26/09/2026
"የመስቀል በዓል፣ በልብ ውስጥ ያለ ፣በተግባር የተገለጠ ፍቅር፣ የተቀበረ እውነትን መግለጥ እንደሚችል ማሳያ፣ የመታመን እና የትጋት ሽልማት ምልክት ነው።"
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ
ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ፀሐፊ ለመስቀልና ለደመራ በአል ያስተላለፋት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት
ክቡራን የሀገራችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ ክርስቲያኖች እና የዚህ ታላቅ በአል ተካፋዮች እንኳን ለብርሃነ ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ቀናት የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል፣ ከታሪካዊና መንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር ሕዝባችን በአብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ያስቻለ ታላቅ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ እሴት ነው።
መፅሐፍ ቅዱስ፣የታሪክ መፃህፍት ፣የትውፊት ድርሳናት፣ መንፈሳዊ አስተምህሮቶቻችን እንደሚነግሩን መስቀል በዓል ታሪካዊ መሠረት የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት ከሶስት መቶ ዓመታት በኋላ እንደሆነ እና ታላቁ ንጉሠ ቆስጠንጢኖስ በጠላቶቹ ሲከበብ በሰማይ የታየውን የክርስቶስን መስቀል ምልክት ተጠቅሞ ድልን ከተቀዳጀ በኋላ፣ እናቱ ንግሥት እሌና እውነተኛው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ለዘመናት ተደብቆ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የሆነውን ቦታ ከአባቶች በተረዳችው መሰረት ደመራ ደምራ እጣን አጪሳ ጢሱ በባረፈበት ቦታ በመስከረም 16 ቅዱስ መስቀሉን ለማግኘት ቁፉሮውን አስጅምራ መጋቢት 10 ቀን በ326 ዓ.ም እውነተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘቱን ምክንያት በማድረግ ህዝበ ክርስቲያኑ በድምቀት የመስቀልን በአል እያከበረ ዛሬ ለይ ደርሰናል።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ድልን የተጎናፀፍንበት፣ ሰላም የተሰበከበት እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ወደር የማይገኝለትን ፍቅር ያየንበት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፣ ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው” (1ኛቆሮ. 1፥18) በማለት እንደገለጸው፣ መስቀል የሰው ልጆች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁበት፣ የኃጢአት ዕዳ የተከፈለበት እና የዘላለም ሕይወት የተገኘበት የማዳን ምሥጢር ነው። ክርስቶስ በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ በመሞቱ፣ የሰው ልጆችን ሁሉ ከፍጡራን ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጋር አስታርቋልና መስቀል የአደባባይ የእርቅ ሰነዳችን ነው።
ንግስት እሌኒ ይህንን የሰው ልጆች የሞት እዳ የተከፈለበትን እውነተኛ የእርቅ ምልክት የሆነውን መስቀል ብርቱ ዋጋ በመክፈል በእውነተኛ መንፈሳዊ ትጋት ፈልጋው ማግኘቷ ዛሬ የምናከብረው የመስቀል በዓል ለኛ በልብ ውስጥ ያለ በተግባር የተገለጠ ፍቅር፣ የተቀበረ እውነትን መግለጥ እንደሚችል ማሳያ፣ የመታመን እና የትጋት ሽልማት ምልክት ሆኖልናል።
የመስቀልና የደመራ በዓል ኢትዮጵያውያንን ዘር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድነት የሚያሰባስብ ታላቅ የማኅበራዊ ትስስር መንፈሳዊ ህብረት መገለጫ ነው።
የደመራ መብራት ከሩቅ ሲታይ የሁሉንም አይን እንደሚስብ፣ የዚህ በዓል መከበርም የኛን ልብ በአንድነት ፣አብሮነት ያጠናክራል በዓሉ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ዘመድ ከዘመድ ጋር የሚገናኝበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት እና የደስታ መካፈያ ትልቅ መድረክ ነው።
የደመራው እሳት እሳት ብቻ አይደለም ጥላቻን እና መለያየትን በማቃጠል፣ በምትኩ ይቅርታን፣ ፍቅርንና የምንሰብክበት በመስቀል ለይ የሞተውን ጥል ከልባችን አውጥተን ጥለን ፍቅርን እርቅን የምናውጅበት ነው።
ጥቂት የብርሃን ጭላንጭል ጨለማን የማስወገድ ጉልበት እንዳላት ሁሉ ጨለማ የሆነውን ጥላቻ ፣መለያየት፣ ቂም እና በቀልን ለማስወገድ የሚረዳንን የመንፈስ ብርሃን እንድንታጠቅ ይህ ከመስቀል ደመራ የሚወጣው ብርሃን ወደ አማናዊዉ የክርስቶስ መስቀል እለት እለት በህይወታችን እንድናስብ ያደርገናል።
በዓሉ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ መስተጋብር፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ባህላዊ እሴቶች ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ ቅርስ በመሆኑ እኛ የሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች እንዲሁም ምእመናን በዓሉን ስናከብር የጥላቻና የግጭት መንፈስን ተወግዶ የይቅርታና የሰላም አየር እንዲሰፍን ለፀሎት መትጋት ስለሰላም አብዝቶ ማስተማር እንዲሁም የሳተው መመለስ ከኛ ይጠበቃል።
በመጨረሻም የመስቀል በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን፣ የተሰደዱትንና ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳትና በመተጋገዝ እንደ ደመራው በጋራ በመሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር ማሳየት ይኖርብናል።