የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ Ethiopian Teachers Association /EI/

  • Home
  • Ethiopia
  • Addis Ababa
  • የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ Ethiopian Teachers Association /EI/

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ Ethiopian Teachers Association /EI/ BETTER EDUCATION FOR BETTER WORLD!

የትምህርት ሚኒስቴር  በመላው ሀገሪቱ ትምህርት መስከረም 5/2019 ዓ.ም እንደሚጀመር አስታወቀ ወጥነት ያለው የማስተማር ሂደት እንዲኖር ለማስቻል ያዘጋጀውን የ2019 ዓ.ም አጠቃላይ የትምህ...
02/07/2026

የትምህርት ሚኒስቴር በመላው ሀገሪቱ ትምህርት መስከረም 5/2019 ዓ.ም እንደሚጀመር አስታወቀ

ወጥነት ያለው የማስተማር ሂደት እንዲኖር ለማስቻል ያዘጋጀውን የ2019 ዓ.ም አጠቃላይ የትምህርት ዘመን ዓመታዊ የጊዜ ሰሌዳ (ካላንደር) ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች አስተላልፏል።

​በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፦

ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም የአዲስ ተማሪዎች ምዝገባ ይከናወናል።

መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ትምህርት ይጀምራል።

ኢመማ 13ኛውን  የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በሀዋሳ ከተማ አካሄደ  የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከሚያከናውናቸው ትምህርት ነክ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ...
26/06/2026

ኢመማ 13ኛውን የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በሀዋሳ ከተማ አካሄደ

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከሚያከናውናቸው ትምህርት ነክ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ ማካሔድ ነው፡፡ በመሆኑም ሀዋሳ ከተማ በሚገኘው የማህበሩ የጋራ ህንፃ ላይ የተለያዩ ተባባሪ አካላት በተገኙበት ሰኔ 18/2018 ዓ/ም 13ኛውን የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ አካሂዷል፡፡
በኢፌደሪ ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ፣ የሲዳማ ክልል ምክትል ር/መስተዳድር እና የትምህረት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ በየነ በራሳ፣ የክልሎች፤ ከተማ አስተዳደሮችና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር አመራሮች፣ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ትምህርት ኮሌጅ፤ከከተማው በ1ኛ ደረጃ፣ በ2ኛ ደረጃ እንዲሁም ከቴ/ሙያ ኮሌጅ የተውጣጡ መምህራን በኮንፈረንሱ ታድመዋል።

የኢመማ ፕሬዚዳንትና በትምህርት ዓለም አቀፍ አፍሪካን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ማህበሩ ከመምህራን መብትና ጥቅም ጎን ለጎን በትምህርት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰው ይህን ኮንፈረንስ ልዩ የሚያደርገው በማህበሩ ህንጻ የተካሔደ የመጀመሪያው ኮንፈረንስ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ምክትል ር/መስተዳድር እና የትምህረት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ በየነ በራሳም በዚሁ ኮንፍረንስ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢመማ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ አንጋፋ ማህበር መሆኑ ብቻም ሳይሆን ሀገራዊ ፋይዳና ትርጉም ያላቸውን ተግባራት በብቃት እየተወጣ ያለ ማህበር በመሆኑ በዚህ ኮንፈረንስ የሚቀርቡ የጥናት ውጤቶች ምክረ ሀሳብን እንደ ክልላችን ወስደን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ኮንፈረንሱን በንግግር ከከፈቱት መካከል አንዷ ሲሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢመማ ጋር በትብብር በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ተቋርጦ የነበረው የመምህራን የክረምት የሥራ ላይ ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና በያዝነው ክረምት እንደሚጀምር ተናግረው የተለያዩ የመምህራን የጥቅማ ጥቅም ሰነዶችን ከማሀበሩ ጋር እየሰራን ነው በማለት በኮንፍረንሱ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ተናግረዋል፡፡

ከወለዲያ ዩኒቨርሲቲ፤ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲተ፤ ከሚዘን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በግጭት ዙሪያ፣ ቴክኖሎጂን አካቶ ማስተማር ላይ፣ በ12ኛ ክፍል የተማሪ ውጤት ፣በርዕሰ-መምህራን የአመራር ዘይቤ እና በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለውይይት ቀርበው ጥልቅ ውይይት ተደረጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የጋራ ውይይት ተደርጎ ኮንፈረንሱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ይህ ኮንፈረንስ የተሳካ እንዲሆን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ላደረጉት ድጋፍ ኢመማ በመምህራን ስም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች... እንኳን ለ1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል አደረሳችሁ።በዓሉ የሰላም የጤና እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።                   ...
27/05/2026

ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች... እንኳን ለ1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል አደረሳችሁ።
በዓሉ የሰላም የጤና እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።
ኢመማ

09/05/2026

ሊታረም የሚገባ አስተሳስብ ... "እንኳንም ዩንቨርስቲ አልገባሁ❗""

ሁሉም ዜጎች የዪኒቨርሲቲ ትምህርት ዕድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ እገር ትለወጥ ነበር፤ ስለዚህ ሊታረም የሚገባ አስተሳስብ ነው ።

#ቢዝነስሚዲያ l ከዱባ ወጥ ቀጥሎ ኢቶጲስ ውስጥ የማይወደድ ነገር ቢኖር ትምህርት ነው። አለመማር አንድ ነገር ሁኖ ሳለ የተማሩት ላይ መሳለቅ ደግሞ የሚገርም ነው።

ትምህርት አያስፈልግም ብለው የሚናገሩ ሰዎች በኩራት የሚያነሷት ነጥብ "የተማሩ ሰዎች የት ደረሱ" የምትለዋ ልክ ያልሆነ የማሸማቀቂያ ምክንያት ስትሆን፤ የተማሩት የት እንደደረሱ አብረን እንመልከት።

ከመሰረታዊ ጥናቶች እንጀምር።

1. ወንጀል ⛓

በ2021 Institute for Securities Studies (ISS) ባሳተመው ጥናት መሰረት 92.7% ገደማ ከባድ ወንጀሎች የሚፈፀሙት ዩንቨርስቲ ባልቀመሱ ግለሰቦች ሲሆን፤ 6.5% ወንጀሎች ዲግሪ ባላቸው እና ቀሪው 0.8% ብቻ ደግሞ ማስተርስ እና ከዛ በላይ ባላቸው ግለሰቦች የሚፈፀሙ ናቸው ይላል።

ይሄ ጥናት ኢቶጲስ ውስጥም የሚሰራ መሆኑን ለማወቅ፤ ስልክ ለመስረቅ ብሎ አንገት በጩቤ የሚወጉትን እና ወጡ ላይ ጨው አበዛሽ ብለው ሚስታቸውን በዘነዘና ከሚገሉት ሰዎች ጀምሮ መመልከት በቂ ነው።

እዚህ ጋር የተማረ ሰው ምን አተረፈ ካልክ? "ህሊና" የሚባል ነገር እልሀለሁ።

2. ገንዘብ 🪙

ሌላኛው የተማሩ ልጆች ላይ የመዘባበቻ ነጥብ፤ ስራ እና ገንዘብ የማጣታቸው ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ የነሱ ድክመት ሳይሆን የሀገሪቱ ድክመት ነው፤ እሱን ትተን ወደ ንግድ እንኳ ብንመለስ፤ ንግድ ላይም የተማረ እና ያልተማረ ሰው ቢሳተፍ የተማረው ሰው የተሻለ successful የመሆን እድል እንዳለው የሚያሳዩ ብዙ ዳታዎች አሉ።

ለምሳሌ አለማችን ላይ ካሉ ቢሊየነሮች መሀል 71 ፐርሰንቱ ከዩንቨርስቲ ዲግሪ እስከ PhD የጨረሱ ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው። Bill Gates ወይም Mark ZuckerBerge አይነት በጣም ጥቂት ባለሀብቶች በእርግጥ ከኮሌጅ ት/ት አቁመዋል፤ ነገርግን እነዚህ ግለሰቦች ት/ት ያቆሙት ከ Harvard እና Yale እንጂ ማትሪክ ወድቀው አይደለም።

ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን ሀብታሞቹ ደንቆሮ ሆኑ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ፤ አግባብም ነው። ለዚህ ቀላሉ መልስ "ቁጥር 1ን" ተመልከት ነው፤ የኛ ሀገር ሀብታም በአመዛኙ ደፋር፣ ወንበዴ፣ አጭቤ፣ አምታች ነው። ይሄንን ውንብድና ደፍሮ እንዲሰራ የሚያደርገው ደግሞ አለመማሩ ነው።

ኢትዮጲስ ውስጥ ለምን generational wealth እንደሌለ ታውቃለህ? አባት ሀብታም ሲሆን ልጆቹን ጥሩ ቦታ ያስተምራል፤ ከዛ ልጆች ህሊና ይኖራቸዋል፤ ከዛ የአባታቸውን የወንበዴ ቢዝነስ ማስቀጠል ይከብዳቸዋል፤ አለቀ።

የተማረ ሰው ቁጥር ማነስ ከPolitical Stability፣ ከPoverty Alleviation፣ ከInnovation & ከEntrepreneurship እና አጅግ ብዙ አሁን ላለንበት አዘቅት ምክንያቶች ጋር በብዙ ጥናቶች አስደግፎ ማስረዳት ይቻላል።

በአጭሩ ት/ት ምን ያደርጋል የሚልህ ነጋዴ ሂሳቡን የሚያሰራው በተማረ Accountant ነው፣ ሲከሰስ ተከራክሮ ንብረቱን የሚያስመልስለት የተማረ ጠበቃ ነው፣ ህንፆውን የሚያስገነባው በተማረ ኢንጂነር ነው፣ ሲያመው የሚሄደው የተማረው ዶክተር ጋር ነው፤ ከዛ አልፎ ልጁን አጥና እያለ የሚጨቀጭቀው እና ፅድት ያለ international school ልኮ የሚያስተምረው ይሄው ራሱ ሰውዬ ነው።

እና ምን ልልህ ነው፤
አለመማር አያኮራም።
እንኳንም ዩንቨርስቲ አልገባሁ አይባልም፤ ነውር ነው።

ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ቴሌግራም ገጽ የተወሰደ

የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር የመምህራን ሆስፒታል እና ሁለገብ ሕንጻዎች ግንባታ ሥራ የመሠረት ድንጋይ አሰቀመጠሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የሲዳማ ክልል ር/መስተዳድር  የተከበ...
03/05/2026

የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር የመምህራን ሆስፒታል እና ሁለገብ ሕንጻዎች ግንባታ ሥራ የመሠረት ድንጋይ አሰቀመጠ

ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የሲዳማ ክልል ር/መስተዳድር የተከበሩ አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት አካላት፣ የኢመማ ፕሬዚዳንት እና የትምህርት ዓለም አቀፍ ቦርድ አባል ዶ/ር ዮሐንስ በንቲና ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንቶች እንድሁም ሌሎች አጋር አካላት በተገኙበት በደመቀ ሥነሥርዓት የሁለገብ ህንፃና የሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል።

በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ የመምህራንን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የክልሉ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገልፀው የክልሉ መምህራን ማህበር ለሚያስገነባቸው የመምህራን ሆስፒታል እና ሁለገብ ሕንጻዎች ግንባታ ሥራ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

መምህራን በክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑንና በተለይ ከማህበሩ ጋር በመቀራረብ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የክልሉ መስተዳድር አቶ ደስታ የክልሉ መንግስት ለግንባታ ሥራው ማስጀመሪያ የሚሆን 50 ሚሊየን ብር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንና ሕንፃው ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው መምህራን በትውልድ ግንባታ ውስጥ ተሳትፏቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የመምህራን ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲሻሻል፣ ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲኖራቸውና ጤናቸው በአግባቡ ተጠብቆ በበለጠ ትጋት እንዲሰሩ ለማስቻል ማህበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ኢያሱ ፍቅሬ በበኩላቸው የክልሉ መምህራን ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ማህበሩ ከ46 ሺህ በላይ አባላትን በሥሩ መያዙን ጠቁመው የመምህራን መታከሚያ ሆስፒታልና ሁለገብ ሕንጻዎቹ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ በየደረጃው በመንግስት እየተደረገላቸው ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነው የማህበሩ አባላት ትውልድ የመቅረጽ ሀላፊነታቸውን በበለጠ ተናሳሽነትና ትጋት አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ለመምህራን ሆስፒታል የሚገነባው ሕንጻ ባለ 6 ወለል መሆኑን ገልጸው፣ ሁለገብ ሕንጻው ባለ 12 ፎቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ  በዓል በሰላም አደረሳችሁ። በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ  እንዲሆንላችሁ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ይመኛል
12/04/2026

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ እንዲሆንላችሁ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ይመኛል

02/04/2026

የመምህራን የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ...
በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ተሻሽሎ የወጣ

ጥቅምት 06/2018 ዓ/ም

መግቢያ
አንድ ሙያ ከሌላው የሚለይበት የራሱ የሆነ ሥነ ምግባር ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአገራችን የፍትሀብሔር ህግ ቁጥር 2031 ላይ አንድ ባለሙያ የተሰማራበትን ሙያ ስነ ምግባር ደንብ መጠበቅ እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 64 ንዑስ አንቀጽ 64.1 ላይ "አባሉ/ማህበሩ፣ ሙያው/መምህርነት/ ወይም የሚያስተምርበት ት/ቤት እንዳይታመን ወይም ተቀባይነት እንዳያገኝ መጣር ወይም አፍራሽ ተግባር መፈፀም አይገባውም" በማለት ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ዝርዝር የሥነ ምግባር ደንብ በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚዘጋጅ ተመክቷል።
የትምህርት ሥራ ዉጤታማ እንዲሆን መምህራን ከበርካታ አካላት ጋር መሥራት የሚጠበቅባቸዉ ሲሆን በተለይ ከሥራ ባልደረቦች፣ ተማሪዎች፣ ተማሪ ወላጆች፣ ትምህርት አመራሮች፣ ከአካባቢዉ ማህበረሰብ እና ከሙያ ማህበራቸዉ ጋር በቅርበት ሊሰሩ ይገባል። ስለሆነም ከእነዚህ አካላት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በመራሄ ሙያዉ/ሥነ ምግባር ደንብ የሚመራ ይሆናል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በየጊዜው ከኢትዮጵያ የትምህርት ልማት እድገት ጋር በሚራመድ መልኩ የሥነ ምግባር ደንብ ሲያዘጋጅ የቆየ ሲሆን ከዓለም አቀፍ ባህሪው የተነሳ በዘላቂነት የሚቆዩት ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ከወቅቱ የኢትዮጵያ የትምህርት ዕድገት ጋር በሚሄድ መልኩ ማሻሻል ተገቢ ነዉ።

በመሆኑም በአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1368/2017 አንቀጽ 55(1) ላይ የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ የማዘጋጀት ኃላፊነት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መሆኑ በተደነገገዉ እና በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አንቀጽ 64 መሠረት የተሻሻለ የመምህራን ሥነ ምግባር ደንብ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡

1. መምህራን ከሙያቸው ጋር
የመምህርነት ሙያ የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ ነው። ስለሆነም በዚህ ሙያ ለማገልገል የሚሰማሩ ግለሰቦች በጥንቃቄ መመረጥ ያለባቸዉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዴ ወደ ሙያዉ ዉስጥ የገቡ መምህራን ከሙያዉ ጋር ያላቸዉ ግንኙነት የሚመራበት ሁኔታ እንደሚከተለዉ ተዘርዝሯል።

1.1. በሙያቸው ያምናሉ፤ ሙያቸውንም ያፈቅራሉ፤ ይንከባከባሉ፡፡
1.2. መምህርነት የጠለቀ እውቀት፣ ችሎታ እና ክህሎትን የሚጠይቅና በጥንቃቄ መከናወን ያለበት ሙያ መሆኑን ተረድተው በግል ጥረት በማንበብ፤ ልምድን በመለዋወጥ፣ በስልጠናዎች በመሳተፍ፣ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም ሙያቸውን ያዳብራሉ፡፡
1.3. ትምህርት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚችል በማመን ንድፈ ሀሳብን ከተግባር በማዛመድ እና ትምህርት በአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ልማት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፡፡
1.4. እውቀት፣ ክህሎትና ዝንባሌ በውይይት በክርክርና በትችት ሊዳብር እንደሚችል በማመን ከተማሪዎችም ይሁን ከባልደረቦች የማያውቁትን ለመማር እና አስተያየቶችን ለመቀበል እንዲሁም የማያውቁትን ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ትምህርት የህይወት ዘመን መሆኑን ይገነዘባሉ፧ ያስረዳሉም
1.5. ችግሮችን ለመፍታት እና አዳዲስ ግኝቶችን ለመተዋወቅ በምርምር ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ፤ የሰሯቸውን የፈጠራ ሥራዎችንም ያስተዋውቃሉ፤ ለማህበረሰብ አገልግሎት እንዲውል ጥረት ያደርጋሉ፡፡
1.6. በእቅድ ይመራሉ፤ ትምህርትን በመርጃ መሳሪያዎች ደግፈው ያስተምራሉ/ያሰለጥናሉ፡፡
1.7. ትምህርት ሰኩላር መሆኑን ተገንዝበው ተማሪዎችን ሲያስተምሩ በስርዓተ ትምህርቱ ከተነደፈው ውጭ የግላቸውን አመለካከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አያራምዱም፡፡
1.8. የቁሳቁስ፣ የአይድዎሎጂ ወይም ሌላ ጥቅም ለማግኘት ሙያው የሚፈጥርላቸውን አጋጣሚ አይጠቀሙም፡፡
1.9. የመምህርነት ሙያ በሚስጢር እንዲያዝ የሚጠይቃቸውን ምስጢሮች ሁሉ ይጠብቃሉ፡፡
1.10. በሙያ ሥነ ምግባራቸውና በብቁ ዜግነት ስብዕናቸው በአርአያነት ይቀርባሉ፡፡
1.11. የሙያቸውንና የራሳቸውን ክብር ከሚነኩ ድርጊቶች ሁሉ ይታቀባሉ፡፡
1.12. በተማሪዎች መካከልም ይሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ግላዊ ልዩነቶች እንደሚኖሩ አምነው በመቀበል ግለሰባዊ አመለካከቶችን ያከብራሉ፡፡
1.13. ሙያቸውን ከብክነትና ከሙስና ይከላከላሉ፡፡
1.14. እራሳቸውን ለለውጥ ዝግጁ በማድረግ በየጊዜው ከሚደረጉ ገንቢ ለውጦች ጋር ይራመዳሉ፡፡
1.15. በመደበኛ መድረኮችም ይሁን በግላዊ ግንኙነት በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ በማወቅም ይሁን በቸልተኝነት ስለስራቸው ያሉትን እውነታዎች አዛብተው አያቀርቡም፡፡
1.16. የስራ አፈጻጸም ብቃታቸውን ለማሳደግ ራሳቸውን ለማሻሻል ዝግጁ ናቸው፡፡

2. መምህራን ከተማሪዎች ጋር
መምህራን የተማሪዎቻቸዉ የዕዉቀት አባቶችና እናቶች ናቸዉ። ስለሆነም የተማሪዎቻቸዉን ዝንባሌ በመለየት በዝንባሌያቸዉ መሠረት እየተንከባከቡ ማሳደግ እንዲሁም ብቁና ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንዲሆኑ ማብቃት ይጠበቅባቸዋል። በዚሁ መሠረት መምህራን ከተማሪዎች ጋር የሚኖሯቸዉ ግንኙነት የሚከተሉት ናቸዉ
2.1 የህፃናት መብት ድንጋጌዎችን ያከብራሉ፡፡
2.2 በተማሪዎች ላይ አካላዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ቅጣት አይፈጽሙም፡፡
2.3 ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸውን ያከብራሉ፡፡
2.4 ተማሪዎች በግል አቅጣጫና አመለካከት(Perspective) የማራመድንና ውሳኔ የመስጠት መብታቸውን ያከብራሉ፡፡
2.5 የተማሪዎችን የአካዳሚክ ነጻነት ይጠብቃሉ፤ማንኛውንም ጥያቄ የመጠየቅ፣ ማንኛውንም ሀሳብ የመግለጽና የማቅረብ መብታቸውን የከብራሉ።
2.6 መምህራን ከዘር፣ ከቀለም፣ ከእምነት፣ ከጾታ፣ ከዕድሜ፣ ከጋብቻ ሁኔታ፣ከአካል ጉዳት፣ ከብሔር ወዘተ አድልኦ ነፃ የሆነ አገልግሎት ለተማሪ ይሰጣሉ፡፡
2.7 ተማሪዎቻቸውን ይወዳሉ፤ ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን አክብሮት ይሰጣሉ፡፡
2.8 የአካል ጉዳት ላለባቸው ይሁን ሌሎች የልዩ ትምህርት ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
2.9 በሴት ተማሪዎች ላይ ጾታዊ ትንኮሳም ይሁን ሌሎች ጎጂ ተፅዕኖዎች ከማድረስ ይቆጠባሉ፤ እንዳይደርሱባቸውም ይከላከላሉ፡፡
2.10 ተማሪዎች ጤንነታቸውን እና ደህንነታቸውን ከሚጎዱ ሁኔታዎች እንዲጠበቁ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
2.11 የተማሪዎችን ዝንባሌና ችሎታ እንዲሁም የስነ ልቦናና የአካል እድገት ጠብቀው ትምህርቱን ይሰጣሉ፡፡
2.12 ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ እንዲደርሱ ያበረታታሉ፤እንደዝንባሌያቸዉ ማደግ እንዲችሉም ይመክራሉ
2.13 የእያንዳንዱ ተማሪ የትምህርት ፍላጎት የአካልና የስሜት ጥንካሬ እንዲሁም የማህበራዊ ግንኙነታቸውን ኮትኩቶ በማሳደግ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡
2.14 በሙያዊ ተግባራት ተማሪዎችን ሲያሳትፉ ስዕብናቸው እንዳይነካና እፍረት እንዳይሰማቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡
2.15 ተማሪዎች ከኩረጃ ነፃ ሆነዉ ፈተና በራሳቸዉ ሰርተዉ በራስ እንዲተማመኑ ይመክራሉ፤ ያደርጋሉ

3. መምህራን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር
የመማር ማስተመር ሥራ ስኬታማ እንዲሆንና መምህራን በሚየስተምሩበት የስራ ቦታ የተለያዩ ሠራተኞች የተሰማሩ ስለሆነ መምህራንን ጨምሮ ከሁሉም ጋር በጎና ገንቢ የሆነ ግንኙነት ሊኖራቸዉ የሚገባ ሲሆን ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ተዘርዝረዋል።
3.1 የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ለማዳበርና ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ለማብቃት ከባልደረቦቻቸውና ከሌሎች ሠራተኞች/ባለሙያዎች ጋር ይተባበራሉ
3.2 በመምህርነት ሙያ አዲስ ሥራ ለሚጀምሩና በዝውውር የሚመጡ መምህራን ከሥራውና ከአካባቢው ጋር ያለማምዳሉ፤ድጋፋቸውን ለሚፈልጉ ሁሉ ያልተቆጠበ እገዛ ያደርጋሉ፡፡
3.3 በባልደረቦቻቸው ሲጠየቁም ሆነ በት/ቤቱ በኩል የሱፐርቪዥን ሚና እንዲጫወቱ ሲጠየቁ ያለማመንታት ይተባበራሉ፡፡
3.4 ከሥራ ጓደኞቻቸውና ከኃላፊዎቻቸው ጋር ስራን ማዕከል ያደረገና ጤናማና ግልጽነት ያለበት ግንኙነት ይፈጥራሉ፤ በቡድን ሥራም ይሳተፋሉ፡፡
3.5 ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ቅሬታዎችን በውይይትና በሠላማዊ መንገድ በመግባባት ይፈታሉ፡፡
3.6 በባልደረቦቻቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመለካከት እና በዜግነት መብቶች ጣልቃ አይገቡም፡፡
3.7 ስለ ባልደረቦቻቸው የሚኖራቸውን ትችት ለሚመለከተው ክፍል ከማሳወቃቸው በፊት በቀጥታ ለችግሩ ባለቤቶች በመንግር እንዲታረሙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
3.8 አስፈላጊ በሆኑ መድረኮች ሁሉ መምህራንን የሚገነቡና የሙያውን ተቀባይነት ከፍ የሚያደርጉ አስተያየቶችን ያቀርባሉ፡፡

4. መምህራን ከወላጆች ጋር
ተማሪዎች ብቁ ይሆኑ ዘንድ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነዉ። በመሆኑም መምህራን ተማሪዎችን በሁለንትናዊ መልክ ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት የወላጆችን ድጋፍና ዕገዛ በእጅጉ ይፈልጋሉ። ይሄን ድጋፍ ለማግኘት ያስችላቸዉ ዘንድ የሚከተለዉን ማከናወን አለባቸዉ።
4.1 አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ወላጆች/አሳዳጊዎች ከትምህርት ቤት ጋር የቀረበ ግንኙነት ፈጥረው ለልጆቻቸው ደህንነትና ለትምህርታቸው እድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
4.2 ወላጆች/አሳዳጊዎች በልጆቻቸው ላይ ያሏቸውን መሰረታዊ ኃላፊነቶችና ልጆቻቸውን በተመለከተ መረጃዎችን የመጠየቅና የማማከር መብቶቻቸውን ያከብራሉ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተገቢውን መረጃ ይሰጣሉ፤ ያማክራሉ፡፡
4.3 የተማሪ ቤተሰብን ማንነት (Identity) ያከብራሉ፤ የቤተሰብን ግላዊ ምስጢር ይጠብቃሉ፡፡
4.4 ወላጆች/አሳዳጊዎች በልጆቻቸው ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ የት/ቤት ደንቦችንና ህጎችን እንዲያውቁ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

5. መምህራን ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር
ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በማህበረሰቡ ዉስጥ ብቻ ሣይሆን በዋናነት የሚያገለግሉት የአካባቢዉን ማህበረሰብ እንደመሆናቸዉ መጠን መምህራን በሚኖሩበት ማህበረሰብ ዉስጥ ተቀባይነት ያለዉ የአኗኗር ዘይቤ መከተል አለባቸዉ። የሚከተሉት ዝርዝሮች መምህራን ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸዉ የሚያመለክቱ ናቸዉ።
5.1 ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ክብርና ግምት ይሰጣሉ፤ የብሔር ብሔረሰብና ህዝቦችን እኩልነት ያከብራሉ፡፡
5.2 አስፈላጊ በሆኑ የህብረሰቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ይሳተፋሉ፡፡
5.3 የህብረተሰቡን ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ባህልና ልማድ ያከብራሉ፤ ኢ‐ሳይንሳዊ/ጎጂ ልማዶች በውይይትና በትምህርት እንዲወገዱ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
5.4 ለሀገራቸውና ለህብረተሰቡ ታማኞች ናቸው፡፡
5.5 የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡
5.6 ከህብረተሰቡ ለመማርና ህብረተሰቡንም ለማስተማር ግንኙነታቸውን ሥርዓት ባለው መንገድ ያደርጋሉ፡፡
5.7 ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስፋፋትና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
5.8 የትምህርት አመራር ቦርዶችንና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን የግል ጥቅም ለማግኘት ይሁን የማንኛውንም የፖለቲካ ድርጅት አመለካከት ለማራመጃነት አይጠቀሙም፡፡

6 መምህራን ከትምህርት አመራርና አስተዳደር ጋር
የትምህርት አመራሮችና አስተዳደሮች በተሰጣቸዉ ኃላፊነትና በሕግ መሠረት እንዲመሩና እንዲያስተዳድሩ የተመደቡ ስለሆነ ተባብሮ መሥራት ተገቢ ነው። በመሆኑም በት/ቤትና በየደረጀዉ ትምህርትን እንዲመሩ ከተመደቡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምህራን የሚከተሉ ግንኙነቶች ይኖሯቸዋል።
6.1 የሀገርቱን ህገ መንግስት፣ የሲቪል ሰርቪስ ደንቦችንና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎችን እንዲሁም የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውንና ሌሎች የትምህርቱ ስራ የሚመራባቸው ደንቦችን መመሪያዎችን በማወቅ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡
6.2 በተጠየቁ ጊዜ ሁሉ ስለ ትምህርት ደረጃና ስለ ችሎታቸው የተስተካከለ ወይም ትክክለኛ መረጃ ይሰጣሉ፡፡
6.3 ኩረጃን ይፀየፋሉ፤ የሌላዉን ዕዉቀት ዕዉቅና ሳይሰጡ (plagiarism) አይጠቀሙም
6.4 ከሙያው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ልዩ ልዩ የኃላፊነት ደረጃዎችን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፡፡
6.5 የቀጣሪ መሥሪያ ቤታቸውን ህግና ደንብ በመከተል በተመደቡበት ስራና ቦታ ይሠራሉ፡፡

7. መምህራን ከሙያ ማህበራቸው ጋር
አንድ ሙያ እንደሙያ ይወሰድ ዘንድ ከሚጠቀሱ መስፈርቶች መካከል የሙያ ማህበረሰብ (professional community) መኖር መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ነዉ። ይህ የሙያ ማህበረሰብ ሙያዉ ለዜጎች/ሀገር አስፈላጊ መሆኑን፣ የሙያዉ ተቀባይነት ከፍ እንዲል እና ለሙያዉ ባለቤቶች ጥቅም መከበር የሚሰራ ነዉ። ይህ ደግሞ የሙያ ማህበር ነዉ። ስለሆነም ወደ ማስተማር ሙያ ተቀላቅለዉ ባሉበት ጊዜ ወደውና ፈቅደው ለማገልገል መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ በመምህርነት ሙያ ዉስጥ የሚገኙ ሁሉ የሙያ ማህበሩ አባል የመሆን የዉዴታ ግዴታ አለባቸዉ። በመሆኑም መምህራን፥
7.1 የሙያ ማህበሩ አባል በመሆን ትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማሩ ስራ ተስማሚ አካባቢ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
7.2 በማህበሩ ደንብ መሠረት መብታቸውን ያስከብራሉ፤ ግዴታቸውንም ይወጣሉ፡
7.3 የማህበራቸውን ደንብና መርሆዎች ያከብራል፡፡
7.4 ማህበራቸው በሚጠናከርበት ሂደት ላይ አስተዎጽኦ ያደርጋሉ፡፡
7.5 ሙያዊ አንድነታቸውን መሠረት ያደረገ ህብረታቸውን በማህበራቸው አማካኝነት በማጠናከር ለሀገራዊ ልማት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
7.6 የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ በጥናትና ምርምር በመደገፍ ጭምር ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ማህበር እንዲሆን አስፈላጊውን ጥረትና እገዛ ያደርጋሉ፡፡
7.7 በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ እና በሥራ ክቡርነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር የማህበሩ ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን በሚገኙበት/ባሉበት ሁሉ የራሳቸውን ድርሻ ይወጣሉ፡፡
7.8 የሙያ ማህበራቸው፣ የአባላት መብትና ጥቅም፣ ማህበራዊ ደህንነት፣ የሙያውን ክቡርነትና የአካዳሚክ ነፃነት የሚያስከብር፣ በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ እና በቁሳቁስ ተደራጅቶ ጠንካራ ማህበር እንዲሆን የሙያ ማህበር አባልነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡

8. ርዕሳነ መምህራንና ምክትል ርዕሳነ መምህራን
በዚህ ሥነ ምግባር ደንብ ለመምህራን የተዘጋጁት ድንጋጌዎች እንደአግባቡ ለርዕሳነ መምህራንም ሆነ ለምክትል ርዕሳነ መምህራን ተፈፃሚ ይሆናሉ

9. ስለ ፆታ አገላለጽ
በዚህ ደንብ ዉስጥ እንደ ወንድ የተገለጸዉ ለሴትም ያገለግላል

10. የተፈጻሚነት ወሰን
ኢትዮጵያውያን ከሙያው ማግኘት ከሚገባቸው ጥቅም አኳያና የመምህርነት ሙያ የሁሉም ሙያዎች ምንጭ እና የትውልድ ጉዳይ በመሆኑ ይህ የሥነ ምግባር ደንብ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስትም ሆነ በግል ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት እና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እንዲሁም በውጪ ሀገር በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት በሚያስተምሩ ትምህርት ተቋማት መምህራን ላይ ተግባራዊ ይሆናል።

11. የደንቡ አፈጻጸም
በአዋጅ ቁጥር 1368/2017 አንቀጽ 55(2) ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው ባለው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መዋቅር ስለ ደንቡ አፈጻጸም የሚከታተል ንዑስ ኮሚቴ ይደራጃል

12. ደንቡን ስለመሻሻል
ይህን ደንብ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ሊያሻሽለዉ ይችላል

13. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ የሥነ ምግባር ደንብ በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ከፀደቀበት ከጥቅምት 06 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ የፀና ይሆናል።

ዮሐንስ በንቲ(ዶ/ር)
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚደንት

ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
20/03/2026

ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1447ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው ዜጐቻችንን በማስመልከት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የተሰማውን ጥልቅ ...
13/03/2026

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በጋጫ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው ዜጐቻችንን በማስመልከት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለወዳጅ ቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይመኛል።

ለጠቅላላ ዕውቀት  ይጠቅም ዘንድ ከመምህራን ሙያና የስራ ዘርፍ ጋር የተያያዙ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እየተተገበሩ የሚገኙ ህጎች...
03/03/2026

ለጠቅላላ ዕውቀት ይጠቅም ዘንድ ከመምህራን ሙያና የስራ ዘርፍ ጋር የተያያዙ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እየተተገበሩ የሚገኙ ህጎች...

Address

Addis Ababa
13205

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ Ethiopian Teachers Association /EI/ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር /ኢመማ/ Ethiopian Teachers Association /EI/:

Shortcuts

Share