22/04/2026
በየዓመቱ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ሚያዝያ 22 ቀን በዛሬው ዕለት ማለት ነው የዓለም የመሬት ቀን ይታሰባል። ዕለቱ ሲታሰብም በየዓመቱ የራሱ መሪ ቃል ይኖረዋል፤ የዘንድሮው «የእኛ ኃይል፤ የእኛ ፕላኔት» የሚል ሲሆን በመላው ዓለም በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ለአፍታ እንቅስቃሴውን ገታ አድርጎ ስለሚኖርበት መሬት ያስባል ተብሎ ይገመታል። ዋና ዓላማው የመሬትን ተፈጥሯዊ ገጽታ እያበላሹና እየለወጡ ያሉ ድርጊቶች የሚገቱበትን መንገድ ለማፈላለግና መሬት ለሰዎች ልጆች የምትሰጠውን ጥቅም ለማገናዘብ ነው። የተመድ ዕለቱን አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጾቹ ባወጣው መረጃ ምድራችን ከአግባብ ውጪ በሚደረጉ ተግባራት ምክንያት የደረሰባትን ተጽዕኖ የሚያመላክት ግልጽ መልእክት እየላከች ነው ብሏል። የአየር ንብረት ለውጥ አንስቶ የደን መራቆት እና ለእርሻ የመሬት አጠቃቀም መለወጥ፤ የእንስሳት እርባታና እየተባባሰ የመጣው ሕገወጥ ሰደድ እሳት ተደራርበው በመሬት ላይ ከፍተኛ ጫና በማስከተላቸው የዓለምን ውድመት እያፋጠኑ ነው ሲል አስጠንቅቋል። የዓለም የመሬት ቀን ሲታሰብም ሆነ በየዕለቱ ዓለም ዘላቂነት ያለውን ኤኮኖሚ ለመገንባት ወደሚያስችል አሠራራር የሚያደርገውን ለውጥ ማፋጠን እንደሚኖርበትም አሳስቧል።