18/07/2023
የመኪና ባላንብረት ሆነው የግድ መታወቅ ያለባቸው መሰረታዊ የተሸከርካሪ ክፍሎች እና ጥቅማቸው
================================
ክፍል 1
# - ኮኔክቲን ሮድ (ቤላ) - በፒስተን እና በክራንክሻፍት (ኮሎ) መካከል በመሆን የሚያገናኝ ዘንግ ሲሆን በሲሊንደራችን ውስጥ ፍንዳታ በሚፈጠርበት ግዜ የሚገኘውን ሀይል በቀጥታ ለክራንክሻፍት (ኮሎ) የሚያስተላልፍ አገናኝ ዘንግ ነው፡፡
------------------------------------
# - ስፓርክ ፕለግ - በቤንዚን ሞተር ላይ የሚገጠም ሲሆን በሲሊንደራችን ውስጥ ከታመቀው የአየር እና ነዳጅ ቅልቅል ላይ የእሳት ብልጭታ በመፍጠር እንዲቀጣጠል የሚረዳ የእሳት አቀጣጣይ ክፍል ነው፡፡
------------------------------------
# - ዲፍሬንሻል - ከጊርቦክስ (ካምቢዮ) ሀይልን ተቀብሎ ለሺምያዝ (አክስል) የሚያስተላልፍልን ነው፡፡ ኃይል በሚያስተላልፍበት ግዜ ቀጥ ባለ መንገድ ላይ እኩል ኃይል በመስጠት እንዲሁም በመታጠፊያ መንገዶች ላይ የውጭው ጎማ ከውስጠኛው የበለጠ እንዲዞር በማድረግ ከሞተር በመነሳት በትራንስሚስዮን በኩል የሚመጣውን ዙር (ኃይል) ወደ ጎማ ዙር ይቀይራል፡፡
------------------------------------
# - ካም ሻፍት (አልብሮ ካም) - ይህ ክፍል ወጣ ገባ ያለ ቅርጽ ያለው ሲሆን ከክራንክ ሻፍት (ኮሎ) የሚገኘውን ኃይል በመጠቀም አስወጪ እና አስገቢ ቫልቮች ግዜያቸውን ጠብቀው እንዲከፈቱ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የዘይት እና የነዳጅ ፓምፖች እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡
------------------------------------
# - ኦይል ፓን (ሶቶኮፓ) – በሞተራችን የታችኛው ክፍል ላይ የሚገኝ ለሞተራችን ማለስለሻ የሚሆን ዘይት የሚይዝ ሲሆን በውስጡ ባለው ማጣሪያ በመታገዝ የተጣራ ዘይት ያቀርባል፡፡
------------------------------------
# - ፍላይዌል (ቮላኖ) - ከክራንክሻፍታችን (ኮሎ) በስከኋላ በኩል በመገጠም ክራንክሻፍት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሽከረከር ከማስቻሉም በላይ ባሉት ጥርሶች አማካኝነት ሞተራችን እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ይህ ቦታ ለፍሪሲዮን መግጠሚያነት ያገለግላል፡፡
------------------------------------
# - ቴርሞስታት - የሙቀት መለኪያ እና መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሲሆን ከሞተራችን ወደ ውኃ ማቀዝቀዣ ክፍል ራዲያተር ውሀ እንዲያልፍ ወይም እንዳያልፍ መንገድ የሚዘጋ እና የሚከፍት ነው፡፡ ሞተር በምናስነሳበት ግዜ በቂ ሙቀት እስከሚያገኝ ውኃው እዛው ሞተር ውስጥ እንዲቀር እና ወደ ማቀዝቀዣ ክፍል እንዳይመለስ መንገዱን በመዝጋት ሞተራችን ቶሎ እንዲሳ ያግዛል፡፡
------------------------------------
# - ስታርተር ሞተር (ሞተሪኖ) - ይህ ክፍል ተሽከርካሪያችንን በቁልፍ (ኳድሮ) ስናስነሳ የሚተላለፈውን የኤሌክትሪክ ሀይል ወደ ሜካኒካል እንቅስቃሴ (ኃይል) በመለወጥ ሞተራችን እንዲነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ ሞተሪኖ ኃይል ሲደርሰው የፍላይዌልን (ቮላኖ) ጥርስ በመምታት ፒስተናችን እንዲንቀሳቀስ እና ኃይል እንዲያገኝ ምክኒያት ይሆናል፡፡