17/07/2026
ከኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋ ባንክ አገልግሎት፤ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተላለፈ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት!!
***
ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት (EPHI) አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና መላው የሥራ ባልደረቦች፤
እንኳን ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት 100ኛ ዓመት (የመቶ ዓመት የጉዞ ስኬት) የምስረታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ላለፉት 100 ዓመታት በሀገራችን የሕብረተሰብ ጤና ጥበቃ፣ በበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር፣ በሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲሁም በላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ታሪካዊና ወደር የማይገኝለት ነው። ተቋሙ የሀገራችንን የጤና ደህንነት ለመጠበቅና ወረርሽኞችን ለመመከት በየዘመናቱ የከፈለው መስዋዕትነት ሁልጊዜም በታሪክ መዝገብ ላይ በደመቀ ሁኔታ የሚታወስ ነው።
"ደም መለገስ ህይወትን ማዳን ነው፤ የሕብረተሰብ ጤናን መጠበቅ ደግሞ ሀገርን ማዳን ነው!"የኢትዮጵያ ደም ባንክ እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት የዜጎችን ህይወት ለመታደግና ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር በሚደረገው አገራዊ ጥረት ውስጥ የማይነጣጠሉ የቅርብ አጋሮች ናቸው። ደህንነቱ የተጠበቀ ደምና የደም ተዋጽኦ ለዜጎች እንዲደርስ በማድረግ እንዲሁም በላቦራቶሪ ጥራትና ምርምር ዙሪያ እንዲሁም የቅመ አደጋ መከላከል ዝግጁነት ላይ ያለን ትብብር የብዙዎችን ህይወት ለመታደግ አስችሏል።በቀጣይም ተቛማችን የአካል ክፍል እና የህብረህዋስ ማስተላለፍ ተግባራት ላይ በሙሉ አቅሙ ሲገባ የትብብር አቅማችን በእጅጉ እንደሚልቅ እምነታችን ነው።
ይህ ታላቅ የምስረታ በዓል፣ ተቋሙ በቀጣይም ለላቀ የሳይንስ ምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ይበልጥ ጠንካራ ለሆነ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት ግንባታ አዲስ ጉልበትና አቅም የሚሰጥ እንደሚሆን ፅኑ እምነታችን ነው።
በቀጣይ ዘመናትም የዜጎቻችንን ህይወት በጋራ ለመታደግና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ያለንን አጋርነትና ቁርጠኝነት ዳግም እያረጋገጥን፤ ለተቋሙ መላው አመራሮችና ሰራተኞች መልካም የክብረ በዓል ጊዜ እንዲሆንላችሁ እንመኛለን!
ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት መልካም የ100ኛ ዓመት ክብረ በዓል!
የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው።