24/04/2026
የሀዲያ ዞን ወጣቶች ማህበር ጽ/ቤት "በወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተሳካ ምርጫ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ።
ሆሳዕና፣ሚያዚያ 16/2018 ዓ/ም የሀዲያ ዞን ወጣቶች ማህበር ጽ/ቤት "በወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተሳካ ምርጫ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን በመድረኩ የሀዲያ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ዲሞክራሲና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስዩም ደጉ፣የዞኑ ወጣቶች ማህበር ጽ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ስንታየሁ አለማየሁ፣ የሆሳዕና ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኪበሞ ሰለሞንን ጨምሮ የዞን እና የሆሳዕና ከተማ ወጣት አደረጃጀቶች ተገኝተዋል።
የሀዲያ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ዲሞክራሲና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስዩም ደጉ እንደገለፁት ወጣቶች ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ላይ እያደረጉት ላለው ብርቱ ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም የዛሬው መድረክ ከዚህ በፊት በወጣቶች ለተሰሩ ስራዎች እውቅና የሚሰጥበት እና ቀጣይ ለምንሰራቸው ሥራዎች አቅጣጫ የምንይዝበት ነው በማለት ተናግረዋል።
ወጣቶችን የብልጽግና መንግስት ይፈልጋቸዋል ያሉት አቶ ስዩም ደጉ አፍራሽ ሀይሎችም ወጣቱን ለእኩይ አላማቸው መጠቀም ስለሚፈልጉ የዞናችን ወጣቶች የተለመደውን በጎ ስብዕና በማስቀጠል 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ከወዲሁ መስራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
የሀዲያ ዞን ወጣቶች ማህበር ጽ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ስንታየሁ አለማየሁ በበኩላቸው የሆሳዕና ከተማ ወጣቶች ህዝቡ የምርጫ ካርዲ እንዲያወጣ ከመቀስቀስ እና ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ላበረከቱት ጉልህ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን የገለፁት አቶ ስንታየሁ የምርጫው ቀን እስኪደርስ ለመራጩ ማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠርና በምርጫው ቀን ሁሉም በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ ማድረግ ከወጣቱ ይጠበቃል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሆሳዕና ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኪበሞ ሰለሞን አክለው በሆሳዕና ከተማ በሁሉም ቀበሌዎች ህዝቡ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ የተደረገው ብርቱ ጥረት በሁሉም መስክ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በማለት ጠቁመዋል።
የሆሳዕና ከተማ የወጣቶች ስብዕና ማዕከል ለወጣቱ ክፍት ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ወጣቱ ትርፍ ጊዜውን አልባሌ ቦታ ከመዋል ወደ ወጣቶች ስብዕና ማዕከል በመሄድ እንዲዝናናም ጥሪ አቅርበዋል።