20/10/2026
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ የ2019 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ የ2019 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ አበረታች ስራዎች ተገምግመው በቀጣይ ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
የግምገማ መድረኩን አስመልክቶ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም አብዱማሊክ እንደገለፁት ባለፉት ሶስት ወራት የወጣቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አቅም ለማሳደግ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
በፓርቲው እና በወጣቶች ክንፉ የተቀናጀ ጥረት የተከናወኑ ስራዎችም ተጨባጭና አበረታች ውጤቶችን አስገኝተዋል።
አቶ አብዱልሀኪም አብዱማሊክ እንደገለፁት፣ ባለፉት የሩብ ዓመቱ ወራት ወጣቱን ባሳተፈ መልኩ በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ይህም በወጣቶች መካከል ያለውን የመተሳሰብ እና የህብረተሰብ አገልግሎት እሴት ከፍ አድርጎታል ብለዋል።
ወጣቶች በራሳቸው ጥረት እና በመንግስት ድጋፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
የወጣቱን ሁለንተናዊ ንቃተ-ህሊና እና አመራር ሰጪነት ለማጎልበት የታለሙ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አንስተዋል።
ወጣቶች በአካል እና በአዕምሮ የጠነከሩ፣ የሰላም እና የአብሮነት እሴቶችን የሚጋሩ እንዲሆኑ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች መካሄደቸውን ገልፀዋል።
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ኃላፊ ወጣት ጫላ ሙክታር በበኩሉ፣ ፓርቲው የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስቷል።
ወጣቱ የሀገሪቱ የነገ ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የዛሬ የልማት እና የሰላም ባለቤት በመሆኑ የተጀመሩ ሰፊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል።
በግምገማ መድረኩ ላይ ባለፉት ሶስት ወራት የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ክፍተቶች የታዩባቸውን አፈፃፀም ደግሞ በማረም በቀጣይ ወራት ለተሻለ ስራ መዘጋጀት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።