28/08/2025
🛑 ቀይ ባህር ለእኔ ዘላለማዊ ቤቴ እንዲሆን ወስኛለሁ።
#የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጥዋቱ 1:30 ሲሆን ብርጋዴር ጄነራል ተሾመ ተሰማ ምጽዋ ከተማ ላይ የተወሰኑ የጦር መኮንኖችንና ማዕረግተኞችን ሰብስበው ንግግር አደረጉ።በንግግራቸውም እንዲህ አሉ፡-
‹‹......ሻዕብያ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ ምጽዋን ለመያዝ ቆርጦ መነሳቱ ጥርጥር የለውም። እኔ የሚጠበቅብኝን አደራ ተወጥቻለሁ፡፡ ከጥር 30 ጀምሮ እስከ የካቲት 9 ቀን1982 ዓ.ም የሞት ሽረት ትግል አድርጌያለሁ። ከዚህ በኋላ የራሴን ህይወት በክብር ማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖች ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም።
ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ሁኖ አለመገኘት ነው። እኔ ዛሬ ብሞት ብሸነፍም በታሪክና በመጭው የኢትዮጵያ ትውልድ ፊት አልሸነፍም። የአጼ ቴዎድሮስን እድል በማግኘቴ በጣም እኮራለሁ።
#ጎበዝ ስሙኝ! ይህ የአደራ መልክቴ ነው። ነገ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይደርስ ይሆናል። ምን አልባት አምላክ ካለ ከእናንተ አንዱ መልዕክቴን ያደርስልኛል።ዛሬ ሻዕብያ ምጽዋን ይቆጣጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገሬ እና ህዝቧ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነውንና ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ጸንቶ የቆየውን የባህር በራችንን በመዝጋት በምድር ተወስነን እንድንቆይ ይደረግ ይሆናል። ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነው።...... የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የባህር በር አልባ ሁኖ በኢምፔሪያሊስቶችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ተሸንፎና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ይህ ከሆነ የአጼ ዮሐንስ፣ የራስ አሉላ አባነጋና የእኔን ጨምሮ የአብዮታዊ ሰራዊት አባላት አጥንትና ደም በኢትዮጵያውያን ትውልድ ሁሉ እስከ ዘላለሙ ይፈርዳል።ጊዜውን ጠብቆ የኢትዮጵያ ጀግና ምጽዋን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የጸና ነው።
#እናንተ መኮንኖች ስሙኝ!
#አንድ ሰው ቤት ሲሰራ የሚሰራው ቤት በርና መስኮት አሉት። አንድ ሰው ደግሞ ሞተ እንበል መቃብሩ በርና መስኮት የለውም። ይህ ምሳሌ ከገባችሁ ባህር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ሰው የምትለየው በትንሹ ነው።ቀይ ባህር ለእኔ ዘላለማዊ ቤቴ እንዲሆን ወስኛለሁ። ደስተኛ እና እድለኛ ጄነራል ነኝ።እኔ ብሞት ታሪኬ አይሞትም። ቻው! ቻው! ማንም ሰው ወደ እኔ እንዳይጠጋ›› አሉና ጄነራል ተሾመ መኮንኖቹ ከተሰበሰቡበት ቦታ ተፈናጥረው ወደ ቀይ ባህር ጠረፍ አመሩ፡፡
#የሰራዊት አባላቱ ተደናግጠው ከተቀመጡበት ተነስተው የጄነራሉን የመጨረሻ ፍፃሜ ለማየት እየዘገነናቸው እንባ በእንባ ሆኑ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ህይወታቸውን ለማጥፋት የመሳሪያቸውን መጠበቂያ ከፍተው የጀነራል ተሾመን ምሳሌነት ለመከተል ተዘጋጁ።
ተሾመ ከወደቡ በስተቀኝ ለቀይ ባህር ውሃ መገደቢያ በተሰራ ግንብ ጠርዝ ላይ ጀርባቸውን ቀይ ባህር ፊታቸውን ወደ ምጽዋ ከተማ አድርገው ቆሙ። ቀጥለው በእጃቸው የነበረውን ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ወደ ቀይ ባህር ወረወሩና በወገባቸው ታጥቀውት የነበረውን ኮልት ሽጉጥ አውጥተው አፈሙዙን በአፋቸው ጎርሰው የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጥዋቱ 2:10 ቃታውን ሳቡት። ድምጹ እንደተሰማም በጀርባቸው በቀይ ባህር ውሃ ላይ ወድቀው ሰጠሙ። ወዲያውም የጄነራሉን ሞት በምስክርነት ቆመው ካዩት መካከል ከ150 የማያንሱ መኮንኖችና ማዕረግተኞች በተለያየ መሳሪያ ህይወታቸውን አጠፉ።ሌሎችም እንደዚሁ አደረጉ፡፡በአጭር ደቂቃ ውስጥ አካባቢው ሬሳ በሬሳ ሆነ!
ኤርትራን ከኢትዮጵያ የነጠለ ጦርነት አይምጽዋ፤አስር አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ