13/11/2023
እኔና የካፌዋ አስተናጋጅ!
ትናንት አንድ ካፌ ቁጭ ብዬ አንድ መጽሐፍ እያነበብኩኝ ሳለሁ ከአስተናጋጆቹ አንዷ ቀረብ ብላ “ምን ላምጣልህ” አለችኝ፡፡ ሃሳቤ በማነበው ነገር ተወስዶ ስለነበረ ለመልስ ዘግየት ስላልኩባት በትእግስት ከጠበቀችኝ በኋላ “ምን አይነት ሃሳብ እያነበብክ ቢሆን ነው እንደዚህ ትኩረትህን የሳበው?” አለችኝ፣ በፈገግታ፡፡ እኔም ለጥያቄዋ መልስ ከሰጠኋት በኋላ፣ “መጽሐፍ ታነቢያለሽ?” ብዬ ጠየኳት፡፡
የልጅቷ መልስ፡- “ሰዎች ከሚሰጡኝ “ቲፕ” የማገኘውን ገንዘብ በመለቃቀምና በማጠራቀም የየእለት ኑሮዬን ለማሸነፍ ከጠዋት እስከማታ ስለፋ ስለምውል ለማንበብም ጊዜ የለኝም” የሚል ነበር፡፡ ይህ መልሷ በወቅቱ አጠር ያለች ሃሳብ እንድለግሳት፣ ቤቷ ስትሄድ ደግሞ የምትሰራውን የቤት ስራን እንድሰጣት አነሳሳኝ፡፡
ይህቺ ሴት የዘነጋችው ነገር ቢኖር በየእለቱ የማንበብን ልማድ ብታዳብር፣ በምትለቅመው “ቲፕ” የየእለት ኑሮዋን ለማሸነፍ ከመታገልና ማለቂያ የሌለው ዑደት ውስጥ ከመቅረት አልፋ በምታነበው ሃሳብ ደግሞ የነገ ኑሮዋን የተሻለ የማድረግ አመራጩ እንዳላት ነው፡፡
ከዚህ በፊት አንብቤው ያነቃቃኝ አንድ ሃሳብ ትዝ አለኝና እሱን አሳብ በአጭሩ አጋራኋት፡-
በቀን ውስጥ ካለን ጊዜ አንድ በመቶውን (1%) ብቻ ከዓላማችን አንጻር እድገት-ተኮር የሆኑ ጽሑፎችን ብናነብ በሌላ መልኩ ልናመጣ የማንችለውን ለውጥና እድገት እናመጣዋለን፡፡ ይህ ማለት በቀን ውስጥ ካሉን 1,440 ደቂቃዎች ውስጥ አንድ በመቶውን (1%) ማለትም 14.4 ደቂቃዎችን (15 ደቂቃ የማይሞላ) ጊዜያችንን ለንባብ መጠቀም ማለት ነው፡፡
ሰዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዓታትን በጥናት አሳልፈው በጥቂት ገጾች ውስጥ ያሰፈሩልንን እውቀት እኛ በቀን 15 ደቂቃዎችን ብቻ በማሳለፍ፣ በማንበብና ተግባራዊ በማድረግ ታላቅ የሆነ እድገት ውስጥ መግባት እንችላለን፡፡
አንድ ጥናት እንደሚነግረን በቀን ውስጥ በአማካኝ ከ60 ጊዜ በላይ ጊዜ ስልካችንን እናነሳለን፡፡ ይህ ልማድ በቀን ውስጥ ከ3 ሰዓታት በላይ ስልካችን ላይ የማሳለፍን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ለ15 ደቂቃዎች መጽሐፍን ማንሳት አስቸጋሪ አይደለም፣ የልማድ ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ!
የልጅቷ መልስ ከዚህ ስሌት አንጻር ሲተረጎም፣ “ለማደግ ጊዜ የለኝም” የሚል ይሆናል፡፡ በየቀኑ የእለት ኑሮዋን ለመግፋት ሰዓታት በማሳለፍ የምትለቅመው “ቲፕ” አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በየቀኑ የወደፊት ኑሮዋን ለመለወጥ አስራ አምስት ደቂቃዎች በመውሰድ ሕይወት ለዋጭ እውቀት “የመለቃቀምን” ልማድ ብትጨምርበት ደግሞ እጅግ የተሻለ ነው፡፡
ካላት የማስተናገድ ስራ ሩጫ ሰረቅ በማድረግ የሰጠችኝን ትኩረቷን በመጠቀም ከላይ የዘረዘርኩትን ሃሳብ ጠቆምኳትና እንዳጋጣሚ በቦርሳዬ ውስጥ የያዝኩትን በራሴው ከተጻፉት መጽሐፎች አንዱን ሰጠኋት፡፡
የመጨረሻ ጥያቄዋ እንዴት የንባብን ልማድ ላዳብር ነበረና የሚከተሉትን ለእኔ የጠቀሙኝን ልምምዶች አጋራኋት፡፡
1. የምታነቢውን የመጽሐፍ ርእስ ለማምጣት ከምትፈልጊው ለውጥ አንጻር ምረጪ፡፡
2. የማንበብን ልማድ በደንብ እስከምታዳብሪ ገጻተቸው አነስ ያሉ መጽሐፎች ላይ አተኩሪ፡፡
3. በቀን ውስጥ ለ15 ደቂቃዎች የምታነቢበትን ንቁ ሰዓት ለይተሽ መድቢ፡፡
4. በዚያን ጊዜ ሌሎች ማድረግ የምትፈልጊያቸው ነገሮች ብቅ ቢሉም፣ ሆን ብለሽ ከእነሱ ይልቅ ማንበብ ላይ አተኩ፡፡
5. ማንበብ ካስቸገረሽ የማንበብ ልማዱ ያላቸው የንባብ አጋሮችን በማዘጋጀት የጋራ ነገር በማንበብ ተበረታቱ፡፡
6. በቀን ውስጥ የማንበቢያ ክፍተቶችን ለይተሽ ተጠቀሚባቸው፡፡ የማንበቢያ ክፍተቶች ማለት፣ ሰውን ስትጠብቂ፣ በታክሲ ውስጥ ስትጓዢ፣ በስራ መካከል ያለ እረፍት፣ ከመተኛትሽ በፊት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
አንብቡ! እናንብብ! እንደግ! የወደፊታችንን እኛው እንወስን!
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/