09/06/2026
ለብዙዎች ምናልባት ተምሮ ጨርሶ መመረቅ፤ በተለይ በመጀመሪያ ዲግሪ አሁን አሁን ብዙም ብርቅ አይደለ ይሆናል። እውነት ነው ከፍ ብሎም ባለ ደረጃ በተማሩበት መስክ መጨረስና መሸለም ምንም ሊሆን ይችላል።
ግን የመንገዱ ነገር ከዚህ ይለያል። በተለይ ደግሞ እግዚአብሔር ሲመራ እሺ ብሎ ለሚጓዝ ሂደቱ ልብ አንጠልጣይ ነው።
ብዙዎች እንደሚሉ የእግዜር መንገድ መሃሉ አይነገርም! አቀበት፣ ቁልቁለት፣ ሜዳ፣ ጎርባጣ፣ ስርጓጎጥ፣ ዓይነቱ እልፍ ነው። ግን ደግሞ እርሱም አለ። ጌታ ካለ ደግሞ የትም ይመቻል። የአእኔም የETC ጉዞዬ ይሄንኑ ነው የሚመስለው።
እውነቱ የአራት ዓመት ትምህርትን ሰባት ዓመታት አድርጌ ስጨርስ በመሃል እንዳልጨርስ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግዳሮቶች ነበሩ ግን በእግዚአብሔር ሃይል አሸነፍኳቸው።
በእነዚህ ዓመታት ካሳለፈኳቸው ከባባድ ሁኔታዎች ውስጥ ትልቁ ሶስተኛዋን ልጄን ሩትዬን ለስምንት ወራት በማህፀኔ ተሸክሜ ቀኑ ደርሶ ላቅፋት ጓጉቼ ያጣሁበት ጊዜ ነበር። በዚህ ምክንያት አቋርጬም ነበር።
ደግሞ የካሳው ጌታ የተወደደውን ልጄን ክርስቲያንን የሰጠኝና የተቀበልኩትም በእነዚሁ ዓመታት መሃከል ነበር።
ሌሌችም እዚህ ልገልጣቸው የማልችላቸውን አስቸጋሪ ጎዳናዎችን ተጉዣለሁ። በርግጥ ይሄም ብርቅ አይደለም። ግና አብሮኝ የተጓዘው ኢየሱስና ከመንገዴ የተማርኳቸው መርኾዎች ብርቅ ናቸው። ከዚህ መንገድ ውጪ አይገኙምና!
እናማ ምን ለማለት ነው? እያለቀሱ የሚስቁበት፣ እየታመሙ ለሌሎች የሚያበሩበት መንገድ። ይህ በጌታ መንገድ ላይ ብቻ የሚገኝ እውነት ነው። ይህ ደግሞ ከብርቅ በላይ ነው!