪው ግንቦት 5 እና 6 "አለኝታ" በሚል መሪ ቃል 9ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ስለመዘጋጀቱ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በሳሮማሪያ ሆቴል በተሰጠው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ተናጋሪዎቹም የጥምረቱን አስፈላጊነትና የወደፊት ዕቅዶችን በዝርዝር አብራርተዋል። በመጀመሪያ መግለጫ የሰጡት ወይዘሮ ሚሻሜ ደስአለኝ የጥምረቱን ራዕይና ተልዕኮ ሲያብራሩ፣ ደቦ አሊያንስ የበጎ አድራጎትና የሃይማኖት ተቋማት ጥምረት ሆኖ የተመሰረተው እያንዳንዱ ህፃን በቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ እንዲያድግ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። ጥምረቱ በመተባበር የላቀ ተፅዕኖ መፍጠር፣ በትህትና ላይ የተመሰረተ አንድነት፣ በርህራሄ ማገልገል እና ለተሻለ ተሞክሮ ቁርጠኛ መሆን በሚሉ አራት ዋና እሴቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ሚሻሜ፣ የህፃናትን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ማህበረሰቡና መንግስት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሲቢሉ ቦጃ በበኩላቸው፣ የጥምረቱን አመጣጥና እድገት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ደቦ አሊያንስ የተመሰረተው ከ14 ዓመታት በፊት መስራቾቹ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የጉዲፈቻ ጉባኤ ላይ ካገኙት ተሞክሮ በመነሳት መሆኑን አውስተዋል። በስምንት መስራች ድርጅቶች ተጀምሮ አሁን ላይ 14 አባል ድርጅቶችን ለማቀፍ የበቃው ይህ ጥምረት፣ ትኩረቱን በቤተሰብ ላይ ያተኮረ እንክብካቤ ላይ ማድረጉን ገልጸዋል። አቶ ሲቢሉ አክለውም ህፃናት ከቤተሰብ እንዳይለዩ መከላከል፣ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲያድጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና በውጭ እርዳታ ላይ ከመደገፍ ይልቅ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን መጠቀም የወደፊት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አሳስበዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ጉልላት ታደሰ ደግሞ በሀገራችን በግጭት፣ በበሽታና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ለችግር ቢጋለጡም ድምፃቸው ብዙ ጊዜ የማይሰማ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት "አለኝታ" በሚል መሪ ቃል 9ኛው ዓመታዊ ጉባኤ መዘጋጀቱንና ዓላማውም ህፃናት በቤተሰብ ውስጥ የደህንነትና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ የመንግስት አካላትና የሃይማኖት ተቋማት ለህፃናት ጥበቃ በጋራ እንዲቆሙና በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም አቶ በላይ የጥምረቱን ሶስት ዋና ዋና ስልታዊ ምሰሶዎች ማለትም ሰዎችን ማነቃቃት (Inspire)፣ ድርጅቶችን በተሻለ አሰራር ማስታጠቅ (Equip) እና ትስስር መፍጠር (Connect) የሚሉትን በዝርዝር አብራርተዋል። ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ መቆሙን ተከትሎ የጥምረቱ ስራ ለሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን የገለጹት አቶ በላይ፣ መጪው ጉባኤም ህዝቡን የሚያነቃቁ አጠቃላይ መድረኮችንና ባለሙያዎች ቴክኒካዊ ስልጠና የሚያገኙባቸውን ልዩ ክፍለ ጊዜዎች እንደሚያካትት ገልጸዋል። በአጠቃላይ ጋዜጣዊ መግለጫው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለህፃናት የተሻለ የድጋፍ ስርዓት ለመገንባት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ በማስተላለፍ ተጠናቋል።

ተዘጋጅተው ስለሚጠብቋችሁ በልጆች ዙሪያ ላይ መሳተፍ የምትፈልጉ ሁሉ መጥታችሁ በዚህ ፕሮግራም ላይ እንድትሳተፉና የመፍትሄው አካል እንድትሆኑ ተጋብዛችሗል። የምዝገባ ሊንኩን ከታች ታገኙታላችሁ!

Registration link https://www.deboalliance.org/orphansummitethiopia
+251908074740
[email protected]
0916152103 Mishame
0913145919 Banchiayehu

ቤተክርስቲያን ውስጥ ስብከት ላይ ወጣቶችን ቴክስት መደራረግን የማያስቆም መልእክት ከሌለኝ፣ ቴክስት መደራረግ ይቀጥሉ። መልዕክታችን እየተሰበከ እንኳን ኢንተርቴይመንት ሊያምረን፣ ሰዓት ጠብቀን...
16/04/2026

ቤተክርስቲያን ውስጥ ስብከት ላይ ወጣቶችን ቴክስት መደራረግን የማያስቆም መልእክት ከሌለኝ፣ ቴክስት መደራረግ ይቀጥሉ። መልዕክታችን እየተሰበከ እንኳን ኢንተርቴይመንት ሊያምረን፣ ሰዓት ጠብቀን የምንወስደውን መድኃኒት የሚያስረሳ መሆን አለበት። አሁን እኮ ስብከታችን ይዘት የለውም፤ እኛም የምናወራው ዝም ብሎ ተደጋጋሚ ቃላት ብቻ ነው። ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን አስገድደው ቸርች እንዲመጡ ያደርጓቸዋል። ልጆቻቸው ወይ ግቢ ውስጥ ይጫወታሉ ወይ በግድ ይቀመጣሉ። ዛሬ ማስተካከል ካልቻልን ከስረናል ማለት ነው። ለትውልዱ መልእክት አጥተናል ማለት ነው። ይዘት ያለው መልዕክት ይፈልጋሉ። ካልተዘጋጀን ትውልዱ በጣም ያመልጠናል። ፍጥነቱ በጣም ከፍተኛ ነው። እኛ ካልሰጠነው ዓለም የምሰጠው በጣም ብዙ አለ።

እኔ መልእክቴን ስዘጋጅ የሚያስጨንቀኝ አንዱ ነገር ይሄ ነው። እኔ ካልሰጠሁት፣ እኔ ካላጎረስኩት፣ ይህ ትውልድ አየር ላይ ተንጠልጥሎ አይኖርም። የሚያጎርሰው አለ። መንገዱ አማራጭ በአማራጭ ነው። ኢንተርኔት ላይ ቢገባ፣ ጎግል ቢያደርግ ብዙ የሚጠቅም ነገር ያገኛል። የኔን የማይጠቅም ነገር ለመስማት ለምን ቁጭ ይላል? ድሮ አማራጭ ስለሌለ ነው። ዛሬ ምንም የሚዘገይ ነገር የለም፤ ድሮ ጋዜጣ እንኳን በደንብ በሌለበት አገር ነበር። አሁን መዓት ነገር አለ። ሁሉን የሚያስጥል! እኛ የፈለግነውን ነገር እያደረግን ወጣቱ በጠብታ እያለቀቀው ነው። አሁን ቸርች ውስጥ ረሃብ በጣም አለ። በጣም! አንዳንድ ወጣቶች ያስታውቃሉ። ዓለም ነች የምትመግባቸው። እኛ ስላልመገብናቸው ረሃብ ዝም ብሎ አይኖርም። እውነተኛ ምግብ ካላገኘህ ቆሻሻ ያስበላሃል። መንፈሳዊ ረሃብ በጣም ስላላቸው በዚህ ይሞክሩታል፣ በዚያ ይሞክሩታል። እና ዓለም የምትሰጣቸው ጃንክ ሆኖባቸዋል፣ ሰልችቷቸዋል፤ ቸርች ደግሞ የምትሰጣቸው ብዙ ሚረባ ነገር የለም። ስለዚህ ምን ይሁኑ? እጆቼን ሳስብ በጣም እጨነቃለሁ። የልጅ ልጆቻችንን ስናስብ በጣም ሊጨንቀን ይገባል።

ወጣቱ እሁድ ቤተክርስቲያን ሲመጣ የሚጠቅም ነገር አገኛለሁ ብሎ ነው ሚመጣው፣ ሰኞ ዩኒቨርሲቲ ስመለስ የአስተማሪዎቼን ቻሌንጅ የሚያስቆም ነገር አገኛለሁ ብሎ ይመጣል ወይ? ወይስ we’re just playing church? ጉባኤ ለማድመቅ፣ ከዚያኛው ለመብለጥ፣ እዚያ ማዶ ያየነውን ለማምጣት... በዚህ ሁሉ መካከል የተሰቀለው ክርስቶስ የለም። አሁን የትዕይንት (performance) ስቃይ ማቆም መቻል አለብን።

ቤተክርስቲያን ምሳሌነቷ የሙሽሪትነት እንጂ የጋለሞትነት አይደለም።

እግዚአብሔር አንድ ጊዜ በጣም የተናገረኝ ይመስለኛል። ለትንሽ ጊዜ ሁሉ አገልግሎት ማቆም አምሮኝ ነበር። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ ናት። ጋለሞታ አይደለችም። ሙሽራችንን ከማግባታችን በፊት በደምብ እናውቃታለን። ምናልባትም የተለየ ጌጣጌጥ የሰርግ ቀን ነው የለበሰችው። ጌጣጌጧን አሰማምራና ለብሳ ስለመጣች አይደለም ያገባኋት። ያንን ሳትለብስ በፊት ነው የታጨችው። አንዳንድ ጊዜ በደንብ ለብሳ፣ አንዳንድ ጊዜ በደንብ ሳትለብስ፣ አንዳንድ ጊዜም ቆሽሻ። ያማረ ስትለብስ፣ ያማረ ሳትለብስ... ሙሽሪት ባሏን በውጭ ገጽታ በጭራሽ ለመማረክ የምትሞክር አይደለችም። ሙሽራ መሆን፣ ለአንድ ባል የታጨች መሆን ማለት እጅግ ትልቅ ክብር ነው። የሰርግ ቀን ይደርሳል፣ ግን ከሰርጉና ከድግሱ ቀን በፊት ነው ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የወደዳት፣ ያጫት።

ለምሳሌ እኛ አገር ላይ በአብዛኛው የኢኮኖሚክ ችግር ስላለባቸውና በዝሙት ስራ የሚተዳደሩ፣ መንገድ ላይ የሚቆሙ ሴቶች፣ በገንዘብ ስለሚቸገሩ ነው ብዬ ነው የማስበው። ድህነቱ ያመጣው ነገር ነው። ግን አንዳንድ ጊዜ መንገድ ላይ የምናያቸው እኚህ ሴቶች ወንድን ለማማለል የሚሞክሩት በውጭ ገጽታቸው ብቻ ነው። የሚሳቡላቸው ወንዶችም የውጭ ገጽታቸውን ብቻ አይተው ነው። ባህሪ አይተው አይደለም። እነሱም እርግጠኛ ሆነው የሚያደርጉት በውጭ ገጽታቸውን ማሳመር ነው፣ ሙሉ ትኩረታቸው እሱ ነው።

ቤተክርስቲያን እንደዛ አይደለችም። ውጭ ገጽታችንን እንደ ዓለም አሰማምረን፣ አዳራሾቻችን የፈለገ ያህል ቢያምሩ ሰው አይስቡም። ለሰው እንዲመች አዳራሽ ማሳመር በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን ህዝብን በዚህ መማረክ ማሰብ መንፈሳዊ ግልሙትና ነው። ኢየሱስን ከዓለም ጋር ማጋባት ነው። ኪቦርዱ፣ ሙዚቃው፣ ባንዱ፣ ጂፕሰሙ፣ ቀለሙ... ጥሩ ነው! እኔ ደስ ይለኛል። ያማረ መድረክ ሲሰራ በጣም ደስ ይላል። ይሄ ግን ወደ ኢየሱስ ያመጣል? ኧረ በፍጹም! ሰው ለማማረክ፣ የእግዚአብሔር ቃል የሌለበት 'ኑና ያማረ አዳራሽ እዩ?’ እንዴት አድርጎ ይማርካል? ይሄ እኮ ግልሙተኝነት ነው። ሙሽራ እኮ ሙሽራ ነች።ብዙ ትእይንት፣ ጓጓታው፣ ኳኳታው እንደ መሳሪያ ማየት በጣም ጥሩ ነው። በባንድ እንዘምራለን፣ ጥሩ ነው። እንደውም ለሙዚቃውና ለአርቱ ዓለም መበልጸግ ዋናው ምክንያት ቤተክርስቲያን ናት። በጣም ትልልቅ የሆኑ ሙዚቀኞች የወጡት፣ ዓለምን እስከዛሬ ድረስ የሚያስገርሙ ሙዚቃዎችና ኖታዎች የወጡት ከቤተክርስቲያን ነው። እንዘምር፣ መሳሪያዎችን እንጠቀም፣ አዳራሹን እናሳምረው፣ መብራቱ... ጥሩ ነው። መብራት አስጊጠን ኢየሱስ ከሌለ ግን ያስፈራል።

ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናትን የሆኑትን ለእኛም እየፈራሁ ነው። አሳምረው አሳምረው አሳምረው ሰርተው፣ አሁን በቃ ለመሸጥ እንኳን መከራ። መንግስት አንዳንድ ቦታ እኮ እየገባ ሁሉ ለማስቆም ይሞክራል። ሰዎች ህንጻውን ይዘው መቆየት ስለማይችሉ ትውልድ ጠፋ። በአዳራሽ የማትማርኩት ትውልድ መጣ። በአዳራሽ የተማረከ ነበር ላለፍቱት 30 40 ዓመታት፤ አሁን ግን አዳራሽ የማይማርከው ከቸርች ሽምጥጦ ጠፋ። ለዚህ ትውልድ የእኛ ጂፕሰም ቀፎ ነው። ለዚህ ትውልድ የእኛ ቀለምና ጌጣጌጥ በቃ ቀፎ ነው።

ዛሬ ትውልድ ላይ ትኩረት አድርገን ካልሰራን፣ ልጆቻችን ከልባቸው እንዲያመልኩ የሚያደርግ አገልግሎት ካላገለገልን፣ ይዘት ያለው ስብከት ከሌለን፣ ክርስቶስን ካላሳየናቸው፤ እናጣቸዋለን።

ከኒቆዲሞስ ሾው ቃለምልልስ ላይ የተወሰደ።
ሙሉ ቃለ ምልልሱን በሚከተለው ምስፈንጠሪያ ያገኙታል።
https://youtu.be/REe0weZiQxw

Equip Media- Mamusha Fenta

15/04/2026
እኛ አማኞች ነን፡፡ ያመንነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በገለጠውም የእውነት ትምህርት ነው፡፡ እርሱ ያለ አንዳች የሰው ጥረት፣ ያለምንም የኛ አስተዋጽኦ እንዲያው በጸጋው አዳነን፡፡ ...
14/04/2026

እኛ አማኞች ነን፡፡ ያመንነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በገለጠውም የእውነት ትምህርት ነው፡፡ እርሱ ያለ አንዳች የሰው ጥረት፣ ያለምንም የኛ አስተዋጽኦ እንዲያው በጸጋው አዳነን፡፡ መጽሐፍ አረጋግጦ እንደሚነግረን፡- “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፣ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንት አይደለም፡፡ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም፡፡” በከንቱ አልባሌ ኑሮ፣ በጨለማ ድንብርብር ሕይወት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ድንቁርናና ልበ ድፍንነት የኖረ ማንም ዐመፀኛ የአዳም ልጅ የጌታችን የፍቅር ጥሪ ሲገባውና አለኝታውን በእርሱ ሲያደርግ አመንሁህ ብሎ እጅ ሲሰጥ በዚህ ብቻ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ፡፡ እንዴት ያለ ታላቅ ጸጋ ነው! አድርግ፣ አታድርግ በሚሉ ሺህ ደንቦች ክስ ሥር የወደቅን ጎስቋሎች በጸጋ ብርቱ ክንድ ተነሣን፡፡ ምንም ምን ክፋት እንዳላደረግን ተቆጠርን፡፡ ወንጀለኛነታችን በእንከን የለሹ ክርስቶስ ላይ ሲያርፍ እኛ ጻድቃን ሆንን፡፡

ይህ ከመዓት ያተረፈን ጸጋ ሥራው እዚያ ላይ ተደምድሟልን? ከትቢያ ካነሣን በኋላ “እንግዲህ ዕወቁበት” ብሎ ትቶን ሄዷልን? መጽሐፍ እንደርሱ አይልም፡፡ ይልቁን አዳኙ ጸጋ አሠልጣኙም እርሱ ራሱ እንደሆነ አረጋግጦ ይነግረናል፡፡ “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞት ክደን የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ 2÷11-13)

የጸጋን ድነት የተቀበልን ሁላችን የጸጋን ሥልጠና የምንሸሸው ስለምንድነው? ጸጋ ኮ ሲያድነን ጉልበት እንደሆነን ሁሉ ሲያሠለጥነንም ዐቅም የሚሰጠን ከነስሙ ባለጸጋ ነው፡፡ እርግጥ ትምህርቱ ቆፍጣና ነው፡፡ በወለም ዘለምታ የሚያዝ አይደለም፡፡ ምን ያስተምራል የተባለ እንደሆነ ጳውሎስ እንደሚነግረን አንዱ ዋና ኮርሱ ክህደት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው የእምነት ትምህርት ቢሆንም እምነት የሚጸናው የማይታመነውን በመካድ ነው፡፡ የነፍሴን መድኃኒት መድኃኔአለምን ሙጥኝ አልኩት፣ ታመንሁበት የሚል አንድ ምስኪን የአዳም ልጅ ወዲያው አያይዞ ነፍሴን አውዳሚ መርዝ የሆነውን ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን እክዳለሁ እንዲል ጸጋ ይጠይቀዋል፡፡ በደባልነት ሊኖሩ ለማይችሉት ለእነዚህ ለሁለቱ ቁርጥ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ ለአንዱ አመኔታ ለሌለው ክህደት፡፡ በእሁድ ጧት ስብከታችን “ጌታን ለማመን የወሰናችሁ ወደፊት ኑ” እንደምንል ሁሉ “ዓለማዊነትን ለመካድ የቆረጣችሁ ወደፊት ኑና ይጸለይላችሁ” ማለት የሚገባን ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ ዘመን እያንዳንዱን አማኝ እና ቤተክርስቲያንን በጥቅሉ እየናጡ ካሉ ከፍተኛ ኃይላት መካከል ምናልባት ዋነኛው ዓለማዊነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህች ዓለም አሮጌ ብትሆንም፣ ዘዴዎቿ ድሮ ገና የታወቁ ቢሆንም፣ “እኔን ያየህ ተቀጣ” የሚሉ እርሷ ወግታ የጣለቻቸው አያሌ ቢሆኑም÷ዛሬም እንኳ ወይንጠጇ ያንገዳግዳል፤ ዛሬም የደጃፏ ድጥ ሙልጭልጭ ነው፡፡

ዓለማዊነትን ብርቱ ያደረገው ምንድነው ቢባል አባባይነቱ ነው፡፡ የደስታና የርካታ ገበታ አቅርቦ ማስጎምጀቱ፣ የባልጀራ የአጫፋሪ ብዛት አሳይቶ ማባባሉ፣ የዋስትና የአለኝታ ዜና እየለፈፈ ማሳሳቱ፣ የክብር የዝናና የታዋቂነት ሥዕል እየሳለ ማማለሉ፣ ይህን ይህን የሚመስል ደመነፍሳዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ፍላጎታችንን ተገን ያደረጉ ብዙ ማባበሎች እንደ ሠራዊት በፊታችን ማሰለፉ ነው ያርበተበተን፡፡ ጉልበቱ የእኛ ልዩ ልዩ ዐይነት ራብ ነው፡፡ እንግዲያው ዓለማዊነት የማይደፍረው ወይም ቢቃጣም የማያንበረክከው የጠረቃውን ሰው ነው፡፡ በልቶ የጠገበ፣ ጠጥቶ የረካ፣ እግሩ የፈረጠመ፣ ልቡ ሙሉ የሆነ፣ ዓይኑ ያተኮረ፣ ልቡናው የሰመረ ሰው ሲያገኝ ትግሉን አይችለውም፡፡

የዓለማዊነት መርዝ ማርከሻው እግዚአብሔር መሰልነት (Godliness) ነው ይህም ማለት እውነተኛ መንፈሳዊነት ማለት ነው፡፡ ከእርካታ ሁሉ ምንጭ ከሰማዩ አምላክ የሚያገኘውን የመንፈስ ቅዱስ ፍስሓ ያገኘ ሰው ሌላው ሌላው ፈንጠዝያ ተራና አልባሌ ይሆንበታል፡፡ በሰው ቋንቋ ከመገለጽ በላይ ከፍ ያለውን የክርስቶስን ፍቅር የሚያጣጥም ሰው የዓለም ፍቅር መናኛ ይሆንበታል፡፡ ከማርና ከወለላውም የሚጣፍጠውን የቃለ እግዚአብሔርን ማዕድ የቀመሰ ሰው እንቶ ፈንቶ የሆነውን ያሁኑን ዓለም ትዕይንት ይንቃል፡፡ በሕይወት መጽሐፍ ስሙ መጻፉን የተገነዘበ ሰው ለአላፊ ጠፊ የዚህ ዓለም መዝገብ እጅግም አይጨነቅም፡፡ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም” “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡” ተብሎ የተነገረውና ይኸው ተስፋ የዘለቀው ሰው ዓለም ዋስትናና መተማመኛ እያለች የምታቀርብለትን ሁሉ ዝቅ አድርጎ ለመመልከት ጉልበት ያገኛል፡፡ ወዳጆቼ ዓለማዊነት “ዞር በል” በማለት ብቻ የምንረታው ጠላት አይደለም፤ እኩይ መሠሪ ስለሆነ በየራባችን ቀዳዳዎች ሁሉ እየገባ “አለሁ” ይለናል እንግዲያው ሥራችን ራብን ማጥፋት ሊሆን ይገባል፡፡ ለቅልውጥ ችግር አብነቱ ይኸው ነው፡፡ እቤት በልቶ መሠማራት፡፡ የእግዚአብሔርን አርኪነት በዝርዝር እየገባን መረዳት፤ በዚሁ ርካታ ውስጥ ለመኖር ራሳችንን ማሠልጠን፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የእርካታ ቤት እንጂ ጠኔ ያጠላበት የተራቆተ ቤት እንዳይሆን የፍቅርን ገበታ፣ የሰላምን ማዕድ፣ የደስታን ዘይት ቶሎ ቶሎ ከመንፈስ ቅዱስ እየተቀበልን ሲጎድል እያስሞላን ማዕዱ እንዳያጥጥ፣ ራብተኛም እንዳይደነግጥ መትጋት የጊዜው ዋና ጥሪ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

የጸጋ ሥልጠና የራስ መግዛትም ሥልጠና ነው፡፡ ለካ ራስ መገዛት ያለበት ነገር ነው፡፡ ያልተገዛ እንደሆነ አፈትልኮ ወጥቶ አምባውን ሁሉ ያሸብራል፡፡ የሚይዘውን የሚጨብጠውን እንደማያውቅ ድንጉላ ፈረስ ሜዳውን ሁሉ ይጎደፍራል፤ አጉራ ዘለል ይሆናል፡፡ ክልክል የሚባል እንደሌለ እያመነና እያሳመነ አገሩን በማን አለብኝነት ይሞላል፡፡ የድፍረቱን ዕዳ ጽዋ እያንገሸገሸው እስኪጠጣ ድረስ ማረፊያም የለውም፡፡ አዳኙ ጸጋ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ እንዳወጣን ሁሉ ከራሳችንም ሊያድነን ነው የመጣው፡፡ የራስን ገናን ጉልበት የሚያንቀሳቅሰውን የሥጋ ሞተር በመንፈስ ቅዱስ ብርቱ ኃይል ሊተካው ነው የተዛመደን፡፡ ወዳጆቼ ራስ በምን ይገዛል በጌታ ቃል እውነት ብርሃን ያገኘ ኅሊና በመንፈስ ቅዱስ ዐቅም ካላንበረከከው በቀር! “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ… የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡” የተባለው እኮ የራስ ፈቃድ እየገነነ በሚያቅራራበት ክፉ ዘመን ዐውድ ውስጥ ነው፡፡ እንግዲያው ወገኖቼ በራስ እንዳንሞላ፣ ናላ በሚያዞር በነገርና በምናምንቴው ሁሉ እንዳንሰክር የልባችንን ማድጋ ተሸቀዳድመን ቅዱሱን መንፈስ እናስሞላው፡፡ የዘመናዊው ሰው አንድ በሽታ የዐይኑ መቃበዝ ነው፤ የዙሪያ ገባው ውልብልብታ እረፍት አልሰጠውምና ውልብ ያለውን ሁሉ ለማየት ሲዟዟር የአንገቱ ዋልታ ላላ፡፡ የገበያ ጋኔን ከሁሉ ሳይከፋም አይቀር፡፡ የዕቃ፣ የአስተሳሰብ፣ የቄንጥ፣ የአላፊ አግዳሚ ወረት ሁሉ ልቡናችንን አቅበዘበዙት፡፡ ትክ ብሎ የሚታይ እየጠፋ እይታ የአፍታ የአፍታ ብቻ እየሆነ ሕይወት አዙሪት ጨዋታ ውስጥ ወደቀች፡፡ የጸጋ ትምህርት የትክታ ትምህርት ነው፡፡ አትኩሮ የማየት፤ ጸንቶ የመጠበቅ፡፡

“የተባረከ ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን እንድንኖር ያስተምረናል፡፡” አትኩሮት ለመላ አካላችን ቅርጽ ይሰጣል፤ ወደ አተኮርንበት አቅጣጫ እናዘምማለን፡፡ ከሰማይ የሚመጣውን ይህን ክቡር ጌታ ስንጠብቅ የተነጣጠረ ሕይወትና ደማቅ መስመር እናገኛለን፡፡ ዓይናችንም መንከራተቱን ይገታና ሁነኛ ነገር ላይ ይውላል፡፡ የየዕለት እርምጃችን ከየስላቹ በሚያንባርቅ ጥሩምባ ሳይሆን በሰማይ ቅኝት ይመራል፡፡ ባለ ክቡር ዓላማ ገስጋሽ ሠራዊት እንሆናለን፡፡ ጸጋው አማኞች ብቻ ሳይሆን ጠባቂዎችም ያደርገናል፡፡ ክርስቲያንነት ጥበቃ ነው፤ የዘወትር ተጠንቀቅ ነው፤ ሁሉ ነገር ያው የሆነበት ምድር ዓለሙ ሳይቋረጥ የሚጓዝበት የሰው ልጅ ታሪክ ዞሮ እየገጠመ እንደገና ዝንተዓለሙን የሚዞርበት ሽክርክሪት ሳይሆን ታሪክ ሁሉ ወደ አንድ ሁነኛ መድረሻ የሚገሠግስበት በዚህም ሳቢያ አማኙ ሰው “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ፣ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋሁ” የሚልበት ንቁ (active) ሕይወት ነው፡፡ እነዚህ ቆፍጣና የጸጋ ትምህርቶች መነሻቸው የክርስቶስ ሞት ዓላማ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጸጋ መገለጥ ከጸጋም ሥልጠና ጋር አያይዞ የሚያነሣ መሠረቱና ድምድማቱ መስቀለ ኢየሱስ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለምንድነው?” የሚለውን ዋና ጥያቄ ለወትሮ በምንመልስበት “የሰማይ ቤት ሊያወርሰኝ” በሚል ወደፊታዊ መልስ ብቻ አያቀርበውም፡፡ የጌታችን ሞት ፋይዳ የዛሬም ጉዳይ ነው፡፡ የዛሬ ኑሮ ጉዳይ ነው፡፡ “ከዐመፅ ሁሉ ሊቤዠን” ሞተ ይለናል፡፡ የዐመፀኛነት፣ የመለኮትን ሃሳብ የመቃወም የራስን ሃሳብ የማግነን የጌታችንን ትዕዛዝ የመግፋት፣ የእንቢታ፣ የሽፍትነት ባሕርያችንን ሊለውጥልን ከዚህ ዲያብሎሳዊ ክፉ ዐመል ሊያላቅቀን ሞተ ይለናል፡፡ “መልካሙን ለማድረግ የሚቀና ሕዝብ” ፈልጎ ሞተ ይለናል፡፡ በመስቀሉ የተዋጀው ሕዝብ ሥራው ባያድነውም ከዳነ በኋላ ግን ብርቱ የመልካም ሥራ ዐርበኛ እንዲሆን ተፈልጎአል፡፡ “በጎ ሥራ የት ይገኛል? ብሎ በዓይኑ የሚማትር ሲያገኘውም በትጋት የሚፈጽመው ቅን ኅብረተሰብ የመስቀሉ ምርት ነው፡፡ “ገንዘቡ የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ” ሞተ ይለናል፡፡ የክርስቶስ ሞት አንድም የግዢ ውል ነው፡፡ በደሙ ስለገዛን የባለቤትነት ሙሉ መብት አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱ ሕዝብ፣ ለወደደው ዓላማና ተግባር የሚያሰማራው ሠራዊት ፈልጎ ነው የሞተ፡፡ ታላቁ ጠቢብ በዚህ ሙዐለ ሕይወት (ኢንቨስትመንት) ሊከስር አይሻም፡፡ የተባለው ሁሉ ተብሎ እንደ አንድ የክርስቶስ ተከታይ እንደ ቤተክርስቲያንም ልናስብባቸው የሚገቡ ሁለት ዋና ነገሮች ይታዩኛል፡፡ የተያያዙም ቢሆኑ በየስማቸው ቢጠሩ ይወዳሉ፡፡ መጀመሪያ ነገር እስከዛሬ ስንማር ስናስተምር የቆየነው ስለማመን ስለመቀበል ጌታን እሺ ስለማለት ነበርና አሁን ደግሞ ጨምረን ክህደትን እንማር፣ እናስተምር፡፡ ያው እንደተባባልነው በወደር የለሹ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለማጽናት ተፎካካሪ ገናኖችን ልክ ልካቸውን ነግረን ቦታቸውን እናሳያቸው፣ ለአንድ ጌታ ሎሌነት ማደራችንን እናስታውቃቸው ብዙ የሚካዱ ኅሳዌ መሲኃን (እንደዚህ ሲባል ሥጋ የለበሱ ሰዎችን ብቻ ለምን እናስባለን) ከጽድቅ የሚያፈናቅሉንን የራሳችንን አጓጉል ምኞቶችና ዐመፀኛነቶች እንዳሉ ለባልጀሮቻችን ሁሉ እንንገር፡፡ ክፉውን ደግ ደጉን ክፉ የሚያደርገውን፣ ክቡሩን ቀሊል ገለባውን ፍሬ የሚያስመስለውን የዓለሙን የተዛባ ሥራተ እሴት አንቀበልም ብለን እንካድ፡፡

ሁለተኛ ነገር ይህን ዓለም ማሸነፊያ ዮሐንስ እንደነገረን በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለ እምነታችን ነውና በእርሱ ያለንን እምነት ስንኖርበት የሚያዩ ሁሉ “ውይ እንዴት ያማረ እንዴት የሰመረ ሕይወት ነው” እንዲሉ በጌታ ዘንድ ያለውን ሀብት እንጠቀምበት፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ” እንደተሰኘው ተረት እንዳይሆንብን ከመለኮታዊ ጸጋው የሚመነጨውን ደስታ፣ ፍቅር፣ ሰላምና ርካታ የሚያጣጥም ምላስ እናዳብር፡፡ ጤነኛ አፒታይት (የምግብ ፍላጎት) እንዲፈጥርልን የነፍሳችንን ጌታ እንለምነው፡፡ እናምናለን በመስቀሉ እንቆማለን በወንጌሉ ሕያው ሆኖ ይሠራል አልተለወጠም ቃሉ፡፡

Negussie Bulcha

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ሁሉ የዳነ አይደለም። ቆሞ ጌታን የተቀበለ ሁሉ የዳነ አይደለም። ብዙ ጊዜ ችግራችን የዳንነው በእምነት ነው፤ እሱ ላይ ብቻ ነው የምንቀረው። ብቻውን በቆመ እምነት...
13/04/2026

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ሁሉ የዳነ አይደለም። ቆሞ ጌታን የተቀበለ ሁሉ የዳነ አይደለም። ብዙ ጊዜ ችግራችን የዳንነው በእምነት ነው፤ እሱ ላይ ብቻ ነው የምንቀረው። ብቻውን በቆመ እምነት እንደዳንን እናስባለን፤ እምነት ብቻ ብለን ነው የምናስበው። ነገር ግን ከእምነት ወደሚገኝ መታዘዝ ነው የተጠራነው። ያመነ ሰው ወደ መታዘዝ መምጣት አለበት። ህይወቱ መታዘዝ የሚታይበት መሆን አለበት። አለበለዚያ መዳኑን በምን እናውቃለን? ወንጌል እንደለወጠን በምን ይታወቃል?

ስንዴው መሐል እንክርዳድ አለ፤ መጽሐፉ እንደዛ ነው የሚለው። አሳ አጥማጁ ያወጣው መረብ ውስጥ አሳ ብቻ አይደለም ያለው። ቀኑ ሲመጣ የሚገለጡ ብዙ ነገሮች አሉ። የኢየሱስን ስም የጠራ ሁሉ፣ መባና አስራት የሰጠ ሁሉ የዳነ አይደለም። እያየን ነው አይደል? ዘመኑ ግልጽ ነው። በኢየሱስ ስም የሚሰሩ፣ በአገልግሎት ስም የሚሰሩ ብዙ ነገሮች እናያለን። ከእምነት ወደሚገኝ መታዘዝ ነው የተጠራነው።

ሮሜ 16:26 ላይ መልዕክቱንም ሲጨርስ ይህን ነገር ያነሳል፤
"አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምስጢር እንደተገለጠ..."

እምነትና መታዘዝ የተያያዘ ነው። እምነት ብቻውን ሊቆም አይችልም። እብራውያን 11 ላይ አብርሃም እንዳመነ፣ እንደታዘዘም ሰምታችኋል ነው የሚለው። አብርሃም አመነ፣ ከዚያ ደግሞ ታዘዘ! መታዘዝ ከእምነት ጋር መጣበቅ አለበት። እምነት፣ እግዚአብሔርን ወደ መታዘዝ፣ ጽድቅን ወደ መታዘዝ፣ ፍቅርን ወደ መታዘዝ፣ ክርስቶስን ወደ መታዘዝ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወደ መታዘዝ መምራት አለበት። እግዚአብሔርን እሺ ወደ ማለት መሄድ አለበት። እምነት ከመታዘዝ ጋር ካልተገናኘ፣ ሰዎች የመታዘዝ ልጆች ካልሆኑ፣ አመጻ በህይወታቸው የሚገለጥ ከሆነ... አምነዋል? እምነት ምንድነው? ዝም ብሎ የአእምሮ ኮንቪክሽን (conviction) ብቻ ነው? ለክርስቶስ መገዛት ካልሆነ፣ መታዘዝ ካልሆነ ትርጉም የለውም። ኢየሱስ ክርስቶስን "ጌታዬ" ስል እኔ "ባሪያ ነኝ" እያልኩ ነው። "እታዘዝሃለሁ፣ እሰማሃለሁ" እያልኩ ነው። "እምቢ አልልም" እያልኩ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ የሚለው እምነት ወደ መታዘዝ መምጣት አለበት። ከእምነት ወደሚገኝ መታዘዝ፣ አለበለዚያ "ኢየሱስ ጌታ ነው" ማለት መፈክር ብቻ ነው። "አምኛለሁ" ማለት መፈክር ብቻ ነው። "በማመኔ ብቻ" ብሎ መዘመር መዝሙር ብቻ ነው፤ መታዘዝ ከሌለበት ህይወት አይደለም። እያንዳንዳችን "መታዘዝ በህይወቴ አለ ወይ?" ብለን ልንመረምር ይገባል።

ምስባከ ጳውሎስ - Paul's Pulpit

10/04/2026

"The enemy wants you to define yourself by your scars, but Jesus wants you to define yourself by His scars.”
Joby Martin

የአንድ መሪ "ብቸኝነት" እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ህልውናበብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታየው ትልቁ ስጋት የአንድ ሰው ብቻ "ኮከብ" መሆን ነው።ፓስተሩ ወይም መሪው ብቻውን ሰባኪ፣...
09/04/2026

የአንድ መሪ "ብቸኝነት" እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ህልውና

በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታየው ትልቁ ስጋት የአንድ ሰው ብቻ "ኮከብ" መሆን ነው።
ፓስተሩ ወይም መሪው ብቻውን ሰባኪ፣ ብቻውን አስተማሪ፣ ብቻውን መካሪና አስተዳዳሪ በሚሆንበት ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ተቋም መሆኗ ቀርቶ የግለሰብ ተገዥ ትመስላለች።
ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መፍረስ ዋነኛው መንስኤ ነው።

1. ብቻህን ልታደርገው አትችልም
በዘጸአት 18 ላይ የሙሴ አማች ዮቶር የሰጠው ምክር ለዛሬዎቹ መሪዎች ትልቅ ደወል ነው። ሙሴ ቀኑን ሙሉ ህዝቡን ለመዳኘት ብቻውን ይቆም ነበር። ዮቶር ግን እንዲህ አለው፦ "የምታደርገው ነገር መልካም አይደለም፤ አንተም ከአንተ ጋር ያለው ይህ ሕዝብ ፈጽሞ ትዝላላችሁ..."
አንድ መሪ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ሲይዝ ሁለት አደጋዎች ይከሰታሉ፦
• የመሪው መዛል (Burnout)፦ መሪው በሰውነቱ ይደክማል፣ በመንፈሱ ይዝላል፣ በመጨረሻም አገልግሎቱን እስከመጥላት ይደርሳል።
• የህዝቡ መንፈሳዊ ድንቁርና፦ ምዕመናኑ ሁልጊዜ ተቀባይ እንጂ ሰጪ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። የሌሎች ስጦታ ታፍኖ ሲቀር ቤተ ክርስቲያን በአንድ እግሯ እንደምትሄድ አካል ትሆናለች።

2. የመሪነት ትርጉም "መስራት" ሳይሆን "ማሰራት" ነው
መጽሐፍ ቅዱስ መሪዎች የተሰጡት ለምንድነው? መልሱ በኤፌሶን 4:12 ላይ አለ፦ "ለቅዱሳን አገልግሎት ሥራ... እንዲያዘጋጁ።"
መሪ ሆይ፣ ያንተ ትልቁ ስኬት ራስህ በሚገባ መስበክህ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ከአንተ የተሻለ የሚሰብኩ፣ የሚያስተምሩና የሚያስተዳድሩ ሰዎችን ማፍራት ስትችል ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመራር "ተተኪን" ማእከል ያደረገ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን የመጣው ለብቻው ሆኖ ሳይሆን፣ 12 ሰዎችን አሰልጥኖ ስልጣን በመስጠት ነው።

3. "ብቸኛ ሰባኪ" የመሆን አደጋ
ሁልጊዜ ሰባኪው አንተ ብቻ ከሆንክ፦
• የእውቀት ውስንነት ይፈጠራል፦ ህዝቡ የአንድን ሰው እይታ ብቻ እንዲሰማ ይገደዳል።
• ተጠያቂነት ይጠፋል፦ ማንም የማይገስጽህና የማይመክርህ ከሆነ የመውደቅ ዕድልህ ሰፊ ይሆናል።
• ውድቀትህ ውድቀታቸው ይሆናል፦ አንተ በሆነ ምክንያት ብትታመም ወይም ብትወድቅ፣ አጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ አብራ ትወድቃለች። ይህ "የመጽሐፍ ቅዱሳዊ አጥቢያ" ባህሪ አይደለም።

4. መፍትሄው፦ የአገልግሎት ቢሮዎችን ማንቃት
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንጂ የአንድ ሰው ድርጅት አይደለችም። በአጥቢያ ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ስጦታዎች (ጸጋዎች) ለይቶ ማውጣትና ስልጣን ማካፈል (Delegation) ያስፈልጋል።
• አስተማሪዎችን ማሳደግ፦ መሪው በሌለበት ጥልቅ ትምህርት የሚሰጡ።
• ዲያቆናትንና መጋቢዎችን ማፍራት፦ የአስተዳደርና የህዝብ እንክብካቤ ስራን የሚረከቡ።
• ወንጌላውያንን ማሰማራት፦ የቤተ ክርስቲያኒቱን አድማስ የሚያሰፉ።

ማጠቃለያ
የቤተ ክርስቲያን ህልውና የሚወሰነው በመሪው ጥንካሬ ሳይሆን፣ መሪው ባፈራቸው ሰዎች ብዛትና ጥራት ነው። መሪ ሆይ! ዛሬ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ "እኔ ዛሬ በድንገት ባልኖር፣ ይህች ቤተ ክርስቲያን ትቀጥላለች ወይስ ትፈርሳለች?" መልሱ "ትፈርሳለች" ከሆነ፣ የአመራር
ዘይቤህን በአስቸኳይ መቀየር አለብህ።

የእግዚአብሔር መንጋ በአንተ ትከሻ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በክርስቶስ አካላት ሁሉ ትከሻ ላይ እንዲያርፍ አድርግ። ያኔ አገልግሎቱ ዘላቂና ፍሬያማ ይሆናል።

Yohannes Fituma

የመስቀል ሞት ከሌሎች አገዳደሎች የተለየ ነው። ለምሳሌ፣ ተሰይፎ መገደል አስከፊነቱ ያለው የሟቹ ጭንቅላት፣ አንዳንዴም እጁ ተቈርጦ ለትእይንት መቅረቡ ላይ ነው። (የመጥምቁ ዮሐንስን አሟሟት ...
09/04/2026

የመስቀል ሞት ከሌሎች አገዳደሎች የተለየ ነው። ለምሳሌ፣ ተሰይፎ መገደል አስከፊነቱ ያለው የሟቹ ጭንቅላት፣ አንዳንዴም እጁ ተቈርጦ ለትእይንት መቅረቡ ላይ ነው። (የመጥምቁ ዮሐንስን አሟሟት ያስታውሷል!) በመስቀል የሚገደል ሰው ግን ከነሕይወቱ ነው ለትእይንት የሚቀርበው። ምናልባት ከመስቀል ሞት ጋር የሚወዳደረው ለአራዊት ተወርውሮ መሰጠት ነው። ነገር ግን የመስቀል ሞት የትም ሊፈጸም ሲችል፣ ለአራዊት መወርወር ግን ከተማን ይፈልጋል። በመስቀል መግደል ሌላው ተመራጭነቱ፣ ሰዎችን ለተራዘመና ለከፋ ሥቃይ መዳረጉ ነው።

በወቅቱ የተለያዩ የአሰቃቀል መንገዶች ነበሩ። በአብዛኛው ግን፣ የሚሰቀለውን ሰው መስቀሉ ላይ ማሰርና መቸንከር የተለመደ ነበር። ይህም ዋና ዋና ውስጣዊ ብልቶችን ለጕዳት ስለማይዳርግ ሞቱን ያራዝመዋል። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ፣ የተሰቀለው ሰው ነፍሱ ሳትወጣ ለቀናት እዚያው የሚቈይበት ሁኔታ ይኖራል። ብርቱ አካላዊ ሥቃይን፣ የሕዝብን ስድብና ውርደትን፣ የቀኑን ሐሩርና የሌሊቱን ቁር ችሎ ስቁሉ ሰው እንደ ተንጠለጠለ ይቈያል። ዝንቦች፣ የተለያዩ ነፍሳትና ተባዮች የተሰቀለውን ሰው የተጋጋጠ ጀርባ፣ የቈሳሰሉ እጆችና እግሮችን መውረርና መንከስ ይጀምራሉ። የመስቀል ሰለባ የሆነው ሰው እጅ እግሩ ተወጥሮ ስለሚቸነከር፣ ይህ ሁሉ ሥቃይ ሲደርስበት ምንም ዐይነት ፋታ ማግኛ መንገድ አይኖረውም። ዕርቃንን የመሆን ዕፍረትም አለ። የተሰቀለ ሰው ፍጹም ረዳት የለሽ የመሆን ስሜት ይውጠዋል።

እኛ በቀላሉ የምንተገብረው የመተንፈስ ተግባር እንኳ በመስቀል ላይ ላሉ ሰዎች እጅግ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ፣ እንዲሁም ጣርንና ሥቃይን የሚጨምር ሂደት ይሆናል። በእጃቸው አንጓ ላይ የተንጠለጠለው የሰውነታቸው ክብደት፣ ለመተንፈስ የሚያስችሉ ጡንቻዎቻቸውን ያደክሟቸዋል። ስለዚህ አየር ወደ ውስጥ ለመሳብ በእግሮቻቸው ወደ ታች አጥብቀው በመርገጥ ወይም እጆቻቸውን በመጠቀም ወደ ላይ መንጠራራታቸው ግድ ይሆናል። ይህ ደግሞ የእግሮቻቸውንና የእጆቻቸውን ቀዳዳዎች ይበልጥ በማስፋት ሥቃያቸውን ያባብሰዋል።

በእጆቻቸው ላይ የተሰካው ምስማር ነርቮቻቸውን በጣጥሶና ጨቍኖ ስለሚይዛቸው ጥቃቅኑ እንቅስቃሴ ሳይቀር ሥቃይን ይፈጥራል፤ በቃላት የማይገለጽ እጅግ ከባድ ሥቃይ። (እንዲህ ዐይነቱ ሕመም በሕክምና ስሙ Causalgia ይባላል። በ1ኛው የዓለም ጦርነት በፈንጂ ፍንጣሪ (shrapnel) እጃቸውን የተመቱ ወታደሮች ‘ሞርፊን’ (morphine) እንኳ የማያስታግሠው ሕመም ነበራቸው።) በዚህም ላይ ከሙቀቱ፣ ከድካሙና ከደም መፍሰሱ የተነሣ እጅግ ለከፋ የውሃ ጥማት ይዳረጋሉ። የጡንቻዎቻቸውን መኮማተርና መዛል፣ የነርቮቻቸውን መበጣጠስ፣ እንዲሁም የተተለተለው ጀርባቸው ከመስቀሉ ዕንጨት ጋር ሲፋተግ የሚፈጥረውን ሕመም ሁሉ በአንድነት ማሰብ ያስፈልጋል። ከታች ሆነው የሚሳደቡና ምራቅ የሚተፉባቸው ሰዎችም ይኖራሉ።

በዚህ ወቅት ሞት በረከት ነው፤ ግና ቶሎ አይመጣም። የሚሰቀሉ ሰዎች በአብዛኛው በመስቀላቸው ላይ ከ3 ወይም ከ4 ሰዓታት እስከ 3 ወይም 4 ቀናት ድረስ በሕይወት ሊቈዩ ይችላሉ። ነፍስ ያላቸው ሬሶች ሆነው ብዙ ከቈዩ በኋላ ነው የሞትን በረከት የሚያገኙት። ስቅለት፣ በተቻለ መጠን የስቁላንን ሥቃይ ማብዣና ማራዘሚያ መንገድ ነው። ከየቱም ዐይነት ዘመናዊ የሞት ፍርድ ማስፈጸሚያ መንገድ ጋር ሲተያይ ዘመናዊዎቹ “ሐዘኔታ የሞላባቸው” ናቸው።

የተሰቀለው ገጽ 32-33።
ምስባከ ጳውሎስ - Paul's Pulpit

08/04/2026

ማኅበራዊ ሚዲያ, መረጃ እና የክርስቲያን አእምሮ : Equip Podcast EP 03

Address

Dembel City Center 12th Floor
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Semayawi Thought posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Semayawi Thought:

Share