20/09/2024
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ለአገር ለቤተክርስቲያን ለቤተሰብ መሪን ይሰጣል። እግዚአብሔር መሪዎችን በመስጠት በረከትን ይሰጣል። እግዚአብሔር መሪዎችን በመስጠት የሚታወቅ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ሲባርክህ ትክክለኛ መሪን ይሰጠናል። እግዚአብሔር የሚመራን በሚሰጠን መሪዎች ጭምር ነው። ጤናማ መሪ ያላት ቤተክርስቲያን እና ሃገር የተባረከች ናት።
መሪ የራሱ ስነ ምግባር አለው። መሪ ከእግዚአብሔር የተገኘ ምንም ቢሆን እንኳ መሪዎች ስነ ምግባር ሊኖረው ይገባል። መሪ የስነ ምግባር መርሆችን ካልተከተለ የሚመራው ተቋም ላይ መከፋፈልና፣ አለማደግን ይመጣል።
የመሪ ስነ ምግባር ከሌለ ውጤት የለም። በጸጋ ብቻ የሚመጡ ውጤቶች ዘላቂ አይሆኑም ጸጋውን ይዘን የምንቀጥልበት የበሰለ መሪነት ያስፈልገናል፣ ስነ ምግባር ከሌለ እውነተኛ ለውጥ የለም። መሪነት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ጸጋ ሲሆን፣ ራሳችን ላይ በመስራት የምናሳድገው ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንደኛው ተግዳሮች በስነ ምግባር የታነጹ መሪዎች ጉድለት ነው። ስነ ምግባር ማለት እግዚአብሔር ለሰጠን የመሪነት አደራ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃልና በበሰለ አመራር የምናበቃት መንገድ ማለት ነው።
እንከን አልባ መሪ የለም። አይኖርምም። አንድ እንከን አልባ መሪ ኢየሱስ ብቻ ነው። ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችን ላይ በመስራት በተሰጠንን አደራ ራሳችንን በማብቃት ከሰራን፤ ጥሪው ካለንና ጥሪያችንን ካሳደግን ውጤታማ መሪ እንሆናለን።
መሪ ስነ ምግባር አለው ስንል ከመሪ የሚጠበቁ መሰረታዊ ነገሮች አሉ ማለታችን ነው። መሪ ቀዳሚ እንደመሆኑ ምሳሌ መሆንና ለሚመራቸው ትክክለኛ መሪ መሆን አለበት። እስቲ በጥቂቱ የመሪ ስነ ምግባር የሆኑትን እንመልከት።
የመሪ ስነ ምግግባር
1፣ መሪ ይቅርታ አይራጊ ነው። መሪ ምሬትና ጥላቻ የተሞላ መሆን የለበትም። መሪ በተለያዩ ሰዎች ከቅርብም ከሩቅም፣ በውሸት፣ በመከዳት ጥለውት በሚሄዱ ሰዎች፣ በተለያዩ መንገድ ውስጥ ሊያልፍ ይችላል። መሪ በይቅርታ ለመመላለስ ራሱን ማዘጋጀት አለበት። መሪነት ሰዎች ብዙ በደል በመሪው ላይ የሚፈጽሙበት ስፍራ ነው፣ ይቅርታ ለማድረግ ካልፈቀደ መሪነቱን ቢለቅ ይሻለዋል። ስለዚህ ከመሪ መለየት የሌለበት ይቅርታ ማድረግ ነው።
2፣ አመስጋኞች መሆን አለብት። መሪ እግዚአብሔር ስለ ሰጠው ሰዎች፣ ስለ ተሰራው ስራ፣ በአገልግሎቱ ወይም በሚያስፈልገው ነገር አብረውት ስለቆሙ ሰዎች ተገቢ ምስጋና መስጠት አለበት፣ ከምንም በላይ አምላኩን አመስጋኝ መሆን አለብት። ማጉረምረምና መሳበብ መሞላትም የለበትም። ሰዎች ስላደሰጉለት ጥቂት ነገር አመስጋኝ የሆነ መሪ ውጤታማ መሪ ነው።
3፣ ትሁት መሆን አለበት። ከመሪ ህይወት የሚጠቀቀው ሌላኛው ነገር ትህትና ነው። ሁለቱ መሪዎች ማለትም ኢየሱስ እና ሙሴ ትሁቶች ነበሩ። ትህትና ለመሪነትን ሞገስ የሚጨምር በንግግር እና በስብከት ብቻ የማይገለጥ ነገር ግን በመኖር የሚታይ ህይወት ነው ትህትና። እግዚአብሔር ትሁት መሪዎችን ይስጠን።
4፣ አማኝ መሆን መቻል አለበት። መሪ በምንም መንገድ ውስጥ ቢያልፍ በእግዚአብሔር ማመን እና ለሚመራቸው እምነቱን ማጋራት አለበት። መሪው ያላመነውን ነገር ሌላው እንዲያምነው አይጠበቅም። ማለትም መሪው ያልኖረውን ህይወት ሌሎች እንዲኖሩት ግድ አይባልም።
5፣ የጸሎት ሰው መሆን አለበት። መንፈሳዊ መሪ የጸሎት ሰው፣ የራሱም ለሚመራት ቤተ ክርስቲያን እና ለምዕመናን፣ ለአገልግሎቱ ጭምር የሚጸልይ መሆን አለበት። መሪ የምዕመኖቹን መንፈሳዊ ህይወት በጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ፣ በድምጽ ምዕመናኑን የሚመራ ነው። የማይጸልይ መሪ አገልግሎቱን በትግልና በሰው ምድራዊ ጥበብ ይመራል።
6፣ መሪ ሰጪ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ መሪ የምናውቀው ሰጪ ነው። ንፉግነት የመሪ መገለጫ አይደለም። መሪ ገንዘቡን፣ ጊዜውን ያለውን ነገር ሁሉ የሚሰጥ ነው። መቀበል ላይ የተመሰረተ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፣ በመስጠት ውስጥ ያለ መቀበል እንጂ። መሪ ሰጪ ሲሆን እግዚአብሔር በሚሰጡት ሰዎች ይባርከዋል።
7፣ መሪ ትጉህ ነው!! መሪ ብሎ ሰነፍ ከሆነ አረም የሞላበት ተክል የሚጠብቅን ጠባቂ ይመስላል። መሪ ትጉህ ካልሆነ በመንጋው መካከል፣ አረም፣ ያልተገባ ነገር ይኖራል። ስንፍና ምንባቸው ይሆናል። ምክንያት እየፈጠረ ከሐላፊነት የሚሸሽ መሪ አይደለም። መሪ ትጉህ ነው፣ በተሰጠው ነገር በመትጋፍ ፍሬያማ ነው። የመሪ ሐብቱ ያቀደውን ነገር ለማስፈጸም መትጋቱ ነው። ምክንያት ደርዳሪነትና ስንፍና የመሪ መገለጫዎች አይደሉም።
8፣ መሪ የፍቅር ሰው ነው። መሪ የፍቅር ሰው መሆን ይጠበቅበታል። መንፈሳዊ መሪ ሲሆን ደግሞ ዋናው መሪ ኢየሱስ የፍቅር ሰው እንደ መሆኑ የእርሱ ፈለግ የተከተለ መሪ መሆን አለበት። መሪ ሁሉም ሰው ሊወደው አይችልም፣
ነገር ግን ሁሉን የመውደድ ግዴታ ግን አለብን። መሪ ከፍቅር ከጎደለ አመራሩ ሁሉ የወደቀ ይሆናል። የመሪነት ዋነኛው ቁልፉ ፍቅር ነው።
9. ሌሎችን የሚያነሳሳ ነው። መሪ የሚመራቸውን አካላት ለተሻለ ስራና አገልግሎት የሚያነሳሳ መሆን አለበት። ሌሎች መሪዎች ወደ መሪነት እንዲመጡ የሚያነሳሳ፣ ምዕመናኑን ለተለያዩ መንፈሳዊ ሐላፊነቶች እንዲበቁ የሚያነሳሳ መሆን አለበት። ትክክለኛ መሪ ሌሎች ለስራ ሲነሳሱ ደስተኛ ነው።
10፣ መሪ ሌሎችን አክባሪ ነው!! የማያከብር ሰው አይከብርም፣ ሌሎችን የሚያጣጥልና የሚያናንቅ መሪ ነገ በተከታዮቹ ያ ዕጣ ይደርሰዋል። መሪ የሚቀበለው ሁሌም የሰጠውን ነውና። ሰዎችን ባወቅን ቁጥር ማክበር ይበልጣል። ማክበር የመሪ ባህሪ ነው። የሚያከብር መሪ የሚከባበሩና፣ የሚያከብሩት ምዕመናንን ያበዛል። አገልጋዮችን ላይ የሚቀልዱ፣ በመንፈሳዊ ነገር የሚሳለቁ መሪዎች ልቅ ትውልድ ያፈራሉ። መሪ አክባሪ ነው።
11፣ መሪ መልካም ምክር ሰጪም ተቀባይም ነው። መሪ ለሚመራቸው መልካም ምክርን ይሰጣል። ምክርን በተገቢው ቦታ ለተገቢው ሰው ይሰጣል። ከሌሎች ምክርን ይቀበላል። ምክርን ላለመቀበል ግትር አይደለም። ጠቃሚ ምክሮችን ለመቀበል ትሁት ነው።
12 መሪ ገበና ሸፋኝ ነው!! መሪ በሚመራቸው ምዕመናን ህይወት የሰማውን ነገር ለስብከት ማጣፈጫ አያደርግም፣ ለሌሎች ለማይመለከታቸው የሰዎችን ማንኛውን ገመና አደባባይ አያሰጣል። መሪ ገመና ሸፋኝ ነው።
13, መሪ አንባቢ ነው፣ መሪ ራሱን ላይ በንባብ እና በትምህርት የሚሰራ ነው። ትናንት የተረዳውን ሰምቶ የመጣን ትውልድ የትናንቱን ስብከት በመደጋገም አያጸናውም። ከዚያ ይልቅ ቃሉን ያነባል ይቆፍራል። ያስተምራል፣ ይመራል።