09/23/2026
በውጭ ባሉት ዘንድ የተከበረ የክርስትና ሕይወት
1 ተሰሎንቄ 4:9-12
ክርስቲያናዊ ሕይወት በተግባር የሚገለጥ ነው። በአንደበታችን ጌታችንና መድኃኒታችን መሆኑን የምንመሰክርለት ክርስቶስ፣ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን በአሕዛብ ዘንድ ባለን የሕይወት ምስክርነትም እንደዚያው መሆኑን ልናሳይ ይገባል። ቤተ ክርስቲያን መልዕክቷን ተአማኒነትና ቅቡልነት የሚያሳጣት ዋነኛ ምክንያት የምስክርነት ግድፈት ነው። ዓለምን በጽድቅ ሕይወት ለመኮንን የሚያስችል ዐቅም ያስፈልገናል።
ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚለየው ከግብዝነት ከጸዳ ንጹሕ ፍቅር፣ በርኅራኄና በተግባር ከቀረበ ምስክርነት ነው። የተሰሎንቄ ቅዱሳንን በዚህ አንጻር ጳውሎስ እጅግ ያመሰግናቸዋል። በቅድሚያ እርስ በእርስ መዋደድን የተማሩት ከፍቅር አምላክ ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፦
“ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም እንዲጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና።”
የተሰሎንቄ አማኞች ከከተማቸው ባለፈ መልኩ፣ በመላው የመቄዶንያ አውራጃ እንዲሁም በዓለማውያን ዘንድ ሳይቀር በአኗኗራቸውና እርስ በእርስ ባላቸው በፍቅራቸው የታወቁ ነበሩ። ይህ በሁሉ ዘንድ የተመሰከረለት ክርስቲያናዊ ኑሮ የሚፈልቀው እግዚአብሔርን ከማወቅና ለእርሱም ክብር ከመሰጠት ውስጥ ነበር። የኅብረታቸው ማዕከልና የማይበጠሰው ገመድ ክርስቶስ እና የሠራው ሥራ ብቻ ነበር። ቀደም ሲል አይሁድና የተለያዩ ጣዖታት ተከታዮች የነበሩት አሕዛብ፣ አሁን በክርስቶስ አንድ ቤተ ሰብ፤ የአንድ አገር ዜጋ ሆነዋል። ቀድሞ እርስ በእርስ ጠላቶች የነበሩት አሁን በመስቀሉ ሥራ አንድ ሆነዋል።
የክርስቲያናዊ ሕይወት መሠረት በእግዚአብሔር ፍቅር ከውስጥ ወደ ውጭ የተቀየረ ማንነት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይጽፋል፦
“ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።” (1 ዮሐንስ 3:16)
ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ በስደት መካከል ለነበሩት ቅዱሳን እንዲህ ይላል፦
“በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8)
ልክ እንዲሁም ጳውሎስ የተሰሎንቄ ወንድሞችና እኅቶች በዚሁ ምስክርነት እየጨመሩ እንዲኖሩ ያበረታታል። በተግባር ይህ ማለት፦
* የጌታን ዳግም መገለጥ በጽናትና በጉጉት መጠባበቅ፦ወደ ላይ በመመልከት መምጣቱን መጠበቅ፣ ደግሞም በየዕለት ኑሮ ትጋት እያሳዩ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት አምባሳደሮች መኖር።
* ፍጻሜያዊ (Eschatological) ኑሮ፦ በዚህች ምድር ላይ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ መኖር። ይህ መንግሥት መጥቷል፣ እየመጣ ነው፤ ወደፊትም በአካል ይገለጣል።
* ጸጥታና ሰላም የተሞላበት ሕይወት፦እስከዚያው ድረስ ክርስቲያናዊ ኑሮ ረብሻ፣ መከፋፈል፣ ጥል፣ ክርክርና ዓለማዊ ጩኸት የማይሰማበት ጸጥ ያለ ነው።
በኅብረት ብናመልክም ክርስትና እግዚአብሔርን የማክበር የየዕለት የግል ሩጫ ነው። በአጭሩ ሥርዓት ያለው፣ የሰላምና የዝግታ፤ እንዲሁም የትጋት የዘወትር ኑሮ (orderly, peaceful and diligent living) ነው። ስለዚህ በራስ መንገድና በውስጥ የግል ሰላም ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል።
---
* በእግዚአብሔር ፊት የእኛስ ሕይወት ምን ይመስል ይሆን?
* በፍቅር ለክርስቶስ አካል ኅብረት ያለን መሰጠትስ እስከምን ድረስ ነው?
* በውጭ ያሉትስ የእኛን ሕይወት እንዴት ያነቡታል?
“ጌታ ሆይ! አንተን በሚመስል ሕይወት በየዕለቱ እንኖር ዘንድ ጸጋህን ስጠን፤ አድሰንም።” አሜን!