14/05/2026
ቤጂንግ-የቻይና መሪ በታይዋን ጉዳይ የዩናይትድ ስቴትስ እንግዳቸዉን አሳሰቡ
ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና በታይዋን ጉዳይ ላይ ካልተግባቡ የሁለቱ ሐገራት ልዩነት ወደ ግጭት እንደሚንር የቻይና መሪ አስጠነቀቁ።የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊና የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሺ ጂፒንግ ሐገራቸዉን በመጎብኘት ላይ ለሚገኙት ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እንደነገሩት የታይዋን ጉዳይ ለቻይና «ጥያቄ ሊቀርብበት የማይገባ» መሠረታዊ ጉዳይ ነዉ።ቻይና እ.ግ.አ ከ1949 ጀምሮ ከዋና ግዛትዋ የተገነጠለችዉን ታይዋንን አሁንም ድረስ የግማደ ግዛትዋ አካል አድርጋ ትቆጥራታለች።ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ባንፃሩ ለታይዋን የነፃ ሐገርነት ዕዉቅና ባይሰጡም ለታይፔ አስተዳደር ዘመናይ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅን ጨምሮ ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጋሉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ ከትናንት ጀምሮ በቻይና የሚያደርጉት ጉብኝት ሁለቱ ኃያል፣ የዓለም ሐብታም ሐገራት በታይዋን፣ በኢራን ጦርነትና በንግድ ልዉዉጥ ላይ ያላቸዉን ልዩነት ለማጥበብ ይረዳል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር።የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ግን ትራምፕና ሺ ዛሬ ለሁለት ሰዓታት ባደረጉት ዉይይት በሶስቱም ጉዳዮች ላይ የተጠበቀዉን ያክል አልተግባቡም።የአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት AP የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በX ገፁ ያሰራጨዉን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበዉ ሺ ለአሜሪካዉ እንግዳቸዉ « ሁለቱ ሐገራት በታይዋን ጉዳይ ከተስማሙ አጠቃላይ ግንኙነታቸዉ ይሰምራል፣ ይሕ ካልሆነ ግን ሁለቱ ሐገራት መቃቃራቸዉ ምናልባትም መጋጨታቸዉ አይቀርም።» ብለዋል።ሁለቱ መሪዎች በዝግ ከመነጋገራቸዉ በፊት ግን አንዱ ሌላዉን ሲያደንቁና ሲያወድሱ ነበር።ለፕሬዝደንት ትራምፕ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋልም።