08/11/2024
ላልተጠበቀው ነገር መዘጋጀት
ሁል ጊዜ አንድን ነገር ስትጀምሩ በመንገድህ ላይ ያልተጠበቀ ነገር እንደሚገጥማችሁ አትዘንጉ፡፡ እነዚህ የማትጠብቋቸው ነገሮች አብዛኛዎቹ ምንጫቸው ከእናንተ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ሊገመት የማይችል የሁኔታዎች መለዋወጥ፣ ሊተነበይ የማይችል የሰዎች ባህሪይ መቀያየርና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ከመንገዳችሁ ላይ እንቅፋት እንዳይጠፋ ያደርጉታል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች አንድን ነገር ለመጀመር፣ ከጀመርን በኋለ ለመቀጠል፣ አልፎም ወደፍጻሜ ስንደርስ እንዳንጨርስ ሲጋረጡብን እናገኛቸዋለን፡፡ ይህንን አይነቱን የማይቀር የሕይወት ሂደት የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መልኩ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶች ለደረሰብን እንቅፋት ሁሉ በሰዎች፣ በሁኔታዎችና በፈጣሪ የማማረር ልማድ አለብን፡፡ በዚያም ሁኔታ ተደብቀን በተስፋ መቁረጥ እርምጃችንን እንተዋለን ወይም ለሌላ ጊዜ እናስተላልፈዋለን፡፡
ሶስት አይነት እንቅፋቶች አሉ . . .
1. አንዳንዱ እንቅፋቶች ቀድሞውን ሊደርሱ የሚችሉ እንቅፋቶችን በማጤንና በማቀድ ልታስወግዷቸው የምትችሏቸው ናቸው፡፡
2. ሌሎቹ እንቅፋቶች አስቀድማችሁ አቀዳችሁም አላቀዳችሁም ከመምጣት የማታስወግዷቸው እንቅፋቶችና እንደአመጣጣቸው ልትመልሷቸው የምትችሏቸው ናቸው፡፡
3. ሌሎቹ ግን እንቀፋቱና ችግሩ እያለ መንገዳችሁ ላይ ብቻ በማተኮር ወደፊት ልትቀጥሉ የሚገባችሁ አይነት እንቅፋቶች ናቸው፡፡
ከላይ በተጠቀሱት የእንቅፋት አይነቶች መካከል የመለየታችሁ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተጨማሪ እነዚህን አትርሱ፡-
1. ሁል ጊዜ አንድ ነገር ለመጀመር እቅድ ሰታወጡ በእቅዳችሁ ውስጥ ለድንገተኛውና ላልተጠበቀው እንቅፋት ማቀድን አትርሱ፡፡
2. ያልተጠበቀና ድንገተኛ እንቅፋት ሲያጋጥማችሁ ትክክለኛውን ምላሽ በመምረጥ ምላሽን ለመስጠት ሞክሩ፡፡
3. አንድ እንቅፋት ካጋጠማችሁና አስፈላጊውን ምላሽ ከሰጣችሁ በኋላ ወደ ዓላማችሁና ወደስራችሁ በመመለስ እሱ ላይ ማተኮርን አትርሱ፡፡
✍ኢዮብ ማሞ