21/09/2026
የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት በመስቀለኛ መንገድ ላይ፦ የዓርታኢያን ማኅበር ምልከታዎች
(መላኩ ብርሃኑ)
ቀድሞ በስራ አስፈጻሚ አባልነት ያገለገልኩት ፣ አሁንም አባል የሆንኩበት የኢትዮጵያ ዓርታኢያን ማኅበር (Editors' Guild of Ethiopia) በራዲሰን ብሉ ሆቴል ባዘጋጀው 3ኛው ወርሃዊ የዓርታኢያን የቁርስ ላይ ወይይት ላይ የመሳተፍ ዕድል አግኝቼ ነበር።
ይህን አይነት የባለሙያዎች ውይይት በሚዲያ ኢንደሰትሪውና በጋዜጠኝነት ላይ የተደቀኑትን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለመፈተሽ የሚያስችል ፕላትፎርም ነው ብዬ አምናለሁ ።
ለሚቀጥሉት 14 ወራት የሚዘልቀው ወሳኝ የውይይት መድረክ በይፋ የተከፈተው ደግሞ የኢንደስትሪው አሁናዊ አንገብጋቢ ነገር በሆነው "በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት መስቀለኛ መንገድ ላይ መገኘት" ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው።
የትናንቱ ውይይት ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ በርካታ ዋና ዓርታኢያን፣ የመንግሥትና የሙያ ማህበራት ተወካዮች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን እንደመነሻ በአሁኑ ወቅት የአገራችን ጋዜጠኝነት የተደቀነበትን ከባድና የማይካድ ችግር፣ ከአርታኢያን ፈተና ጋር በማሰናሰል በቀረበው ጽሁፍ ላይ ተንተርሰን ተወያይተንበታል።
በተለምዶ ለእውነተኛ መረጃ የመጨረሻው በር ጠባቂ (gatekeeper) የሚባለው የዘመኑ አርታኢ በውስጣዊ ድክመቶችና በውጫዊ ተጽዕኖዎች ሳቢያ ከበባ ውስጥ ነው።
የሶሻል ሚዲያና ኤአይ ተጽዕኖ የፈጠረውን የአርታኢ አስፈላጊነት ጨምሮ ሰፊ ሃሳቦች የተነሱበትን ይህንን ውይይት እንደመካፈሌ በውይይቱ ወቅት፣ በኢትዮጵያ ስላለው የሚዲያ ሁኔታ ያለኝን ጥልቅ ስጋት በሚከተሉት አምስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ላይ በማተኮር አጋርቻለሁ።
የማኅበራዊ ሚዲያ የበላይነት መግነንና የሚዲያ አጀንዳ ቀራጭነት ሚና መላላት አንዱ ተግዳሮት ነው።
እንደቲቪ፣ ራዲዮና ጋዜጣ ያሉ ሚዲያዎች (Legacy media) የራሳቸውን አገራዊ ውይይትና አጀንዳ ከመቅረጽ ይልቅ፣ ያም ይሄም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቃቸውን "breaking news" አንደዘገባ መነሻ በመከተል በሱ ላይ የተመረኮዘ ዜና አጠናቃሪ እየሆኑ ነው። ሚዲያዎችና አርታኢያን የመረጃ ፈር ማስያዝ ተጽዕኗቸውን እያጡ በአንጻሩ የማህበራዊ ሚዲያ ጎርፍ እያሰመጣቸው ነው።
በሌላ በኩል ልምድ ያላቸውን አርታኢያን ከሚዲያ እያጣን መሆኑም አንድ ስጋት ነው። እነዚህኞቹ ከሚዲያ እየሸሹ በምትኩ የሙያ ስነምግባር በቅጡ ያልገባቸው ልጆች ደግሞ መድረኩን እየያዙት ነው። ምንም በማይካድ መልኩ የሙያ ሥነ-ምግባርን የጠበቁ መረጃዎችን ለመቅረጽ የሚያስችል ተቋማዊ ትውስታ ያላቸው፣ ልምድና ብቃት ያላቸው የበሰሉ ዓርታኢያን በኢኮኖሚና በሙያዊ ጫናዎች ምክንያት፣ ወደ ተለያዩ ተቋማት የኮሙዩኒኬሽን ስራዎች ፈልሰዋል።
የእነሱ መልቀቅ የሚፈጥረውን ክፍተት ሚዲያውን የፕሮፌሽናል ዘገባ እጥረት እና የራሱን ቀለም ፈጣሪ የመሆን አድሉን እያሳጣ ዋጋ እያስከፈለው ነው።
በሌላ በኩልም በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚወጡ የተቆጣጣሪ አካላት መመሪያዎች ከመገናኛ ብዙሃን ባለቤት ጫናዎችና ከመንግስትና ከማይታወቁ አካላት ከሚመጡ ፈተናዎች ጋር ተዳምረው የሚዲያው እድገትና የኤዲተሩ ነጻነት አደጋ ላይ ነው።
ከሕግ አሠራር ውጪ የሚመጡ ቅጣቶችና አንዳንድ የሕግ ማዕቀፎች የዓርታኢያንን ያመኑበትን የመስራት ነጻነት ጠፍንገው ይዘውታል። ይህ ሁኔታ ለኢኮኖሚ ህልውና ሲባል መንግሥትን ለማስደሰት ከሚደረጉ የባለቤቶች ጫናዎች ጋር ሲደመር፣ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድመውን ጋዜጠኝነት በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም የሙያ ሥነ-ምግባር መላላት ሚዲያዎች ጠንከር ላለ የሕዝብ ትችት እንዲጋለጡ እያደረገ ሲሆን፣ ይህም ታዳሚዎች ከእምነት ማጣት የተነሳ ኃላፊነት ወደማይሰማቸው አማራጭ የሶሻል ሚዲያ መረጃ አቅራቢዎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ በር ከፍቷል።
እንደአጠቃላይ ግን በዘርፉ ተደማጭነታችንን ጠብቀን ለመቀጠል ማዕበሉ እስኪወስደን ድረስ ዝም ብለን ማየት የለብንም እላለሁ። ሚዲያው ከእንቅልፉ መንቃት አለበት። እንደ ዓርታኢያን ማኅበር ባሉ ተቋማት የሚመራ ዘርፈ-ብዙ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያስችል የተጠናከረ ስብስብ መፍጠር ያስፈልጋል። ሙያዊ መሥፈርቶቻችንን ወደማይጣሱ ጥብቅ ደንቦች መለወጥ ይኖርብናል።
በተጨማሪም፣ አስተማማኝና ሥርዓት የጠበቀ የጋዜጠኝነት ተቋም እንዲኖር መደገፍ ለመንግሥት ለራሱም ቢሆን ስትራቴጂካዊ ጥቅም አለው። ዋና ዋናዎቹ የሚዲያ ተቋማት ከፈረሱ፣ የአገሪቱ የመረጃ ፍሰት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ማጭበርበር በሚመሩ፣ ሥርዓት በሌላቸውና ኃላፊነት በማይሰማቸው አካላት ቁጥጥር ሥር ይወድቃል።ይህ ደግሞ ጉዳቱ "ኮላተራል' ነው።
እንደሚዲያ ባለሙያ በውይይቱ ላይ የተገኘን ሁላችንም በአንድ የማይካድ እውነት ላይ ተስማምተናል፦ ምንም እንኳን አሁን በአሳሳቢ መስቀለኛ መንገድ ላይ ብንገኝም፣ የኃይል ሚዛኑን ግን ወደነበረበት መመለስ አለብን። ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት የሕዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና በዘመናዊው የዲጂታል ትርምስ ላለመዋጥ በጽናት መቆም አለበት።
"ይህንን ዕቅድ በትክክል እንዴት ወደ ተግባር እንቀይረዋለን?" የሚለው ጉዳይ ደግሞ የሚቀጥሉት 14 ወራት ውይይቶቻችን የሚቀርጹትን የመፍትሄ ሃሳቦች የሚጠብቅ ዋና ስራ ይሆናል።
ለማንኛውም ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከፈተና ባሻገር ማንሰራራት እንዲመጣ የሚደረገው ትግል ጉዞው ቀላል አይመስለኝም።