08/11/2025
“ወጣቶች ለሰላም መረጋገጥ የማይተካ ሚና አላቸው!”
የቦሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት “ሀገር በቀል የሰላምና የመቻቻል እሴቶች ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ክፍለ ከተማ አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ አካሄደ፡፡
ጽ/ቤቱ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ቦሌ ክ/ ከተማ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ከአሥራ አንዱም ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መርዕድ አስፋው የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ባሕሎች፣ እምነቶች እና ታሪኮች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ወደላቀ ከፍታ እንድትጓዝ ሰላም ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች ለሀገር ግንባታ ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው” ያሉት ኃላፊው፣ ወጣቱ ትውልድ ሀገር በቀል የሰላምና የመቻቻል እሴቶችን በአግባቡ ተረድቶ ሰላሟ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ መረባረብ እንዳለት አክለው አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ቦሌ ክ/ ከተማ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ ወጣት ታምራት ሚሊዮን በበኩሉ ወጣቶች ሰላም፣ ልማት እ ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ በግንባር ቀደምነት በመሰለፍ ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን አውስቶ፣ በሀገር በቀል የሰላምና የመቻቻል እሴቶች ዙሪያ ወጣቶች የጋራ መግባባት በመያዝ ጸረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን ለማክሸፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ኮንፈረንሱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክቷል፡፡
በኮንፈረንሱ “ሀገር በቀል የሰላምና የመቻቻል እሴቶች ለትውልድ ግንባታ በአዲስ አበባ” በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ጥቅምት 29/2018