09/07/2026
አዲሱ የቤት ኪራይ ውል አከራይና ተከራይን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን የሚገታ ነው
AMN- ሐምሌ 2/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነዋሪዎች ላይ ያለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል እና በቤት ኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ አሰራሮችን ለመፍታት አዲስ የቤት ኪራይ ውል እድሳት እና የጭማሪ ጣሪያ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው ፍትሀዊ የቤት ኪራይ አመታዊ ጭማሪ ጣሪያ 11.5 በመቶ ሆኖ የጸደቀ ሲሆን ከተቀመጠው የጭማሪ ጣሪያ በላይ ዋጋ መጨመር በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ እንዳስታወቁት፤ የውል እድሳቱ አከራይንም ሆነ ተከራይን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን የሚገታ ነው፡፡
ቢሮው ለውል እድሳቱ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን እና የአተገባበር ሂደቱን በመከታተል አዋጁን ተፈጻሚ ለማድረግ በጥብቅ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
ከህጋዊ አሰራር ውጪ የሚደረጉ "የመንደር ውሎች" ፈጽሞ የተከለከሉ መሆናቸውን እና ከተቀመጠው ህጋዊ ተመን ውጪ የሚያስከፍሉ አከራዮች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ኃላፊዋ አሳስበዋል፡፡
ህጉን በሚተላለፉ እና ውላቸውን በማያድሱ አካላት ላይ ቅጣት እንደሚጣል የገለጹት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ፤ የውል እድሳት ጊዜያቸው አልፎ አከራይም ተከራይም አብረው ኖረው እድሳት ሳይፈጽሙ እስከ ሁለት ወር ከቆዩ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ቅጣት ይጣልባቸዋል ብለዋል፡፡
ውል ሳያድሱ ሶስት ወር እና ከዚያ በላይ የቆዩ ደግሞ የሁለት ወር የቤት ኪራይ ቅጣት የሚከፍሉ ሲሆን አዲስ ተከራይ አስገብተው ውል ያላደሱ እና ያላስመዘገቡ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ይቀጣሉም ነው ያሉት፡፡
በጥቆማ ወይም በክትትል ውል ያላደሱ ወይም ያላስመዘገቡ መሆናቸው ከተረጋገጠ ደግሞ ከአንድ እስከ ሶስት ወር የሚደርስ የኪራይ መጠን ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው፣ ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር አዋጅ መሰረት ከተቆጣጣሪው አካል እውቅና ውጪ የሚደረጉ ውሎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
የውል ጊዜ ሲያልቅ አከራዩ ውሉን ማደስ እና ማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በመግለጽ አዲሱ ውል ለሁለት አመታት የሚቆይ ይሆናል ብለዋል፡፡
አዋጁ ተከራዮች መኖሪያ ሲቀይሩ የሚደርስባቸውን የልጆች ትምህርት ቤት እና የሥራ ቦታ መናጋት በማስቀረት ማህበራዊ አብሮነትን እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት በክፍለ ከተማ እና በወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንዲሁም በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫዎች ህጋዊ የውል እድሳት ማከናወን እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡