13/09/2024
በቦዲቲ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት መሪነት የ2017 ዓ.ም የጊፋታ በዓል በደማቁ ለማክበር የሚያስችል ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
ቦዲቲ ፤ መስከረም ፤ 3/2017 ዓ.ም በወላይታ ዞን በቦዲቲ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት መሪነት የ2017 ዓ.ም የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ የ"ጊፋታ" በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የቦዲቲ ከተማ ከንቲባ አቶ ጳውሎስ በቀለ እንደገለፁት ወላይታ ለአለም ህዝብ የሚያካፍላቸው መልካም የሆኑና የምንኮራባቸው በርካታ ባህሎች መኖራቸውን ለውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች አብራርተው "ጊፋታ" ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ጳውሎስ አክለውም መስቀል በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበር ሀይማኖታዊ በዓል እንደሆነና "ጊፋታ" የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነ ታሪካዊና ባህላዊ ልዩ በዓል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ስለዚህ ይህንን የማንነታችን መገለጫ የሆነውን በዓላችንን ለአለም ህዝብ ከማሳወቅ አኳያ ይህ ትውልድ አሻራቸውን በሚገባ ማሳረፍ አለበት ብለዋል።
አቶ ፍሰሃ ሳሙኤል በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ በበኩላቸው ወጣቱ ትውልድ የራሱን ቱባ ባህል ጠንቅቆ ማወቅ እንዳለበት ተናግረው በዚሁ ልክ ሌሎችንም በሚገባ የማሳወቅ ኃላፊነት እንዲሁም ግዴታም እንዳለባቸው አስረድተዋል ።
ጊፋታ ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ በድምቀት ስከበር የመጣ የማንነታችን ልዩ መገለጫ እንደሆነ ያነሱት አቶ ፍሰሃ በዓሉ ምንም አይነት ግንኙነት ከሀይማኖት ጋር እንደሌለው አብራርቷል።
በአሁኑ ጊዜ ጊፋታ በአለም ቅርስነት የማስመዝገብ ስራ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፍሰሃ ጥረቱ ዳር እንዲደርስ አሁንም ከፍተኛ ስራን ስለሚጠይቅ ወጣቱ የእራሱን አሻራ በተለያየ መንገድ ማሳረፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ ታረቀኝ መንግስቱ በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ እንደተናገሩት የወላይታ ህዝብ ለብዙ ዘመናት የራሱን የማንነት መገለጫ የሆነውን ቋንቋውን ፥ ባህሉንና ታሪኩን ጠብቆ የቆየ ጀግና ህዝብ እንደሆነ አስረድተው ባህሉን ለአለም ህዝብ ማስተላለፍ ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።
አቶ ታረቀኝ አክለውም ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን ፡ ባህሉን እና ወጉን አውቀው በመኖር ሌሎች እንዲያውቁ የበኩላቸውን ለወጡ እንደምገባ አሳስበው "ጊፋታ "በዓል በሀይማኖት ተቋም ስም የሚከበር ሳይሆን የወላይታ ማንነት መገለጫ ከዘመን ዘመን መሸጋገሪያ ድልድይ የሆነ ታሪካዊ በዓላችን ነው ሲሉ አብራርተዋል።
አቶ አሸናፊ አፋቶ በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ በንግግራቸው የማንነታችን መገለጫ የሆነውን "ጊፋታ" በዓል አከባበር በአለም ታሪካዊ ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።
ይህንን የወላይታ ብሔር ልዩ መገለጫ የሆነውን ጊፋታ በአለም ቅርስ መዝገብ ላይ በደማቅ ብዕር ተጽፎ እንድቀር የወጣቱ ሚና የጎላ መሆን እንደሚገባም ተናግሯል።