19/06/2026
"የተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲወሰን ያደርጋል"አቶ ነቢዩ ቤዛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዞን ጤና መምሪያዎችና ተጠሪ ተቋማት የጋራ ምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ጤና ቢሮ ኃላፊና አስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነቢዩ ቤዛ በመክፈቻ ንግግራቸው በጤናው ሴክተር የጤና ሰው ሀብቱን ማጠናከር ቁልፍ ተግባር በመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡
የመረጃ ጥራትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፈት የሰው ኃብቱን ማብቃት ዋንኛ ተግባር ነው ያሉት አቶ ነቢዩ፤ ሪፎርሙን መሠረት ያደረገ ክልላዊ የጤና ሴክተር ሰው ኃይል አሠራርን በዕውቀት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መድረኩ ከሰው ኃይል አንፃር ያልተፈቱ የሴክተሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችለን መድረክ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በጤና ሚኒስትር የብቃትና የሰው ኃብት ልማት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሐብታሙ ደምሴ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በጤናው ሴክተር የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ነፃና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቫንት መገንባት፣ ብዝሃነትና አካታችነትን፣ የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀትን ማጠናከር፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫና ምዘና ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ አቶ ሐብታሙ አስገንዝበዋል፡፡
በጤና ቢሮ የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምሳሉ ተስፋዬ የጤና ሴክተር ሪፎርም ሥራን በማጠናከርና የሰው ኃይል ሥምርትን በአግባቡ በመጠቀም የሰው ኃይል እጥረትን መቅረፍ የሚያስችል ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
የሰው ኃብት መረጃ አያያዝና ምዝገባ ሥርዓትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ የመረጃ ድግግሞሽ፣ የመጥፋትና መቅረት ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ተግባቦት እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
ለጤና ባለሙያው አጋዥ አሰራርና የመረጃ አደረጃጀት ሥርዓትን በመዘርጋት ዞኖች ችግር ፈቺ ተግባር በማከናወን የባለሙያውን እንግልት መቅረፍ የሚያስችል አሠራር መከተል እንዳለባቸው አቶ አምሳሉ ተናግረዋል፡፡