Justice For Ethiopia Task Force

Justice For Ethiopia Task Force Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Justice For Ethiopia Task Force, Dallas, TX.

05/14/2025
05/14/2025

♦ልቤን ሰብሮታል!♦

በዛሬው ዕለት
በወልድያ ሆስፒታል የተደረገው የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ላይ ተሳታፊ ነበርኩ። ጥያቄው የትውልድ ጥያቄ ነው። የትውልድን ጥያቄ ፥ ትውልድን ወክለን ለማቅረብ መቻል ዕድለኝነት ነው።

ሀገርና ህዝብ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ጥያቄው ምላሽ ሊያገኝ በሚችልበት ርቀት ሁሉ ለመጓዝ የትውልድ ኃላፊነትና ፥ የህዝብ አደራ እንዳለብን አምናለሁ።

በእውነት
እጅግ በምሳሳላቸው የሥራ ባልደረቦቼ አፍ አንዳንድ ጥያቄዎቹን ስሰማ ልቤ በሀዘን ተላወሰ።








እንዴት ልብ ይሰብራል!

መታከሚያ የሌላቸውን ታካሚዎች ተበድረው የሚያሳክሙ ጓደኞቼ ፥ ሲሉ ስሰማ ልቤ ፈሰሰ።

ለታካሚ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ እና በትጋታቸው የሚየስደንቁኝ የስራ ባልደረቦቼ ድምፅ አውጥተው ከታካሚዎቻቸው ፊት ቆመው ሲሉ ስሰማ ሳግ ተናነቀኝ።

ብዙ ደም ፈስሷት ልትሞት ለደረሰች እናት ፥ ደማቸውን ለግሰው ሕይዎቷን የሚታደጉ (የታካሚያቸው እንባ የሚገዳቸው) ፥ ቤዛ የሚሆኑ የሥራ ባልደረቦቼ ፤ ሲሉ ሳደምጥ ፥ ውስጤ ተረበሸ።

በእርግጥም
በታካሚ ሕመም የሚታመሙ
ሌሎች እንዲድኑ የሚታመሙ ፤ እንዲኖሩ በቀንና በሌሊት ዋጋ የሚከፍሉ የጤና ባለሙያዎች ድምፅ ሲያሰሙ መስማት ያማል።

አወ እውነት ነው
ታካሚን ለማከም ፥ በሕክምና ለማገዝ እና እንዲኖሩ ለማድረግ ፤ በመጀመርያ የጤና ባለሙያው መኖር መቻል አለበት።

ድሮም
የጤና ባለሙያ ዝምታ የምቾት(ያለመራብ) አልነበረም። ነገር ግን ዶ/ር ማለቱ ክብረ ነክ እና የሚያሳፍር ሁኖ ፤ በስሙ እየተፅናኑ (ስሙን ተመግቦ) ወደ ሕክምና የገቡበትን ዕለት እየረገሙ መኖር ተለምዶ ነበር።

አሁን ግን
አንገትን በማቅለስለስ የሚገፋ አልሆነም። ክብር ሆድ አይሞላም ፥ ርሀብን አያስታግስም ፤ እርካታ ቤት ኪራይ አይከፍልም።
በአሁኑ ሰዓት በመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ የጤና ባለሙያ ሁኖ እየሰሩ መቀጠል ፤ እየተራቡ መሥራት ብቻም ሳይሆን ፤ ለመራብ መሥራት መሆኑ እውነት ነው።
ምክንያቱም ርሀብን ማስታገስ የሚችል ሌላ ሥራ በሚሰሩበት ፥ ሙሉ ጊዜና አእምሮን የሚፈልግ ሥራ ላይ እውቀትን ፣ ጉልበትንና ዕድሜን መግፋት ውጤቱ የታወቀ ነውና።

ሙያውን እየወደዱት ፥ የሚወዱትን ህዝብ በሙያቸው ማገልገል አልችል ብለው ፤ ሌላ የሥራ አማራጭ ከመፈለጋቸው በፊት ፥ ሀገርና ህዝብን ወክለው ህዝቡ ሊያቀርበው የሚገባውን ጥያቄ ነው እያቀረቡ ያሉት።

አንዳንዶች የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን ላይረዱ ይችል ይሆናል። እውነቱ ግን ህዝቡ ሊጠይቀው የሚገባውን ጥያቄ ጤና ባለሙያዎች ህዝቡን ወክለው እየጠየቁ መሆኑ ነው።
ጥያቄውን ህዝቡ ራሱ ፥ የህዝብ ጥያቄ ማድረግ ካልቻለ ፤ ጤና ባለሙያውም ሌላ የሥራ አማራጭ ለመፈለግ እና ከህዝቡ እንደ አንዱ ለመሆን ይገደዳል።

ህዝቡ ሙያችን የሚያከብር እና ያስፈልጉኛል ብሎ የሚያምን መኖራችንንም የሚሻ ከሆነ ፤ ጥያቄያችን ጥያቄው ሊሆን ይገባል።
ካልሆነ ደግሞ የጤና ባለሙያው የራሱን ሌላ የሥራ አማራጭ ለመፈለግ ይገደዳል።

በዚ ከቃጠልን ፥ ጥያቄው ካልተመለሰ !
ሲባል ዶ/ር የሚል ትውልድ ይጠፋል።
መስዋዕትነትና ብዙ ውጣ ውረድ የሚሻን ትምህርት እና ሙያ ፥ ዋጋ ከፍሎ ለመማር የሚፈልግና የሚወስን ትውልድ እናጣለን። የተማሩት ከሙያው እየወጡ ፥ ሌላው ሊማረው የሚመኘው ሙያ ፥ ሊሆን በጭራሽ አይችልም።

ጥያቄው
የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚወስን የማዕዘን ድንጋይ ነው።

ይህን ሲባል ቅንጦት የሚመስላችሁ
ምን እየሆነ እና ምን እየጠየቅን እንዳለን የራሴን ሕይዎት በማስረጃ ልንገራችሁ።

10ኛ ክፍል 04 (አራት ነጥብ) አምጥቻለሁ።
12ኛ ክፍል ላይ የትኛውም የትምህርት ዘርፍ ላይ መርጨ መግባት የሚያስችል ነጥብ ለማምጣት ችያለሁ።

በተፈጥሮ ሳይንስ (Natural Science) ትምህርት ከሌሎች ብልጫ ያለው የትምህርት ውጤት የሚፈልግ እንደመሆኑ ፥ የህክምና ሳይንስን የተቀላቀልኩት በምርጫዬ ነው።

የሕክምና ትምህርትን ለመምረጥ
12 ዓመት የልጅነት ሳቅ ጨዋታዬን ሰውቻለሁ።

ጠቅላላ ሀኪም ለመሆን
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለ6ዓመት ከ6ወር በብዙ ድካምና እንቅልፍ ማጣት ውስጥ አሳልፌያለሁ።
የሕፃናት ሕክምና እስፔሻሊስት ለመሆን
03 ዓመት በጥበበ ግዮን እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከታማሚዎች ጋር ታምሜያለሁ።

እስፔሻላይዝ ካደረግሁ
02 ዓመት ከ6ወር አስቆጥሪያለሁ።

በእኛ ባች ባህር ዳር ዩኒቨርሲቱ ከተመረቅን 140 ሀኪሞች ፤ በ6ኛ ዓመት (የInternship ትምህርት) ስድስት ሀኪሞች ቲቢ ተይዘዋል።

እኔም
የዛሬ ዓመት በቅዱስ ላሊበላ ሆስፒታል አገልግሎት እየሰጠሁ ፤ በቲቢ በሽታ ምክንያት ከሞት አፋፍ ተመልሻለሁ።
Refractory Shock 2° Miliary TB with Adrenal crisis.
መዳኔ ተዓምር ነበር።

ለምን እንደሆነ ባላውቅም
የክፍያን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቼ አስቤው አያውቅም ነበር። የታካሚዎችን ግብረ መልስ እንደ ደመወዝ ቆጥሬ በሱ ተጽናንቸ አልፍ ነበር።

እጅግ የሚያስደንቀኝ ነገር ግን
የጤና ባለሙያው ጥቅማ ጥቅም አለመጨመሩ ብቻ ሳይሆን ከበፊቱ መቀነሱ ነው።

በ2015 ዓ.ም ህዳር ወር እስፔሻላይዝ አድርጌ ወደ ቅዱስ ላሊበላ ሆስፒታል ስመደብ ፤ በ2001 ዓ.ም የጸደቀውን የጥቅማጥምቅ መመርያ መነሻ በማድረግ የቤት ኪራይ 1000 ብር ፤
ከሙያ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች 2000 ብር ይከፈለኝ ነበር።

ከ2015 የካቲት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ ደግሞ ሁለቱም በ35 % Tax መደረግ ጀመረ።
አሁን ለቤት ኪራይ 650 ብር ይከፈለኛል።
በእውነቱ እንዲህ ያለ ቤት ታይቶ አይታወቅም።

ሌሎችን ለማዳን ሲባል ለስንት ተላላፊ በሽታዎች ራስን አሳልፎ ሰጥቶ ፤ በሕይዎት ተወራርዶ እየሰሩ የተጋላጭነት 1,300ብር ክፍያ ሽሙጥ እና ስላቅ ነው።

ለአንድ እስፔሻሊስት ሀኪም
8297 ብር የተጣራ የወር ደመወዝ ክፍያ
(Gross Salary = 12,765)

ተጨማሪ የስራ አማራጭ
ካልፈለጉለት የወር ከወር ከወር አያደርስም። ቤተሰብ መምራት አያስችልም። እርካታ ዳቦ አይገዛም እርካታ ቤት ኪራይ አይከፍልም ፤ እርካታ ተበድረን ላሳከምናቸው ታካሚዎች መልስ አይሆንም።

ታማሚ በበዛባት ሃገር ፦
1- ያሉት የጤና ባለሙያዎች መኖር እንዲችሉ እና በሙያው እንዲቆዩ ፤

2- ሌላ የገንዘብ ማግኛ ፍለጋ እየባከኑ ሙያውን እንደ ትርፍ እንዳይቆጥሩት ፤

3- በሌላው የሙያ ዘርፍ የምናየው ብልሹ አሠራር(ገንዘብና ጉቦ) ወደ ሕክምና ተቋማት እንዳይገባ ፥ ከገባም እንዳይንሠራፋ ለማድረግ

4- ብሩህ አእምሮ የሚሻውን ትምህርት ፤ መስዋዕትነት የሚፈልገውን የሙያ ዘርፍ ለመቀላቀል እና ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ ብዙዎችን ለማፍራት (ወደ ሕክምናው ዘርፍ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ) ጊዜው አሁን ነው።

እንዲሉ ፤
ዛሬ ዝም ብለን ፥ ሳንመልሰው አደባብሰነው ብናልፍ ፤ ነገ የሚፈጠረውን ዘርፈ ብዙ የትውልድ ክፍተት ለመሙላት ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል። ነገ የእኛን የልጆቻችን ሕይዎት አምነን እንዲያክምልን የምንሰጠው ባለሙያ ጥራት እያሽቆለቆለ መምጣቱ አይቀርም።

በዚህ ዓመት
ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እስፔሻላይዝ ለማድረግ የሚማርላቸው ሰው ማጣታቸው ፤ ዝም ብሎ ሊታለፍ የማይችል ፤ ለዚህ ማሳያ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ነው።

ሁላችንም
ጥያቄውን ጥያቄያችን እናድርግ!
አብረን መፍትሔ እንፈልግ።

©ዶ/ር ዮሴፍ ጌትነት
የሕፃናት ሕክምና እስፔሻሊስት
30/08/2017 ዓ.ም

Address

Dallas, TX

Telephone

+14692315633

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Justice For Ethiopia Task Force posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Featured

Share