Emanuel/ አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው

Emanuel/ አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው Apocalypse አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅ እና የተፈራ አምላክ በመካከልህ ነው እና ከእርሱ የተነሳ አትደንግጥ ፡፡ ዘዳ 7፡21

16/08/2026

...
በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የዝማሬ ታሪክ ቀደምት ከሆኑት ዘማሪያን መካከል የሆኑ፣ በአገልግሎታቸውም ለብዙዎቻችን መፅናናት እና መታነፅ አድርጎ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው የተወደዱ አገልጋዮች ናቸው መሰረት ፅጌ እና እንዳልካቸው ኪዳነወልድ። ከዚህም በፊት ሁለት የዝማሬ አልበሞችን ወደ እኛ ያደረሱት ብዙዎቻችንም ዝናህ የገነነው፣ የአዲስ ኪዳን በግ በሚሉት እና በሌሎችም በርካታ ዝማሬዎቻቸው የምናውቃቸው መሰረት ፅጌ እና እንዳልካቸው ኪዳነወልድ አሁን ደግሞ ጌታ ረድቷቸው ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሁም ለቅዱሳን መታነፅ ይሆን ዘንድ አንተ አለት የተሰኘ በብዙ የደከሙበትን ቁጥር 3 የዝማሬ አልበማቸውን ወደኛ ይዘውልን መጥተዋል። አልበሙ በቅርቡ የሚለቀቅ ሲሆን ለብዙዎቻችን መታነፅ እና ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ምክንያት ይሆንልናል።
ዝማሬዎቹንም በራሳቸው የyoutube ቻናል መሰረት ጽጌ እና እንዳልካቸው ኪዳነወልድ ያገኙታል።
እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ ከዚህ በላይ ያስፋ...

22/04/2026

"የአምላኬን ቤት አልተውም"

"የአምላካችንን ቤት ከቶ አንተውም" ነህ10:39
​
​ክርስቲያን መሆን ማለት በአበባ በተጎዘጎዘ መንገድ ላይ መጓዝ ወይም ሁሉም ነገር የተመቻቸ አልጋ በአልጋ የሆነ ነው ማለት አይደለም። በተለይ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ለታላቅ ዓላማ ስንነሳ፣ አገልግሎታችንን እንድናቆም፣ ተስፋ እንድንቆርጥና ከቤቱ እንድንርቅ የሚፈልጉ የውድቀት ተጠባባቂዎች በዙሪያችን ይበቅላሉ። ዛሬ የምንማረው እነዚህን ተግዳሮቶች አልፎ፣ ልብን በእግዚአብሔር አበርትቶ እስከ ፍጻሜው ስለመጽናት ነው።
​1. ከድንጋይ የከበደው አንደበት
​ጥንት ሰዎችን በድንጋይ ይወግሩ ነበር፤ ዛሬ ግን ወገራው መልክ ቀይሯል። ዛሬ የሚወገረው በድንጋይ ሳይሆን በአሉባልታ፣ በንቀት፣ በማሸማቀቅና በሐሜት በአሰመሳዮች ነው።
አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት
🗣ታላቅ ሥራ ለመሥራት ስትነሳ መጀመሪያ ከሚገጥምህ ተግዳሮት አንዱ “የምላስ ጦር” ነው።
​
​1. ነህምያ (የውጭ ትችትና የአሽሙር ጦር ገጥሞት ነበር)
​ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለመገንባት ሲነሳ፣ ጠላቶቹ ሰንባላጥና ጦቢያ የድንጋይ ውርወራ ሳይሆን የቃላት ውርወራ ነበር የጀመሩት።
​አሽሙሩ፦ “የሚገነቡትን ቅጥር ቀበሮ ቢወጣበት የድንጋዩን ግንብ ያፈርሰዋል” አሉት (ነህምያ 4:3)። ማለትም “ሥራችሁ ደካማ ነው ዋጋ የለውም” ብለው አፌዙበት።
​ተግዳሮቱ፦ ወሬው የአይሁድን ልብ እንዲዝልና “አንችልም” እንዲሉ ለማድረግ የታቀደ ነበር።
​ነገር ግን ነህምያ ለአሽሙራቸው መልስ አልሰጠም ከቁብ ሳይቆጥረው። ይልቁንም “እኔ ታላቅ ሥራ እሰራለሁ ፣ ወደ እናንተ መውረድ አልችልም” በማለት በትኩረት ሥራውን ቀጠለ።
​2. ከትዳር አጋር፦ ሜልኮል (የዳዊት የቅርብ ሰው ነች )
​አንዳንድ ጊዜ የከበደው ትችት የሚመጣው ከሩቅ ጠላት ሳይሆን አብሮ ካለ የቅርብ ሰው ነው። ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ሲገባ በደስታ በጌታ ፊት ሲዘል፣ ሚስቱ ሜልኮል በንቀት ተመለከተችው።
​፦ “የእስራኤል ንጉሥ ዛሬ እንዴት የተከበረ!” በማለት በአሽሙር ተሳደበችው (2 ሳሙኤል 6:20)። ክብሩን ዝቅ ለማድረግና እንዳያመልክ ለማሸማቀቅ ሞከረች።
​ ዳዊት ግን “ከእግዚአብሔር ፊት ገና ዝቅ ወይም የተናቅሁ እሆናለሁ በአይንሽም እዋረዳለሁ... ” በማለት ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደሚኖር አረጋገጠ። የሰው ንቀት ለእግዚአብሔርን ያለንን ክብር እና የቅንነት አገልግሎት እንዳይጋርድብን ዳዊት ምሳሌያችን ነው።

​3. ከታዋቂ ግለሰቦች፦ ዊልያም ኬሪ (William Carey)
​የዘመናዊ ሚስዮናውያን አባት የሚባለው ዊልያም ኬሪ ወደ ሕንድ ሄዶ ወንጌልን ለመስበክ ሲነሳ፣ የገጠመው ከአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጭምር የነበረ ትችት ነው።
​በአንድ ስብሰባ ላይ ስለ ወንጌል ተልዕኮ ሲናገር፣ አንዱ መሪ ተነስቶ “ወጣት፣ ተቀመጥ! እግዚአብሔር አረማውያንን መለወጥ ከፈለገ አንተንም እኛንም ሳይጠይቅ ያደርገዋል” በማለት አሸማቀቀው።
​🗣ኬሪ ግን በዚህ የንቀት ቃል አልቆመም። "ታላቅ ነገርን ከእግዚአብሔር ጠብቅ፣ ታላቅ ነገርን ለእግዚአብሔር አድርግ" በሚለው መርህ ሕንድ ሄዶ መጽሐፍ ቅዱስን በብዙ ቋንቋዎች ተረጎመ።

​4. ዳዊትና ወንድሙ ኤልያብ
​ዳዊት ጎልያድን ሊጋጠም ወደ ሰልፍ ቦታው ሲመጣ፣ ትልቁ ወንድሙ ኤልያብ በንዴት ተቆጣው።
ዳዊትና ኤልያብ፦ የቅርብ ሰዎች ንቀትና ስም የማጥፋት ዘመቻ
​(1 ሳሙኤል 17:28-30)
ዳዊት ጎልያድን ለመውጋት በቆራጥነት ሲነሳ፣ የመጀመሪያው እንቅፋት የሆነው የገዛ ወንድሙ ኤልያብ ነው። ኤልያብ ዳዊትን ለመግታት የተጠቀመባቸው ቃላት፦
​ኃላፊነት የጎደለው ነህ፦ “እነዚያን ጥቂቶች በጎች በማን ዘንድ ተውሃቸው?” (አነስተኛ ግምት መስጠት)።
​ትዕቢተኛ ነህ፦ “ኩራትህንና የልብህን ክፋት እኔ አውቃለሁ” (ያልሆነ ስም መለጠፍ)።
​✍️ትልቅ ራዕይ ይዘህ ስትነሳ የቅርብ ሰዎችህ “ምን አቅም አለህ?” ወይም “ለዝና ብለህ ነው” ሊሉህ ይችላሉ። ዳዊት ግን ለወንድሙ መልስ በመስጠት ጊዜውን አላጠፋም፤ “ፊቱን ወደ ሌላ ሰው አዞረ” ይላል። ዛሬም አንተን ለሚያሸማቅቁህ ሰዎች መስጠት ያለብህ ትልቁ ምላሽ ትኩረት አለመስጠት ነው።

​ዳዊት አንዳች በቃሉ ሳይናገር እልፎ ብሎ ፊቱን ወደ ሌላ ሰው አዞረ። ከሚተቹን ሰዎች ጋር መጨቃጨቅ ጊዜን መግደል ነው፤ ፊትን ወደ አላማ ማዞር ግን አዋቂነት ነው።

​2. ነህምያና ጠላቶቹ፦ አሽሙርና የስነ-ልቦና ጦርነት
​(ነህምያ 4:1-4)
ነህምያ የፈረሰውን ቅጥር ለመሥራት ሲነሳ ሰንባላጥና ጦቢያ በሦስት ደረጃ የተከፈለ የምላስ ውርወራ አደረጉበት፦
🗣​ማንቆለጳሰስ (Belittling)፦ “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን ያደርጋሉ?”
🗣​ተስፋ ማስቆረጥ፦ “በአንድ ቀን ይጨርሳሉን?”
🗣​ማሾፍ (Mockery)፦ “ቀበሮ ቢወጣበት ግንቡን ያፈርሰዋል”።
​✍️ ጠላቶችህ በአገልግሎትህ ላይ “ቀበሮ ቢወጣበት ይፈርሳል” ይሉ ይሆናል። ስራህን እንደ ቀላልና እንደ ደካማ ይቆጥሩታል። ነህምያ ግን “አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ” ብሎ ወደ ጸሎት ሄደ። በሰዎች አሽሙር ስትገፋ፣ ፊትህን ወደ ሰማይ መልስ እንጂ አካፋህን አትጣል።

​3. ኢያሱና ካሌብ፦ የብዙኃኑ አሉባልታና ተቃውሞ

​(ዘኁልቁ 14:1-10)
እነዚህ ሁለት ሰዎች “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና ምድሪቱን እንውረሳለን” ብለው በእምነት ሲናገሩ፣ መላው ማህበር ምን ለማድረግ እንደሞከረ አስተውሉ። “ማህበሩ ሁሉ በድንጋይ ሊወግሯቸው ተናገሩ” ይላል።
​ አብዛኛው ሰው በክፋት ሲተማማና አንተ ብቻህን በእምነት ስትቆም፣ የብዙኃኑ ድምፅ ሊያሸማቅቅህ ይችላል።
​፦ በአገልግሎትህ ውስጥ ብዙ ሰዎች ቢቃወሙህም፣ አንተ ግን በእውነት ላይ ቁም፤ በዚያ ሰዓት “የእግዚአብሔር ክብር በደመና ተገለጠ” ይላል። ሰዎችን ለመምሰል ብለን አቋማህን አትቀይር፤ የእግዚአብሔር ክብር በአንተ ላይ የሚገለጠው በብቸኝነት ለእውነት ስትቆም ነው።
​
🗣​እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩት አንድ እውነት አለ፦ "ድንጋይ የሚወረወረው ፍሬ ባለው ዛፍ ላይ ብቻ ነው።" ማንም የማይተችህ ከሆነ፣ ምናልባት ሰይጣን የሚፈራው ሥራ እየሠራህ ላይሆን ይችላል። ትችት የአገልግሎትህ “ባጅ” (Badge) እንደሆነ ቁጠረው።
​
​1. ዳዊትና የእግዚአብሔር ጋሻነት

​ጠላት በዙሪያችን ሲከብ፣ የሚያጽናናን ሰው ሲጠፋና የቅርብ የምንላቸው ሰዎች እንኳ ሊወግሩን ሲነሱ የምናገኘው ብርታት ከአምላካችን ነው።
ዳዊት በጺቅላግ ህዝቡ ሊወግሩት ሲሉ "ልቡን በአምላኩ በእግዚአብሔር አበረታ" (1 ሳሙኤል 30:6)።
​ እግዚአብሔር ለአብርሃም "እኔ ላንተ ጋሻህ ነኝ" አለው (ዘፍጥረት 15:1)። ጋሻ ከጠላት የሚሰነዘርን ፍላጻ እንደሚመክት ሁሉ፣ እግዚአብሔርም ከሚዘንብብህ ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ይጠብቅሃል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፤ እርሱ ግን ከመካከላቸው አልፎ ሄደ (ዮሐንስ 8:59)።
​ ሰዎች በወሬና በንቀት ሊወግሩህ ሲሉ፣ ልክ እንደ ጌታህ "አልፈህ ሂድ"። ለሚሰነዘርብህ አሉባልታ ሁሉ ምላሽ መስጠት የለብህም፤ ዝምታና ወደ ፊት መራመድ ከሁሉ በላይ ትልቅ ምላሽ ነው።

​🗣ስትወደድ የሚጠላህ፣ ስትወድቅ ደስ የሚለው "አስመሳይ ማህበር" ቢበዛም፣ አንተ ግን በሰው ሳይሆን በጋሻህ በእግዚአብሔር ተመካ።

​3. ፈውስ በመገረፉ ቁስል ይሆንልሀል
​ሰዎች በአንደበታቸው ሲገርፉህና ልብህን ሲያቆስሉት፣ ፈውሱ የሚገኘው በቆሰለው ጌታ ዘንድ ነው።
​"እርሱም ስለ መተላለፋችን ቆሰለ... በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን" (ኢሳይያስ 53:5)።
ሰዎች ካቆሰሉህ፣ ጌታ በቁስሉ ይፈውስሃል። ሰዎች ቢተዉህም፣ እርሱ ግን "አልተውህም ከቶም አልጥልህም" ብሎሃል።

​4. የዘመናችንን ተግዳሮት ማሸነፊያ መንገዶች
​ይህንን ሩጫ በድል ለመጨረስ የሚከተሉትን አራት ነጥቦች እንደ መጠቀም አስፈላጊ ነው፦

🗣​ጸሎትና ህብረትን አለማቋረጥ፦ 🗣መነጠል ለጥቃት ያጋልጣል። 🗣በቤቱ ጸንተህ ተገኝ።
🗣​በሉዓላዊነቱ መጽናት ይሁንልህ፦ 🗣"ሁሉን የሚገዛው ጌታ ከእኔ ጋር ነው" ብለህ እመን።
🗣​ቅንነትን አትጣ፦ ሰዎች ክፉ ስለሆኑ አንተ ክፉ አትሁን። የልብ ቅንነት በረከትን የመጣል የቅኖች ትውልድ ይባረካል።
🗣​ጌታን እያዩ መሮጥ "የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን በመመልከት..." (ዕብራውያን 12:2)። ትኩረትህ አገልግሎቱ ላይ እንጂ አገልጋዩ ላይ አይሁን።

🗣እነዚህ ሁሉ ሰዎች ቢሰሙአቸው ኖሮ ዛሬ ታሪካቸው አይጻፍም ነበር።
✍️​ዳዊት ወንድሙን ቢሰማ ጎልያድን አይጥልም ነበር።
✍️​ነህምያ አሽሙሩን ቢያዳምጥ የኢየሩሳሌም ቅጥር አይታደስም ነበር።
✍️​ኢያሱና ካሌብ ድንጋዩን ቢፈሩ ርስታቸውን አይወርሱም ነበር።
​

​ በመጨረሻም
​የተጠራህበት ዓላማ ከሰዎች ወሬ ይበልጣል። "የአምላኬን ቤት አልተውም" ስንል፣ ለሰዎች ብለን ሳይሆን ለጠራን ጌታ ታማኝ ሆነን መቆማችንን እያወጅን ነው።
ዛሬ ላንተ የሚመጣው የምላስ ጦር የአገልግሎትህ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም። ጋሻህ እግዚአብሔር ነውና “የአምላኬን ቤት አልተውም” ብለህ ሩጫህን ቀጥል!

🗣 ድንጋይ የሚወረውሩ ሁሉ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔር ቃል እና አማኞቹ በክርስቶስ ለዘለዓለም እንኖራለን።

​ፓ/ር ኤርምያስ ጌታቸው

02/04/2026

ርዕስ፦
በዘመናት ሁሉ ላይ የነገሠው አምላክ

"ቀኑ የአንተ ነው፥ ሌሊቱም የአንተ ነው፤" መዝ74:16

​ይህ መልእክት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡ በቀኑ ብርሃን ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር ማየት እና በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥበቃ መታመን።

​1. ቀኑ ያንተ ነው፡ የድልና የተስፋ ብርሃን
​ቀን የሥራ፣ የእንቅስቃሴ፣ የድልና የለውጥ ምልክት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የብርሃን አባት እንደሆነ ይነግረናል።
​የለውጥና የተስፋ ምንጭ፡ በሕይወታችን ነገሮች ሲሳኩ፣ መንገዶች ሲከፈቱና በረከት ሲፈስ ያ "ቀን" ነው። ያንን ቀን የሰጠን እርሱ ስለሆነ ትዕቢት ሳይሆን ምስጋና ይገባዋል።

​ "እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው?" (መዝሙር 27:1)።
​ምሳሌ፡ እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው በቀን በደመና ዓምድ ሲመራቸው፣ ያ ብርሃን የእግዚአብሔር መገኘት ማረጋገጫ ነበረ።

በሕይወትህ ስኬት ሲመጣ "በጉልበቴ መጣ" አትበል፤ ቀኑ የእርሱ ነውና።

​2. ሌሊቱም ያንተ ነው፡ በጨለማ ውስጥ ያለ ሉዓላዊነትም ቢሆን የእግዚአብሔር ነው
​ሰዎች ብዙ ጊዜ ሌሊትን ይፈራሉ። ሌሊት የጭንቀት፣ የለቅሶ፣ የጥርጥርና የጥቃት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ነገር ግን መዝሙረኛው "ሌሊቱም ያንተ ነው" ይላል።

​ ጠላት ጨለማን ሊጠቀምበት ቢፈልግም፣ ጨለማው ግን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።

እግዚአብሔር በብርሃን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጨለማውም ላይ ንጉሥ ነው።

​ "በእውኑ ጨለማ ይሸፍነኛል ብል፥ ሌሊቱ በዙሪያዬ ብርሃን ይሆናል፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ያበራልና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።" (መዝሙር 139:11-12)።

ለ​ምሳሌ፡ ዮናስ በአሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ (በጥልቅ ጨለማ) በነበረበት ወቅት፣ ሌሊቱ የእግዚአብሔር ነበረ። እግዚአብሔር እዚያም ነበረ፤ ጠበቀው፣ አወጣውም።

​3. አስታውሱ ሁሌም በድቅድቁ ጨለማ ተኝተን የማይተኛው ጠባቂ አስቡት
​ሌሊቱን የምናሳልፈው ተኝተን ነው።
መተኛት የፍጡር ድካምና አቅም ማጣት መገለጫ ነው። ስንተኛ ራሳችንን መጠበቅ አንችልም፤ ነገር ግን ስንነቃ ዓለም እንዳለች ናት አልጠፋችም፣ እኛም በሕይወት አለን።

​ያለ እረፍት የሚጠብቀን፡ እኛ ስንተኛ እርሱ ግን አይተኛም፡፡ "እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።" (መዝሙር 121:4)።

​ አንድ ሕፃን በአባቱ እቅፍ ውስጥ ሲተኛ ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለበት ሁሉ፣ እኛም በሕይወት ማዕበልና ሌሊት ውስጥ "እርሱ ንቁ ጠባቂያችን ስለሆነ " በሉአላዊነቱ እቅፍ ማረፍ አለብን።

​4. ለቅሶ በሌሊት ደስታ በጥዋት
​ሌሊቱ የቱንም ያህል ቢረዝም ጥዋት መምጣቱ አይቀርም።

ይህ ተፈጥሮአዊ ዑደት የእግዚአብሔር የታማኝነት ቃል ኪዳን ነው።
​ስለዚህ በተስፋ ደስ ይበላችሁ ለቅሶ ለአንድ ሌሊት ሊቆይ ይችላል፣ ግን ደስታ በጥዋት ይመጣል። ምክንያቱም ያ ጥዋት የሚመጣው ሌሊቱን የሚቆጣጠረው አምላክ ስላለ ነው።

"ለቅሶ በሌሊት ይመጣል፥ በጥዋት ግን ደስታ ይሆናል።" (መዝሙር 30:5)።

​ ስለዚህ በህልውናው ውስጥ መኖር
​ይህንን እውነት መረዳት በሁለት መንገድ ይጠቅመናል፡

1:​ከፍርሃት ነፃ ያወጣናል፡🙏 "ሌሊቱም የእርሱ ነው" ካልን፣ በክፉ ቀን አንደነግጥም።
​ትሕትናን ያስተምረናል🙏

2:ቀኑ የእርሱ ነው" ካልን፣ በሰላም ቀን አንታበይም።🙏

​ስለዚህ እግዚአብሔር የሌለበት ወቅት፣ የማይገኝበት ሰዓት፣ የማይገዛው ስፍራ የለም። በብርሃኑም በሰላም እንመላለስ ፤ ሲጨልም በህልውናው ጥላ ስር በእምነት እናሳልፍ ። ሲነጋም ሲመሽም የማይለወጠው ጌታ ከእኛ ጋር ነው።
​ተባረኩ! ኤርምያስ

30/03/2026
10/03/2026

ስብከት ስለ እግዚአብሄር ቅድስና፡ የቅድስና መርሆዎች

ቅድስና ማለት ምን ማለት ነው? ቅድስናን በአጭር ቃል ለማስቀመጥ ለእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው። ቅድስና የክርስትና እምነታችን አስፈላጊ አካል ነው። የተጠራነው በቅድስና ህይወት እየኖርን እግዚአብሔር ደስ በማሰኘት እንድንኖር ነው ።

ቅድስና ምንድን ነው?

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው - የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ። ይህ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፣ እሱን ማየት አለመቻላችን እራሱን የገለጠ እውነት ከራሳችን የተለየ መሆኑን ያሳያል

በተጨማሪም ኢሳ 6:3 እና ራእይ 4:8፣ የኢሳይያስ ምላሽ ንጽህና/ እና ቅዱስ የሚለውን ሐሳብ ያገናኛል

ቅድስና ከሰባቱ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ ነው (ገላ 5፡22)። ቅድስና ሃይማኖታዊ ጽንሰ-ሐሳብ ብቻ አይደለም; የሞራል ብቃትም ነው። በሌላ አነጋገር ቅድስና ከሌሎች የሚለየን ነው። ሰዎችን በተለይም ከኛ ደካማ ለሆኑት አርያ እና ምሳሌ በመሆን ጌታን ምናከብርበት መንገድ ነው።

1. ጴጥሮስ ስለ የቅድስና መርሆዎች እንዲህ ይላል 1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።
¹⁴ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።
¹⁵-¹⁶ ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።
¹⁷ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ።
¹⁸-¹⁹ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።

ቅድስናን የሚያስፈልግበት ብዙ ምክንያቶች አሉ።
በመጀመሪያ፣ ቅድስና ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል ይረዳናል።
ሁለተኛ፣ ቅድስና እንደ ክርስቲያኖች እንድንኖር ይረዳናል።
ሦስተኛ፣ ቅድስና አገልግሎታችንን በትጋት እንድናገለግል ይረዳናል።
አራተኛ፣ ቅድስና እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን እንድንወደው ይረዳናል።
አምስተኛ፣ ቅድስና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንድንታዘዝ ይረዳናል።
ስድስተኛ፣ ቅድስና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።
ሰባተኛ፣ ቅድስና ፈተናን እንድናሸንፍ ይረዳናል።

ቅድስና ምን ይመስላል?

ቅዱሳን እንድትሆኑ እዘዙ - እናንተ ደግሞ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ዘሌ 11፡44፣ 19፡2፣ 20፡7 ተብሎ ተጽፎአል።

ቅድስና ማለት ለእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው ስንል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በማክበር መሄድ ማለት ነው። ከምንም ነገር በላይ እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ነው። ሌሎችን ማገልገል ማለት ነው። በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አለመሥራት ማለት ነው። መልካም ሥራዎችን መሥራት ማለት ነው። ንፁህ አእምሮ መኖር ማለት ነው።

2. በዚህ
1ኛ ጴጥሮስ 1፡14-17, 22 ጴጥሮስ ኑሮአችንን ሁሉ በቅድስና ለመኖር ፕሮግራምድ እንድናደርግ ይመክረናል
ስለዚህ በአለም በሚያታልሉ ነገሮች አትታለሉ።

የበለጠ ቅዱስ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

የበለጠ ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት ቅዱስናን በብርቱ መፈለግም መሻትም ሊኖረን ይገባል
አዎ እፈልጋለሁ መሻትም አለኝ የምትል ከሆነ ፣ ልታደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ። መጀመሪያ አዘውትረህ ጸልይ።
ሁለተኛ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ። ሦስተኛ፣ ከሌሎች አማኞች ጋር ጊዜ አሳልፍ ወይም የቅዱሳን ህብረት ይኑርህ ።
አራተኛ, ሌሎችን በፍቅር ከልብህ አገልግል አምስተኛ፣ ንጽሕና ሕይወትን ተለማመድ በድርጊትም በሀሳብም በቃልም።
ስድስተኛ፡ እግዚአብሔርን ውደድ።
ሰባተኛ, ሰዎችን ውደድ.
ስምንተኛ, ሌሎችን ይቅር በል
ዘጠነኛ፣ በትህትና ተመላለሱ።
አሁንም ተባረኩ

09/02/2026

⚠️ "ተሰሩ"

የሕያው እግዚአብሔር ማደሪያ ቤተመቅደስ
​የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን እኛ ዝም ብለን የመጣን ፍጥረታት ሳንሆን፣ በታላቁ አርክቴክት በእግዚአብሔር እጅ በጥበብ የተሠራን ነን። ዛሬ የምናየው እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ለመኖር እንዴት እንደሚሠራንና እኛስ እንዴት ለክብሩ መኖሪያ እንደምንሆን ነው።
🗣​1. የእግዚአብሔር የእጅ ሥራ ነን
​እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት በቃል ብቻ "ይሁን" ብሎ አይደለም፤ ነገር ግን በገዛ እጆቹ አበጅቶና እስትንፋሱን እጅግ ቅርብ በሆነ ሁኔታ እፍ ብሎበት ነው።
​በአምሳሉ መፈጠር፦ "እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው" (ዘፍጥረት 1፥27). ይህ ማለት እኛ የእርሱን ባህሪ፣ ቅድስናና ፍቅር እንድንጋራ ታቅደን ተሠራን።
​የእጅ ሥራው መሆን፦ "እኛ ፍጥረቱ (የእጅ ሥራው) ነንና" (ኤፌሶን 2፥10). እግዚአብሔር እኛን እንደ ሸክላ ሠሪ በጥንቃቄ ቀርጾናል።
🗣​2. እግዚአብሔር የት ይኖራል?
​እግዚአብሔር በሰው እጅ በተሠራ ሕንፃ ውስጥ ተወስኖ መኖርን አይፈቅድም። ሰሎሞን ቤተመቅደሱን በሠራ ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ "በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችሉም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ይህ ቤት እንዴት ያንስ ይሆን?" (2 ዜና 6፥18).
​እውነተኛው መቅደስ፦ እግዚአብሔር የሚፈልገው የድንጋይ ቤት ሳይሆን የሰው ልብን ነው።
​የክርስቶስ ተስፋ፦ "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" (ዮሐንስ 14፥23).
🗣​3. "ተሰሩ" – ሕያው ድንጋዮች መሆን (1 ጴጥሮስ 2፥4-5)
​"እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።"
​ለምን መቅደስ ሆንን? እግዚአብሔር ክብሩን የሚገልጥበት፣ ከሰው ጋር ህብረት የሚያደርግበትና በምድር ላይ ፈቃዱን የሚያደርግበት ማደሪያ እንዲኖረው ነው።
​ማን ይኖርበታል? አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) በውስጣችን ያድራሉ። "ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?" (1 ቆሮንቶስ 6፥19).
🗣​4. ለመሠራት ምን ያስፈልጋል? (ዝግጅት)
​መቅደስ ለመሆን ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይሆን በጸጋው መሠራት ያስፈልጋል።
​በቃሉ መሠረት መሆን፦ ግንባታው የሚካሄደው በቃሉ መመሪያ ነው።
​ንጽህናና ቅድስና፦ "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ" (1 ቆሮንቶስ 3፥17). ያለ ቅድስና ጌታን ማየትም ሆነ ማስተናገድ አይቻልም።
​ትህትናና የልብ ጥራት፦ "ልባቸው ንጹሐን የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና" (ማቴዎስ 5፥8).
​መገጣጠም (አንድነት)፦ ድንጋይ ለብቻው ቤት አይሆንም። "በእርሱም ሕንጻው ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል" (ኤፌሶን 2፥21). ከአማኞች ጋር ያለን ህብረት ለመሠራት የግድ ነው።

​5. መሰናክሎችና በረከቶች
​የመሠራት እንቅፋቶች፦
​ኩራት፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል።
​ያልተናዘዘ ኃጢአት፦ መቅደሱን ያረክሳል።
​ከወንድሞች ጋር አለመስማማት፦ ግንቡ እንዳይገጣጠም ያደርጋል።

🗣​መቅደሱ ካልሆንን ምን ያጋጥመናል?
የእግዚአብሔር መገኛ የሌለበት ሕይወት ባዶ፣ ተስፋ የሌለውና ለጠላት ጥቃት የተጋለጠ ይሆናል። "እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ" (መዝሙር 127፥1).
​የተሠራ ሕይወት በረከቶች፦
​የውስጥ ሰላም፦ የሰላም አምላክ ስላለበት።

🗣​ፍሬያማነት፦ ከምንጩ ጋር ስለተያያዝን።
​ለሌሎች በረከት መሆን፦ መቅደስ የእግዚአብሔር በረከት ለዓለም የሚፈስበት ቦታ ነው።
​

​ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ! እግዚአብሔር ዛሬም እንዲህ ይለናል፦ "ተሰሩ!"። በቃሉ ተጠረቡ፣ በትህትና ተለሰኑ፣ በፍቅር ተገጣጠሙ። ራሳችንን ለእርሱ አሳልፈን ስንሰጥ፣ እርሱ ደስ የሚሰኝበትና ክብሩ የሚታይበት ውብ መቅደስ ያደርገናል።

​የግል ጥያቄ

"ዛሬ የልቤ መቅደስ ለእግዚአብሔር መኖሪያነት የተመቸ ነውን? ወይስ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ኮረብታዎች አሉብኝ?"
​ብለን እንጠይቅ የቃሉን ስልጣን የመንፈሱን ሰራተኝነት በማመን
ለመሰራት የተዘጋጀ እና በረከቱን የሚካፈል ህይወት እንዲኖረን እግዚአብሔር ይርዳን።

Address

Adiss Ababa
Addis Ababa

Opening Hours

Monday 23:30 - 13:30
Wednesday 03:00 - 19:00
Saturday 04:00 - 19:00
Sunday 03:00 - 19:00

Telephone

+251911014887

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Emanuel/ አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Emanuel/ አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው:

Shortcuts

Share